
ከ 4 ሰአት በፊት
በአሜሪካዋ ፍሎሪዳ ግዛት ከገና በዓል ስጦታ ጋር በተያያዘ በአንድ የቤተሰብ አባላት መካከል በተፈጠረ ጭቅጭቅ እህት በታናሽ ወንድሟ በጥይት ተገደለች።
ፖሊስ እንዳለው የተሻለ የገና ስጦታ ማግኘት ያለበት ማን ነው በሚል በተፈጠረ ጭቅጭቅ በአስራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ያለ ታዳጊ የ23 ዓመት እህቱን ደረቷን በጥይት መትቶ ገድሏል።
በመቀጠል ይህ ታዳጊ በአንድ ዓመት በሚበልጠው ሌላኛው ወንድሙ በጥይት ተመትቷል።
የአካባቢው ፖሊስ እንዳለው የ15 ዓመት እድሜ ያለው ታዳጊ የራሱን ሽጉጥ ይዞ በመምጣት እህታቸውን የገደለውን ታናሽ ወንድሙን በጥይት መትቷል።
እህቱን የገደለው የ14 ዓመት ታዳጊ መሆኑን የፖሊስ ሪፖርት ያስረዳል።
ፖሊስ የ23 ዓመቷ ወጣት በጥይት ስትመታ በደረቷ ጨቅላ ልጇን አቅፋ ይዛ ነበር ብሏል።
የፖሊስ አዛዥ ቦብ ጉአልቴይር ለጋዜጠኞች ሲናገሩ የ15 ዓመቱ ታዳጊ ወንድሙን በጥይት ከመታ በኋላ መሳሪያውን ጥሎ ለመሸሽ ቢሞክርም በቁጥጥር ስር ውሏል ብለዋል።
- በጥቅምት ወር በታሪካዊቷ የላሊበላ ከተማ የተከሰተው ምንድን ነው?ከ 6 ሰአት በፊት
- ፈረስ ለጭነት መጠቀም 60 ሺህ ብር የሚያስቀጣባት የኦሮሚያ ከተማከ 6 ሰአት በፊት
- ትራምፕን ከፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ያገዱት ዳኞች የግድያ ዛቻ እየደረሳቸው መሆኑ ተገለጸከ 5 ሰአት በፊት
አክለውም የ14 ዓመቱ ታዳጊ ወደ ሆስፒታል ተወስዶ የሕክምና ድጋፍ ካገኘ በኋላ የደረሰበት ጉዳት ለሕይወቱ አስጊ አለመሆኑ ታውቋል ብለዋል የፖሊስ መኮንኑ።
እነዚህ የ14 እና የ15 ዓመት ታዳጊዎች በዘፈቀደ የጦር መሳርያ ሲይዙ የሚከሰተው ይህ ነው ይላሉ የፖሊስ አዛዡ።
“ይበሳጫሉ፤ ነገሮችን እንዴት ማስተናገድ እንዳለባቸው አያውቁም፤ ከዚያ እርስ በእርስ ይታኮሳሉ” ይላሉ የተፈጠረውን ሁኔታ ሲያስረዱ።
የሁለት ልጆች እናት የነበረችው የ23 ዓመቷ ሴት ሰውነቷ ውስጥ ደም መፍሰስ አጋጥሟት መተንፈስ ሳትችል በመቅረቷ ሕይወቷ አልፏል።
ይሁን እንጂ ደረቷን በጥይት ስትመታ በደረቷ ይዛው የነበረው ጨቅላ ልጇ ምንም አይነት ጉዳት አልደረሰበትም ብለዋል የፖሊስ ኃላፊው በመግለጫቸው።
እህቱን በመግደል የተጠረጠረው የ14 ዓመቱ ታዳጊ ከሆስፒታል ቆይታው በኋላ እንደ አዋቂ ክስ ይመሰረትበት እንደሆነ ዐቃቤ ሕግ ውሳኔ ያስተላልፋል ተብሏል።
የ15 ዓመቱ ታዳጊ ደግሞ በግድያ ሙከራ እና ማሰረጃ በመደበቅ ክስ ተመስርቶበታል።