የእስራኤል ሠራዊት አባላት
የምስሉ መግለጫ,የእስራኤል ሠራዊት አባላት

ከ 3 ሰአት በፊት

በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር በቀጠለው የእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ ባለፉት 24 ሰዓታት 241 ሰዎች መገደላቸውን አስታወቀ።

የፍልስጤም ፕሬዝዳንት መሐሙድ አባስ ጦርነቱን በሕዝባቸው ላይ እየተፈጸመ ያለ “ታላቅ ወንጀል” ብለውታል።

የእስራኤል ጦር መሪ ኸርዚ ሀልቪ በበኩላቸው ከሐማስ ጋር ያለው ጦርነት “ለበርካታ ወራት” ይቀጥላል ብለዋል።

እስራኤል በማዕከላዊ ጋዛ የምድር ኃይል ዘመቻዎቸን እያደረገች እየተገለጸ ባለበት ወቅት፤ ማክሰኞ ዕለት 100 አካባቢዎችን መደብደቧን አስታውቃለች።

ከባድ ፍንዳታዎች በጋዛ ሰርጥና በእስራኤል ድንበር አካባቢ እስከ ረቡዕ ጠዋት ድረስ ይሰማ ነበር።

የጋዛ ጤና ሚኒስቴር በ24 ሰዓታቱ ውስጥ 382 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋልም ብሏል።

እንደ ሚኒስቴሩ ከሆነ ከ11 ሳምንታት በላይ በዘለቀው ግጭት 20,915 ሰዎች ተገድለዋል።

በሁለቱ ተዋጊ ወገኖች መካከል የሚቀርቡ መረጃዎች በገለልተኛ አካል አልተረጋገጡም።

የእስራኤል-ሐማስ ጦርነት መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ላይ የሐማስን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ መጀመሩ ይታወሳል። ሐማስ በጥቃቱ ወደ እስራኤል ድንበር ተሻግሮ 1ሺህ 200 የሚሆኑ በአብዛኛው ሰላማዊ የሆኑ ሰዎችን ገድለዋል።

240 የሚሆኑ ሰዎችም ታግተው ወደ ጋዛ የተወሰዱ ሲሆን፤ በኋላ ላይ በርካቶች ተለቀዋል።

ፕሬዝዳንት አባስ በጋዛ ሰርጥ እየተደረገ ያለውን ጦርነት “ከቅስፈት በላይ” እና “ለማጥፋት ከሚደረግ ጦርነት በላይ” ሲሉ ገልጸውታል።

ጦርነቱ በፍልስጤም ሕዝቦች ታሪክ ተደርጎ የማያውቅ ነው ሲሉም ፕሬዝዳንቱ አክለዋል።

ከጦርነቱ መጀመር በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በራማላህ ከተማ ከግብጽ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ ፕሬዝዳንቱ ግዛቱን ለመለየት አዳጋች ሆኗል ብለዋል። በተወረረው ዌስት ባንክም በየትኛውም ጊዜ ግጭት ሊፈነዳ ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የፍልስጤሙ መሪ የተኩስ አቁም እንዲደረግ የሚያዘውን የመንግሥታቱ ድርጅት የውሳኔ ሃሳብን ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቷን በመጠቀሟ ዋሽንግተንን ከሰዋል።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል አለቃ ሌተናል ጀኔራል ሀልቪ በሰጡት መግለጫ “የእስራኤል ስኬት ለረጅም ጊዜ ጸንቶ እንዲቆይ” ጦርነቱ “ለበርካታ ወራት ይቀጥላል” ብለዋል።

የጋዛ መልከዓ ምድር አስጨናቂ መሆኑን ያመኑት ጀኔራሉ፤ ምንም ያህል ጊዜ ቢወስድም የሐማስን መሪዎች በቁጥጥር ስር ለማዋል አሊያም ለመደምሰስ ቃል ገብተዋል። በሰሜናዊ ጋዛ የእስራኤል ጦር የሐማስን ሻለቃ ጦር ለመደምሰስ ተቃርቧል ሲሉም አክለዋል።

የእስራኤልና አረብ መገናኛ ብዙሐን ግብጽ የተኩስ አቁም እቅድ ማቅረቧን ዘግበዋል።

እንደ ዘገባዎቹ ከሆነ እቅዱ የእስራኤል ታጋቾችና በአገሪቱ የተያዙ የፍልስጤም እሰረኞች በምዕራፍ በመለቀቅ ጀምሮ የእስራኤልን ጥቃት የሚያቋርጥ ነው።

በኳታር አደራዳሪነት ከዚህ ቀደም የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ከጋዛ የተያዙ በርካታ ታጋቾች በፍልስጤም እስረኞች ልውውጥ ተደርጓል።

እስካሁን ድረስ እስራኤልና ሐማስ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ የሚቀርቡ ጥሪዎችን አልተቀበሉም።