December 26, 2023 – Konjit Sitotaw 

መጪውን የ2016ዓም የእየሱስ ክርስቶስ እና የቅዱስ ላሊበላ የልደት ወይንም የገና በዓልን አስመልክቶ ከላስታ አውራጃ ብ/ጄኔራል አሳምነው ፅጌ ፋኖ ክፍለ ጦር የተሰጠ መግለጫ….

በኦርቶዶክሳውያን ዘንድ በታላቅ ጉጉት የሚጠበቀው የጌታችን የመድኃኒታችን የእየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በየዓመቱ በታሪካዊቷ የደብረ ሮሃ ከተማ ከንጉሱ እና ከፃድቁ አባታችን ከቅዱስ ላሊበላ ልደት ጋር እንደሚከበር ይታወቃል። ሆኖም ግን ጦርነት ጠማቂው መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት አምስት አመታት በህዝቡ ላይ የተለያዩ የሽብር ሴራዎችን በማመቻቸት በተለይም የአማራን ህዝብ በመጨፍጨፍና በማፈናቀል ህዝቡን ሰቆቃ ላይ ጥሎት ይገኛል። መላ ሀገሪቱንም በደም አላባ እያጠባት እንደሆነ ማንም የሚያውቀው ሀቅ ነው። ህዝቡ ተረጋግቶ መንፈሳዊ ኩነቶችን በመከወን ከፈጣሪው ጋር እንዳይገናኝ ቤተ እምነቱን በማውደም፣ ካህናቱን በማረድ እና በድንጋይ ቀጥቅጦ በመግደል ጉባዔያት እንዲፈቱ እና ተተኪ ካህናት እንዳይወጡ ብዙ ስራዎችን ሰርቷል፣ በዚህ ሁሉ ችግር ከመታረድ ያመለጡ ምዕመናን በመንፈሳዊ ሀብት በመጎሳቆል ውስጥ ሆነው አምስት የገና በዓላትን አክብረዋል። ከዚህ ባሻገር ይህ ሊቀ ሠይጣን የሆነ ስርዓት ሀገራችንን ከጭስ አልባው ኢንዱስትሪ ቱሪዝም ከሀገር ውስጥና ከውጪ ጎብኝዎች ማግኘት የሚገባትን ሠፊ የቱሪዝም ሀብት እንዳታገኝ አድርጓታል። በተለይም የአካባቢያችን የላስታ ላሊበላ ህዝብ ኑሮውን በከፍተኛ ሁኔታ ከሚደጉምበት የሀብት ምንጩን በማድረቅ ለከፋ ችግር አጋልጦት ይገኛል።

በመሆኑም የዘንድሮውን የገና በዓል የቤተክርስቲያኗ ልጆች እንደመሆናችን ሁሉ አሸባሪው መንግስት የፈጠረውን የህልውና የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ለመቀልበስ ስርዓቱንም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ እንደ አንድ የአማራ ፋኖ ሠራዊት ከሌሎች አደረጃጀቶች ጋር ተናበን እየሰራን እንገኛለን። ይሁን እንጅ መንግስት ነኝ የሚለው አሸባሪ ቡድን የፈረሰውን የመንግስትነት ሚናውን አለሁ ለማለት በልሳን ሚዲያዎቹ በኩል የተከበረውን የልደተ ክርስቶስ በዓልን የፖለቲካ መጠቀሚያ ለማድረግ የ24/7 ለፈፋ ከጀመረ ቆይቷል።

ይህንን የልደት በዓልን ለማክበር የሚዲያ ቅስቀሳ ሳይሰሙ በክርስቶስ ፍቅር እና በቅዱስ ላሊበላ ድንቅ ጥበብ ተማርከው ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍል በየብስ ትራንስፖርት እና በአውሮፕላን በተለይም ከጎጃም፣ ከጎንደር፣ ከትግራይ፣ ከአገው የእግር ጉዞ በማድረግ ወደ ቅዱሱ ስፍራ የሚተሙ እንደሆነ ይታወቃል።

ስለዚህ በእኛ በላስታ አውራጃ ጄ/ል አሳምነው ፅጌ ክ/ጦር ፋኖ በኩል መንፈሳዊ ገብያ ለመሸመት የሚመጣውን ህዝብ እና ጎብኝ በተቆጣጠርናቸው ወረዳዎችና ቀበሌዎች አስተማማኝ የፀጥታ ቁጥጥር በማድረግ የድርሻችንን የምንወጣ መሆኑን በይፋ እንገልፃለን።

በዚህ መሰረት ህዝቡ በላስታ፣ በመቄት ዙሪያ ያሉትን:-
– ዳግማዊ ላሊበላ
– ገነተ ማርያም
– እመኪና መድኃኒዓለም
– ማውሬ እስጢፋኖስ
– ቅዱስ ናኩቶለአብ
– አሸተን ማርያም
– ብልባላ ጊዮርጊስ
– አርባዕቱ እንሰሳ
– ይምርሃነ ክርስቶስ
– ሣርዝና ሚካኤል
እና ሌሎችን ጥንታዊ ገዳማትን መሳለምና በነፃነት መጎብኘት እንደምትችሉ እናረጋግጣለን። ከዚህ ጋር ተያይዞ የዓለም የቀይ መስቀል ማህበርና መሠል ማህበራዊ አገልግሎት የምትሰጡት ተቋሞች ለህዝቡ የሚያስፈልገውን የድንገተኛ ህክምና እና ሌሎች አገልግሎቶችን ለመስጠት መንቀሳቀስ እንደምትችሉ በዚሁ አጋጣሚ ክፍለ ጦር ያሳውቃል።

ይህንኑ በዓል አስመልክቶ ክፍለ ጦሩ የጣላቸው ክልከላዎች የሚከተሉት ናቸው።

1ኛ= የድሮንና ሌሎች የሽብር እንቅስቃሴዎችን ለመከታተል ሲባል አገር አቋራጭ አሽከርካሪዎች ለመንፈሳዊ አገልግሎት በምትንቀሳቀሱበት ጊዜ ከላሊበላ ከተማ ተነስታችሁ ወደ ገጠራማዎቹ ገዳማት ስትንቀሳቀሱ በተለምዶ ከሰኞ ገብያ እስከ ይምርሃነ ክርስቶስ ድረስ ተደጋጋሚ ክላስክና መዝሙሮችን ወደ ውጭ ማውጣት የተከለከለ ነው።

2ኛ= የአካባቢውን መልካዓ ምድር ያላገናዘበ የፍጥነት ወሰን በመጠቀም ማሽከርከር የተከለከለ ነው።

3ኛ= ተሽከርካሪው ከተፈቀደለት ተሳፋሪ የመያዝ አቅም በላይ መጫን የተከለከለ ነው።

4ኛ= ከተፈቀደው ታሪፍ በላይ በተለይ ለመሳለም የመጡ ምዕመናንን ማንገላታትና ከታሪፍ ውጭ ማስከፈል የተከለከለ ነው።

5ኛ= ከጧቱ 12:00 በፊትና ከምሽቱ 1:00 ቡኋላ ማንኛውም ተሽከርካሪ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው።

6ኛ= የጠላትን የድሮንና ሌሎች የሽብር እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር ሲባል ከገዳማቱ ቅፅር ውጪ ለፀጥታ ችግር የሚያስቸግር ማንኛውንም መዝሙርና ጭፈራ ማድረግ የተከለከለ ነው።

7ኛ= ማንኛውም ሰው በተለይ ከገዳማቱ ውጭ ከምሽቱ 2:00 ቡኋላ መንቀሳቀስ አይፈቀድለትም።

8ኛ= በዓሉን አስመልክቶ በምግብና መጠጥ እንዲሁም በሌሎች የሸቀጥ ምርቶች ላይ የሚደረጉ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ በፍፁም የተከለከለ ነው።

9ኛ= ከህዝባዊ ደህንነት በተገኘ መረጃ መሰረት አሸባሪው የአብይ መንግስት የፋኖን ስም ለማጠልሸት እና ከህዝብ ለመነጠል የወረደ የሽብር ሴራ ሊሰራ እንደሚችል መረጃዎች ያመላክታሉ ስለዚህ ህዝቡ በንቃት በመንቀሳቀስ ራሱን እንዲጠብቅ እና የሽብር ሴራዎችን ከወዲሁ እንዲያከሽፍ እናሳስባለን።

ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት ስምንት እገዳዎች እንዳሉ ሆነው ሌሎች ወንጀሎች እንዳይፈፀሙ ክፍለ ጦሩ በንቃት መስራት የሚያስችለውን ዝግጅት መጨረሱን እያሳወቀ ከታህሳስ 15/2016ዓም ጀምሮ ማንኛውም መንፈሳዊ ጎብኝ በነፃነት እንዲጎበኝ ጥሪ እያቀረብን የሚገጥሙ ችግሮች ካሉ በቅርብ ርቀት ለሁሉም ሰው ምቹ እና በማንኛውንም ሁኔታ የሚፈጠርን የፀጥታ ችግር ለመቆጣጠር ዝግጁ ለሆኑት የፋኖ አባሎቻችን ማሳወቅ የምትችሉ መሆኑን እንገልፃለን።

መልካም የገና በዓል ዝግጅት!!