ዛሬ ንጋት በያቤሎ አጠቃላይ ሆስፒታል ተጣብቀው የተወለዱት ሕጻናት
የምስሉ መግለጫ,ዛሬ ንጋት በያቤሎ አጠቃላይ ሆስፒታል ተጣብቀው የተወለዱት ሕጻናት

ከ 2 ሰአት በፊት

በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ያቤሎ አጠቃላይ ሆስፒታል መንትዮች ደረታቸው አካባቢ ተጣብቀው ተወለዱ።

መንትዮቹ የተወለዱት ዛሬ ታኅሣሥ 17/2016 ዓ.ም. ንጋት 11 ሰዓት ላይ መሆኑን የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ አሬሮ ቢቂቻ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዞኑ የዋጪሌ ወረዳ ነዋሪ የሆነችው የጨቅላዎቹ እናት በዚሁ ሆስፒታል የቅድመ ወሊድ ክትትል ስታደርግ መቆየቷን የገለጹት አቶ አሬሮ፤ በአሁኑ ወቅት ሕጻናቱም ሆኑ እናት በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

“ተጣብቀው የተወለዱት ሁለቱም ወንዶች ናቸው። ደረታቸው አካባቢ ነው ተጣብቀው የተወለዱት። አሁን በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ።“

ይህች እናት በቅድመ ወሊድ ክትትል ወቅት በሆዷ የያዘችው ጽንስ መንትያ እንደሆነ አልታወቀም ነበር ይላሉ አቶ አሬሮ።

“በደረታቸው ተጣብቀው ስለነበረ በክትትል ወቅት ለማወቅ ሊከብድ ይችላል። ስለተጣበቁ አንድ ልጅ ሊመስል ይችላል” ብለዋል።

ጨቅላዎቹ ገና ዛሬ ንጋት እንደመወለዳቸው በቆዳቸው ብቻ የተጣበቁ እንደሆነ አልያም ደግሞ የሚጋሩት ሌላ የሰውነት ክፍል ስለመኖሩ እስካሁን ግልጽ አለመሆኑን አቶ አሬሮ ጨምረው ተናግረዋል።

ሥራ አስኪያጁ ሕጻናቱን በቀዶ ጥገና የመለየት ስራው ውስብስብ የማይሆን ከሆነ ቀዶ ጥገናውን በሆስፒታላቸው ለማድረግ ዕድቅ መኖሩን ጨምረው ተናግረዋል።

“የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች አሉን። የሕጻናት ሐኪሞች አሉን። ሊደረግ ስለሚችለው ሕክምና እነርሱ ናቸው የሚወስኑት። የማይቻል ከሆነ ወደሚቻልበት ቦታ ሪፈር እናደርጋቸዋለን” በማለት ስለ ቀጣዩ እርምጃ ተናግረዋል።

ሕጻናቱ በአሁኑ ወቅት በሕጻናት ማቆያ ክፍል ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን እንዲሁም ያለ መተንፈሻ ስርዓት ድጋፍ በራሳቸው እየተነፈሱ እና ጡት እየጠቡ እንደሆነ ገልጸዋል።