December 26, 2023 – Konjit Sitotaw
ለ24 ዓመታት በቀላል ምግቦች አቅርቦት ውስጥ ሰፋ ያለ የገበያ ድርሻ የነበረው እና ቴስቲስ እና ጆሊ ጁስ የተሰኙ ምርቶችን በማምረት የሚታወቀው ቴስቲ ፉድስ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር፣ በውጭ ምንዛሬ ዕጥረት የተነሳ ሥራ ማቆሙን ፎርቹን አስነብቧል።
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ በውጭ ምንዛሬ ችግር የተነሳ ወሳኝ የሆኑት የምርት ግብዓቶችን ከውጪ ማስገባት ባለመቻሉ ፋብሪካው ሥራ ለማቆም እንደተገደደ መናገራቸውን ዘገባው ጠቅሷል።
የድርጅቱ ሠራተኞችም ተጨማሪ ውሳኔ እስከሚያገኙ ድረስ የዕረፍት ፈቃድ እንደተሰጣቸውም ዘገባው አመልክቷል።
ድርጅቱ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በአስቸጋሪ ኹኔታ ውስጥ ማለፉን እና የምርት መጠኑም በከፍተኛ መጠን መቀነሱን የገለፀው ዘገባው፣ ከሦስት ዓመታት ወዲኽ የጆሊ ጁስ ምርቱ በአምስት እጥፍ፣ እንዲኹም የቴስቲስ ምርቱ በ10 ዕጥፍ መቀነሱን ጠቁሟል።
የምግብ፣ መጠጥ እና ትምባሆ ማኅበራት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ደረጄ ዋቅቶላ፣ የድርጅቱ ፈተናዎች እንደ አገር ያለውን የውጭ ምንዛሬ ችግር ያሳያል ማለታቸውንም ዘገባው ገልፇል።