
ከ 1 ሰአት በፊት
ግዙፉ የዴንማርክ የመርከብ ጭነት ማጓጓዣ ድርጅት ሜርስክ በደኅንነት ስጋት ምክንያት አቋርጦት የነበረውን የቀይ ባሕር እና የኤደን ባሕረ ሰላጤ የጉዞ መስመርን ዳግም መጠቀም ሊጀርም መሆኑን አስታወቀ።
ሜርስክን ጨምሮ በርካታ የመርከብ ጭነት አጓጓዣ ድርጅቶች የሁቲ አማጺያን በቀይ ባሕር ዕቃ ጫኝ መርከቦችን ዒላማ ማድረጋቸውን ተከትሎ ይህን የጉዞ መስመር መጠቀም አቁመው ነበር።
ሜርስክ በቀይ ባሕር እና ኤደን ባሕረ ሰላጤ በኩል ጉዞ ለመጀመር ዝግጅት ላይ ነኝ ያለው በቀጠናው የሁቲ አማጺያን የሚያደርሱትን ጥቃት ለመመከት ዓለም አቀፍ ወታደራዊ ዘመቻዎች መጀመራቸውን ተከትሎ ነው።
ሃፓግ-ሎይድ የተባለ የጀርመን የመርከብ ጭነት ማጓጓዣ ድርጅትም እንዲሁ የጉዞ መስመሩን ዳግም ስለመጠቀም ውሳኔ አስተላልፋለሁ ብሏል።
ሰፊ የየመን ግዛትን ተቆጣጥረው የሚገኙት የሁቲ አማጺያን ከእስራኤል እና ከሐማስ ጦርነት መቀስቀስ ወዲህ በቀይ ባሕር በኩል በሚያልፉ ግዙፍ የጭነት መርከቦች ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ ቆይተዋል።
- ኢትዮጵያ ዕዳቸውን መክፈል ካልቻሉ አገራት ተርታ ተመደበችከ 8 ሰአት በፊት
- በፈረንሳይ ሚስት እና አራት ልጆችን በመግደል የተጠረጠረው በቁጥጥር ስር ዋለከ 2 ሰአት በፊት
- የሱተን ግምቶች፡ ዩናይትድ አሁንም ይሸነፋል፤ ሲቲ ነጥብ ይጥላል26 ታህሳስ 2023
አማጺያኑ ከእስራኤል ጋር ጦርነት ውስጥ ለገባው ሐማስ ያላቸውን ድጋፍ በይፋ ከገለጹ በኋላ፣ በቀይ ባሕር በኩል አድርገው ወደ እስራኤል የሚያቀኑ መርከቦችን ዒላማ እንደሚያደርጉ በይፋ አሳውቀዋል።
ባለፉት ሳምንታትም ወደ ተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ነዳጅ እና የተለያዩ ምርቶችን ጭነው የሚንቀሳቀሱ ግዙፍ መርከቦችን በሚሳኤል እና በድሮን ሲያጠቁ ቆይተዋል።
ቀይ ባሕር ወደ አውሮፓ፣ መካከለኛው ምሥራቅ፣ ሰሜን እና ምሥራቅ አፍሪካ እንዲሁም ወደ እስያ ለሚላኩ ምርቶች ቁልፍ መተላለፊያ ነው።
በሰሜን በኩል የግብፁን ሱዌዝ ካናል እንዲሁም በደቡብ አቅጣጫ ጂቡቲ፣ የመን እና ኤርትራን በሚያዋስነው የባብ አል-ማንዳብ መካከል የሚገኘው ቀይ ባሕር የዓለማችን 12 በመቶ ወይም አንድ ትሪሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው ምርት በየዓመቱ የሚተላለፍበት የውሃ ክፍል ነው።
ይህ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የሚደረግበት የውሃ አካል ደኅንነቱ መረጋገጥ ባለመቻሉ የመርከብ ጭነት ማጓጓዣ ድርጅቶች ረዥም ጊዜ እና ብዙ ነዳጅ አባክነው በደቡብ አፍሪካ በኩል አድርገው ወደ መዳረሻቸው እያቀኑ ነው።
ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ እና በሌሎች ምርቶች ዝውውር ላይ ጫናን ስለሚፈጥር የዋጋ ጨማሪ ሊያስከትል እንደሚችል ባለሙያዎች ሲናገሩ ቆይተዋል።
አሜሪካ ከሌሎች አጋር አገራት ጋር በመሆን በውሃ አካሉ የሚያልፉ መርከቦችን ደኅንነት ለማረጋገጥ ‘ፕሮስፔሪቲ ጋርዲያን’ የተሰኘ ዓለም አቀፍ ወታደራዊ ዘመቻ ጀምራለች።
ይህን ዓለም አቀፍ ጥምረት እንደ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ባሕሬን፣ ኖርዌይ እና ስፔንን የመሳሰሉ አገራት ተቀላቅለዋል።
ሜርስክ ይህን ዘመቻ ተከትሎ መርከቦች በቀይ ባሕር በኩል እንዲያልፉ የተያዘን ዕቅድ በመተግበር ላይ ነኝ ብሏል።