December 26, 2023 – Konjit Sitotaw
በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ኮምቦልቻ ወረዳ በሮ ቀበሌ ውስጥ በተፈፀመ የድሮን ጥቃት፣ በዚኹ ቀበሌ የምትገኘው የበሮ ሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች መገደላቸውን ዋዜማ ከአካባቢው ምንጮቿ ሰምታለች።
ጥቃቱ የተፈፀመው ዛሬ ሰኞ ታኅሣሥ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. ከጠዋቱ 1 ሰዓት ከ 30 ደቂቃ አካባቢ እንደሆነ የገለፁት ምንጮች፣ በጥቃቱም በቁጥር ስምንት የሚደርሱ የቤተ ክርስቲያኒቷን የበቆሎ ምርት በመሰብሰብ ላይ የነበሩት አገልጋዮች ሕይወት ወዲያው ማለፉን ገልፀዋል።
ከእነርሱ በተጨማሪም፣ ቁጥራቸው በውል ባልታወቁ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን፣ የበቆሎው ምርት እና አብዛኛው የቤተ ክርስቲያኗ ንብረቶችም በድሮን ጥቃቱ ምክንያት መቃጠላቸውን ምንጮች አክለው ለዋዜማ ተናግረዋል።
ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በወረዳው ሥር ባሉ አብዛኞቹ ቀበሌዎች፣ ድሮኖች በተደጋጋሚ ቅኝት ሲያደርጉ እንደነበርም ዋዜማ ከምንጮቿ መገንዘብ ችላለች።