መቀለ ከተማ

ከ 1 ሰአት በፊት

ከሦስት ሳምንት ገደማ በፊት በአዲስ አበባ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ ጠርተው የነበሩት ፖለቲከኞች፤ በመጪው እሁድ በትግራይ መዲና መቀለ ከተማ ተመሳሳይ ሰልፍ እንዳርጋለን ሲሉ ለቢቢሲ ገለጹ።

አስተባባሪዎቹ ሰልፉን እንደሚያደርጉ ለመቀለ ከተማ አስተዳደር ማስታወቃቸውን ሲገልጹ የከተማ አስተዳደሩ በበኩሉ “በከተማዋ የሚደረግ ሰልፍ የለም” ብሏል።

በመጪው እሁድ ታህሳስ 21፤ 2026 ዓ.ም. በትግራይ ክልል መዲና መቀለ ከተማ ሊደረግ የታቀደውን ሰላማዊ ሰልፍ እያስተባበሩት ያሉት በአዲስ አበባ ከተማ ኅዳር 30/2016 ዓ.ም. ሊደረግ ታቅዶ የነበረው ሰልፍ የጠሩት ከአስር በላይ ፖለቲከኞች ናቸው።

እነዚህ ፖለቲከኞች መካከል የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) እንዲሁም ባለፈው ሳምንት የፖለቲካ ፓርቲነት ማረጋገጫ ያገኘው የትንሳኤ ሰብዓ እንደርታ ፓርቲ አመራሮች ይገኙበታል።

የቀድሞው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አባል የነበሩት አቶ የሺዋስ አሰፋ እና አቶ ናትናኤል መኮንንን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት በግል የሚንቀሳቀሱ ፖለቲከኞችም የሰልፍ አስተባበሪ ኮሚቴው አባል ናቸው።

በአዲስ አበባ የተጠራው ሰልፍ ሲቃረብ ከእነዚህ ፖለቲከኞች ውስጥ አራቱ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ውለዋል። አስተባባሪዎቹም “በመንግሥት ጫና” ምክንያት ሰልፉን ለማራዘም መገደዳቸውን ማስታወቃቸው ይታወሳል።

ይሁንና ኮሚቴው ተመሳሳይ ይዘት ያለው ሰላማዊ ሰልፍ በመቀለ ከተማ ለማካሄድ “ከማዕከሉ [ኮሚቴ] ጋር የሚናበብ ቡድን” በትግራይ ክልል ማቋቋሙን የኮሚቴው አባል የሆኑት የኢሕአፓ ሊቀመንበር ረዳት ፕሮፌሰር ዝናቡ አበራ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከመቀለ ውጪም ሰባት በሚሆኑ ሌሎች ከተሞችም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ለቢቢሲ የሚናገሩት ሌላኛው የሰልፉ አስተባባሪ አቶ ይስሃቅ ወልዳይ፤ የመቀለ ከተማው ዝግጅት ቀድሞ መጠናቀቁን አስረድተዋል።

በመቀለ ከተማ የሚገኘው ንዑስ ኮሚቴም ታህሳስ 5/2016 ዓ.ም. በከተማዋ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚያደርግ ለመቀለ ከተማ ካንቲባ ጽህፈት ቤት በደብዳቤ ማስታወቁንም አቶ ይስሃቅ ገልጸዋል።

ቢቢሲ የተመለከተው ይህ የአስተባባሪዎቹ ደብዳቤ ሰልፉ የሚካሄደው ሦስት ጥያቄዎች ለማንሳት እንደሆነ ያስረዳል።

በደብዳቤው ላይ በቅድሚያ የተቀመጠው ጥያቄ “በመላው ኢትዮጵያ በማንነታቸው ምክንያት የታሰሩ የትግራይ እና የሌሎች ብሔር ተወላጆች ይፈቱ” የሚል ነው። የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደ ቅዬያቸው የመመለሳቸው ጉዳይ ከሰልፉ ዓላማዎች መካከል ተጠቅሷል።

በሰልፉ ላይ ይነሳል የተባለው ሌላኛው ጥያቄ ጦርነት እንዲቆም የሚጠይቅ ነው።

የሦስት የሰልፍ አስተባባሪዎች ፊርማ ባረፈበት በዚህ ደብዳቤ ላይ “ሁሉም ሀገራዊ እና ክልላዊ የፖለቲካ ልዩነቶች እና ችግሮች በፖለቲካዊ ዉይይት ይፈቱ” የሚል ሀሳብ ተቀምጧል።

መነሻውን እና ማጠናቀቂያውን በሮማናት አደባባይ ያደረገው ይህ ሰልፍ “100 ሺህ ገደማ የሚገመቱ” ነዋሪዎች ይሳተፉበታል ተብሎ እንደሚጠበቅም በዚሁ ደብዳቤ ላይ ሰፍሯል።

በዚህ ደብዳቤ ላይ ስማቸው ከሰፈሩት አስተባባሪዎች አንዱ የሆኑት አቶ አማኑኤል ሐዱሽ፤ “[ሰልፉ እንደሚደረግ] ለመቀለ ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት አሳውቀናል። አዎንታዊ ምላሽ ነው የተሰጠን። ያንን አዎንታዊ ምላሽ ይዘን የራሳችንን አንዳንድ ዝግጅቶች እያደረግን እንገኛለም” ሲሉ የከተማ አስተዳደሩ ደብዳቤውን መቀበሉን ገልጸዋል።

ሌላኛው የሰልፉ አስተባባሪ አቶ ይስሃቅ ወልዳይ፤ “ምላሽ የተሰጠው እኛ ያስገባነው ደብዳቤ [ግርጌ] ላይ ነው። ፊርማ እና ጽሁፉ ደብዳቤው ላይ ነው የተሰጠው” ሲሉ ከከተማዋ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ምላሽ የተሰጠበትን መንገድ አስረድተዋል።

ቢቢሲ በተመለከተው ደብዳቤ ግርጌ ላይ “ከጸጥታ አካላት ጋር በመግባባት፤ በተጠቀሰው ቦታ እና ጊዜ የተያዘውን ፕሮግራም በማረጋገጥ፤ ጥያቄውን መቀበላችንን እናስታውቃለን” የሚል ጽሁፍ እና ፊርማ ሰፍሯል።

ይሁንና ቢቢሲ ይህ ምላሽ ከጽህፈት ቤት ስለመሰጠቱ ማረጋገጥ አልቻለም።

ስለጉዳዩ ከቢቢሲ ጥያቄ የቀረበላቸው የመቀለ ከተማ ከንቲባ አቶ ይትባረክ አምሃ፤ በአሁኑ ጊዜ ከተማዋ ውስጥ አለመሆናቸውን በመግለጽ መልስ መስጠት እንዳማይችሉ ተናግረዋል።

ቢቢሲ ከመቀለ ከተማ ሰላም እና ጸጥታ ጽህፈት ቤት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ሙከራም አልተሳካም።

ፖለቲከኞቹ 100ሺህ ነዋሪዎች ይሳተፉበታል የሚሉት ሰልፍ መነሻው እና ማጠናቀቂያ ሮማናት አደባባይ ይሆናል ብለዋል
የምስሉ መግለጫ,ፖለቲከኞቹ 100ሺህ ነዋሪዎች ይሳተፉበታል የሚሉት ሰልፍ መነሻው እና ማጠናቀቂያ ሮማናት አደባባይ ይሆናል ብለዋል

የመቀለ ከተማ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ግን በማህበራዊ ትስስር ገጹ በዕለቱ የሚካሄድ ሰልፍ እንደማይኖር አስታውቋል።

ቢሮው ከሁለት ቀናት በፊት በገጹ በለጠፈው ደብዳቤ “በመቀለ ከተማ የሚካሄድ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሌለ እያመለከትን፤ በዚህ መሠረት የጸጥታ አካላት ጥብቅ ክትትል እንዲያደርጉ እናስታውቃለን” ሲል ሰልፉ በከተማ አስተዳደሩ እውቅና እንደሌለው ገልጿል።

የሰልፉ አስተባባሪዎች አቶ ይስሃቅ እና አቶ አማኑኤል ይህንን ደብዳቤ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ መመልከታቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል። ይሁንና ደብዳቤው የተጻፈው በክልሉ ለሚንቀሳቀሱ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት መሆኑን በመጥቀስ “ለእኛ የደረሰን ደብዳቤ የለም” ብለዋል።

አቶ አማኑኤል፤ “ከማን እንደሆነ [ባላውቅም] የተጻፈ ደብዳቤ አይቻለሁ። ግን [ሰልፉ እንዲደረግ] የጠየቅነው እኛ ነን፤ መልስ መሰጠት ያለበትም ለእኛ ነው። በሕገ-መንግሥቱ መሠረት [ሰልፉን] መከልከል የተፈቀደ ባይሆንም፤ ‘ከልክለናል’ የሚሉ ከሆነም በጽሁፍ ጥያቄ ላቀረብነው መቀለ ውስጥ የምንገኝ አስተባባሪዎች በጽሁፍ መልስ መስጠት ይገባ ነበር” ብለዋል።

አስተባባሪዎቹ እሁድ ዕለት ሰልፉን ለማድረግ የሚያስፈልጋቸውን ዝግጅት መቀጠላቸውን አክለዋል።

የትግራይ ክልልን የሚመራው ጊዜያዊ አስተዳደር ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ከተቋቋመ ወዲህ ፖለቲከኞች በመቀለ ከተማ ውስጥ የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ ሲያደርጉ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

ከአራት ወራት በፊት ጳጉሜን 2፤ 2015 ዓ.ም. በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሶስት የፖለቲካ ፓርቲዎች በከተማዋ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ከጀመሩ በኋላ በጸጥታ ኃይሎ እንዲበተኑ መደረጋቸው ይታወሳል።

“የአስተዳደር አቅም ማነስ አለ” እንዲሁም “የትግራይ ሕዝብ ስቃይ አላበቃም” በሚል በተጠራው ሰልፍ ላይ የተገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና ተሳታፊዎች ለእስር ተዳርገው ነበር።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በከተማው የተጠራውን ይህንን ሰልፍ የተቃወመው የተቃውሞ ስልፍ የማድረጊያ “ትክክለኛው ጊዜ አይደለም” በሚል ነበር።