December 27, 2023 – Konjit Sitotaw 

ብልጽግና በአዲስ አበባ መርካቶና አካባቢው ከፍተኛ የጅምላ አፈሳ እያካሄደ መሆኑን የማዋከቡ ሰለባዎች ተናገሩ።

የአገዛዙ ብረት ለበስ ፖሊሶች ሰሞኑን በመርካቶ፤ ተክለሃይማኖት፤ አሜሪካን ግቢ፤ ጎጃም በረንዳና አካባቢው ባሉ ሰፈሮች ከፍተኛ የሆነ የጅምላ አፈሳ እያካሄዱ መሆኑን በአገዛዙ ታጣቂዎች መዋከብ የደረሰባቸው የከተማ ነዋሪዎች ለሮሃ አረጋግጠዋል፡፡
በተለይም የንግዱ ማህበረሰብ አካላት የሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በእነዚህ የንግድ እንቅስቃሴ በሚበረታባቸው ሰፈሮች በድንገት ከበባ የሚፈጽሙ የብልጽግና የጸጥታ ሃይሎች እስካሁን ለምን እንደሆነ ግልጽ ባልተደረገ ምክንያት የጅምላ አፈሳ እያደረጉ ሰዎችን ወደ እስር እየወሰዱ መሆኑን ለማወቅ ችለናል፡፡

አንድ መርካቶ ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራ ወጣት ለሮሃ በሰጠው ቃል ‹‹ድንገት የሰፈሮቹን መውጫና መግቢያ መንገዶች ይዘጋሉ፤ ከዚያ እዚያ አካባቢ እንቅስቃሴ የሚያደርግን ሰው ሁሉ አፍሰው ጭነው ይወስዳሉ›› ብሏል፡፡

‹‹ባለፈው ሀሙስ በድንገት ፖሊሶች መጥተው እኔና አጠገቤ የነበሩትን ነጋዴዎች ወሰዱን›› የሚለው አስተያየት ሰጪው ‹‹ከዚያ በኋላ ንግድ ፈቃድ አድሰሃል ወይ፡ ቲን ነምበር አለህ ወይ እያሉ አዋከቡኝ፤ አለኝ ላሳያችሁ ብልም ቀኑን ሙሉ አሰሩኝ›› ሲል አብራርቷል፡፡
ይህ እስርና ማዋከብ ሁሉ ነገሩ ከእጁ የወጣበት ብልጽግና በአዲስ አበባው ነዋሪ ላይ እየወሰደው ያለው የመጨረሻ የማስፈራሪያ እርምጃ መሆኑን የሚገልጹት የጥቃቱ ሰለባዎች የመንግስትነት አቅሙ የተገፈፈው ብልጽግና በንግዱ ማህበረሰብ ዘንድ ቅቡልነት ለማግኘት ሲል የተጠቀመው ስልት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

‹‹ነጋዴው ለቢዝነሱ እንደሚጨነቅ ስለሚያውቁ ብልጽግናን በግልጽ ከተቃወመ አስከፊ ነገር እንደሚደርስበት ለማስፈራራት የሚጠቀሙት ዘዴ ነው›› ብለዋል አንድ አስተያየት ሰጪ ለሮሃ በሰጡት ቃል፡፡
ብልጽግና ከአዲስ አበቤው ልብ ውስጥ ከወጣ ዓመታት ቢቆጠሩም ግማሹን በእስርና በማዋከብ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያለውን ደግሞ በጥቅም ለመደለል በመሞከር ዕድሜውን ለማራዘም እየጣረ ይገኛል፡፡
ምክንያቱም አዲስ አበባ ላይ የሚነሳ ህዝባዊ ተቃውሞ መጨረሻውን እንደሚያፈጥንበት ተገንዝቧል፡፡