ግብፅ፣ ኢትዮጵያ የኅዳሴ ግድቡን የምትገነባው፣ አመነጫለኹ ካለችው የኤሌክትሪክ ኅይል ባለፈ በናይል ወንዝ ላይ የበላይነቷን ለማስፈን ነው ስትል ወቀሳዋን አሰማች።
ይኽን የተናገሩት የአገሪቷ የመስኖ እና ውኀ ሃብት ሚንስትር ሓኒ ሰዊላም፣ ባለፉት ዐሥራ ኹለት ዓመታት በነበሩት ድርድሮች፣ ግድቡ ያመነጫል የተባለውን የኤሌክትሪክ ኀይል ለማመንጨት ከሚያስፈልገው ውኀ በላይ የሚይዝ እጅግ ግዙፍ የውኀ ማጠራቀሚያ እንዳለው መጥቀሳቸውን የአገሪቷ ጋዜጦች አስነብበዋል።
“በድርድሮቹ ጊዜያት ኢትዮጵያ ከተከተለቻቸው ሂደቶች፣ ግድቡን አስመልክቶ ካላት አተያይ እና ከተጋነነው ውኀ ማከማቻ አኳያ ሌሎች ስውር አጀንዳዎች ይናጠቃሉ” ያሉት ሚንስትሩ፣ “ግድቡ የፖለቲካ ፋይዳ አለውና፣ ኢትዮጵያ የናይል ወንዝን እንድትቆጣጠር ግብፅ አትፈቅድም” ማለታቸውም ተዘግቧል።
ኢትዮጵያ ግብፅን ስለምትወቅስበት “የቅኝ-ግዛት ስምምነት” የተጠየቁት ሚንስትሩ፣ ኢትዮጵያ ይኽን ደጋግማ የምታነሳው ሉላዊ አተያዩን ለማሳት ነው ሲሉ ክሱን አስተባብለዋል። ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን በኅዳሴ ግድቡ ዙሪያ ባለፈው ሳምንት ያካሄዱት አራተኛው ዙር ድርድር፣ ያለውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል።