December 26, 2023 

ከዕዳ ወደ ዕዳ ወደ ፍዳ

(ዶር ስዩም መኮነን የቀድሞ የስላም ሚንስቴር ዲኤታ)

የለውጡ ወቅት የሀገራችን መሰረታዊ ስብራቶች ማለትም ሀገራዊ አንድነት፣ የዴሞክራሲ፣ የእኩልነት፣ የፍትሃዊነት ችግር ይፈታል፤ ዘላቂ ሰላም ያረጋግጣል በሚል ትልቅ ተስፋ የተጣለበት፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ድጋፍ ያገኘ ነበር፡፡ ይሁንና ካለንበት አዘቅጥ (ዕዳ) ከመውጣት ይልቅ ከእለት ወደ እለት በሁሉም የመለኪያ መስፈርቶች እየወረድን፣ የአለም መሳቂያ መሳለቂያ ሆነናል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ የብልጽግና ፓርቲ እና የመንግስት ቁመና የወረደ፣ የመንግስታዊ ባህሪ ያልተላበሰ፣ ከህዝብ የተነጠለና የተጠላ፣ አባላቱ በራስ የሴራ ፖለቲካ ተጠምደው የራስን የነጠላ ድብቅ ዓላማና ፍላጎት ለማሳካትና በሌሎች ላይ ለመጫን፣ የራስ ታላቅ ሀገር ለመመስረት የሚሯሯጡበትና የሚራኮቱበት፣ የአላማና የተግባር አንድነት ያልጠፈጠረበት ፓርቲና መንግስት ነው ብሎ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ ለዚህም ትልቅ ማሳያ ህግ-ማስከበር የተሳነው፣ 70% የሚሆነውን የኢትዮጰያ ህዝብና አካባቢ (ለምሳሌ አማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያ …ክልሎች) በቅጡ መምራት የማይችል መንግስትና 13 ሚሊየን የሚሆኑ የራሱ አባላት እንኳን እምነት የማይጥሉበትና የማይቀበሉት በቁሙ የሞተና በአሸዋ ላይ የተሰራ ፓርቲ መሆኑ ነው፡፡

ጠቅለል ብሎ ሲታይ “በለውጡ ዘመን” ሀገራችን እና ህዝባችን በግጭትና ጦርነት አዙሪት ውስጥ የገባንበት፣ ዜጎች በገፍ የሚፈናቀሉበት፣ የሚገደሉበት፣ ተጠያቂነት የሌለበት ስርዓት ተፈጥሯል፡፡ በፖለቲካ ረገድ በፓርቲ ውስጥም ይሁን በውጭ የሀሳብ ነጻነት የሌለበት፣ አድር ባዮች የሚሾሙና እርስ በርስ የሚንቆለጳጰሱበት፣ በመንግሰት ደረጃም ተጠያቂነት ጠፍቶ ጥቂት ባለጊዜዎችና በጥቅም የተሳሰሩ ቡድኖች እንደፈለጉ የሚፈነጩበት፣ በሙስና የተዘፈቁበት፣ ሀገር አፍራሽና ማህበረሰብን እርስ በርስ የሚያጋጭ ንግግር በማድረግ መርዝ የሚረጩበት ስርዓት ሆኗል፡፡ በተቃራኒው በፓርቲው እና በመንግሰት መርህ እየተመሩ፣ ነጻ ሀሳብ የሚያራምዱና የሚተቹ፣ ሙስናን የሚታገሉ አባላት የተለያየ ታርጋ የሚሰጣቸውና የሚፈረጁበት፣ በፈጠራ ክስ የሚታሰሩበት ሀገር ተፈጥሯል፡፡

በተለይ ደግሞ ያለፈውን የኢህአዴግ ውርስ አጠናክሮ በማስቀጠልና በስጋት በማየት የአማራ የህዝብ ተመራጮች፣ ባለሀብቶች፣ ምሁራን፣ ጋዜጠኞች፣ አንቂዎች፣ ተጽእኖ ፈጣሪዎች በመላው ሀገሪቱ ያለህጋዊ ስርዓት የሚታፈኑበት፣ የሚሰቃዩበት፣ የሚታሰሩበት፣ የሚገደሉበት፤ እንደ ክልልም አቅመቢሶችና ተላላኪዎች በባትሪ ተፈልገው የሚሾሙበት፣ አቅም ያለቸው የተለያየ ስም እየተሰጠ የሚገፉበት፣ እንደህዝብ በክልሉም ውስጥ ይሁን ከክልሉ ውጭ ከለውጡ ጊዜ ጀምሮ ለተከታታይ ዓመታት ማህበራዊ እረፈት ያጣበት ዘመን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የዘመናት ብሶትና ስቃይ የወለደው ጠንካራ የአማራ እንቅስቃሴ ተፈጥሯል፡፡ ከአሁን በኋላ በተለመደው መንገድ አማራን መምራትና ማጥቃት የማይቻል መሆኑን በግልጽ ያሳየ ነው፡፡ ትግሉ የአማራ ህዝብ የራሱን ፍላጎትና ህልውና ከሌሎች ጋር በጋራ በመሆን የሚወስን ይሆናል፡፡ በአሁኑ ሰአት የአማራ ህዝብ በፋኖ መሪነት እያደረገ ያላው ትግል ፍትሀዊና ለመላው ኢትዮጰያ ህዝብ የተሻለ ስርዓት ለማምጣት የሚደረግ ትግል ስለሆነ ሁሉም የኢትዮጰያ ህዝብ ያለማወላወል ሊደግፈው ይገባል!!!!!!!

ምንም አንኳ በግሌ በህዝብ ላይ ያደረስኩት በደል ባይኖርም፣ እንደ አንድ የመንግስት አካል ሆኘ በቆየሁባቸው ጊዜያት በህዝብ ላይ ለደረሰው ጉዳትና በደል ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡