
ከ 2 ሰአት በፊት
ከፈረንሳይ መዲና ፓሪስ በሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ በምትገኘው ሞ ከተማ አራት ልጆቹን እና ባለቤቱን በመግደል የተጠረጠረው የ33 ዓመት ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ።
በስም ያልተጠቀሰው ግለሰብ ከገደላቸው ልጆቹ መካከል የ9 ወር ጨቅላ እንደሚገኝበት ታውቋል።
ዐቃቤ ሕግ ዣን-ባቲስት ብላዲዬ የሟች ልጆች ዕድሜ ከ9 ወር እስከ 10 ዓመት መካከል መሆኑን ተናግረዋል።
ፖሊስ ግድያው በተፈጸመበት አፓርታማ መኖሪያ ቤት ሲደርስ ቤቱ በደም ተጨማልቆ ነበር ብሏል።
ወንጀሉን በተመለከተ ለፖሊስ ጥቆማ የደረሰው አንዲት ጎረቤት የቤተሰቡን አባላት ለማግኘት ያደረገችው ተደጋጋሚ ጥረት ሳይሳካ ቀርቶ የቤቱ በር እጀታ ላይ ደም ካየች በኋላ ነው።
ፖሊስ ወንጀሉ በተፈጸመበት ቦታ ሲደርስ ከአባት ውጭ ሁሉም የቤተሰብ አባላት “በአሰቃቂ ሁኔታ” ሕይወታቸው አልፎ ማግኘቱን ገልጿል።
ከዚያም የደኅንነት መከታተያ ካሜራዎችን በመከተል ተጠርጣሪውን ከከተማዋ ርቆ በሚገኝ ከተማ በወላጅ አባቱ መኖሪያ ቤት በቁጥጥር ስር አውሎታል።
ዐቃቤ ሕጉ ተጠርጣሪው ከዚህ ቀደም በወንጀል ተከሶ ባያውቅም የቤት ውስጥ ጥቃት በመፈጸም በፖሊስ ይታወቃል ብለዋል።
- ኢትዮጵያ ዕዳቸውን መክፈል ካልቻሉ አገራት ተርታ ተመደበችከ 8 ሰአት በፊት
- የሱተን ግምቶች፡ ዩናይትድ አሁንም ይሸነፋል፤ ሲቲ ነጥብ ይጥላል26 ታህሳስ 2023
እአአ 2019 ላይ ግለሰቡ ባለቤቱን በስለት አጥቅቶ ነበር ብለዋል ዐቃቤ ሕጉ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ።
ዐቃቤ ሕጉ እናት እንዲሁም የ10 እና የ7 ዓመት ሴት ልጆች በርካታ ቦታ በስለት ተወግተው መደገላቸውን ተናግረው ሁለቱ የአራት እና የ9 ወር ልጆች ግን አካላቸው ላይ የሚታይ ጉዳት የለም ብለዋል።
የአራት ዓመቱ ልጅ እና የ9 ወር ጨቅላው “ታንቀው ወይም በውሃ ተዘፍቀው” ተገድለው ሊሆን ይችላል ሲሉ ዐቃቤ ሕግ ዣን-ባቲስት ተናግረዋል።
ጎረቤቶች የ35 ዓመት ዕድሜ ያላትን የአራት ልጆች እናት “መልካም እና ከሁሉም ተግባቢ” ሲሉ ይገልጿታል።
አንዲት ጎረቤት ከሟቿ ጋር በነበራት ንግግር በግድያ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር የዋለው ባል ከሥራው በመፈናቀሉ ምክንያት ድባቴ ውስጥ እንደገባ ነግራናለች ብላለች።
ግለሰቡ እአአ 2019 ባለቤቱ ላይ የስለት ጥቃት ከፈጸመ በኋላ ክስ ሳይመሰረትበት የቀረው ባለቤቱ ክስ ባለመመስረቷ እንዲሁም በወቅቱ የአእምሮ ጤና እክል ስለነበረበት ነው ተብሏል።
በቅርቡ በፈረንሳይ አሰቃቂ የሚባሉ በቤተሰብ የሚፈጸሙ ግድያዎች ተዘግበዋል።
ኅዳር ወር ላይ የ41 ዓመት አባት የ4፣ 10 እና 11 ዓመት ሴት ልጆቹን ከገደለ በኋላ እጁን ለፖሊስ ሰጥቷል።
ከጥቂት ወራት በፊት ደግሞ አንድ የፖሊስ አባል ሦስት ልጆቹን ከተገደለ በኋላ በቁጥጥር ስር ውሎ ነበር።