EthiopianReporter.com 

ሳሙኤል ቦጋለ

December 27, 2023

የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ድርድርንና ቀጣናዊ የንግድ ትስስሮችን በበላይነት የሚመራ ብሔራዊ ኮሚቴ

የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ የሙከራ ንግድ ማስጀመሪያ የሚሆኑ ምርቶችንና አገሮችን መረጣ፣ ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር በመምከር ይከናወናል ተባለ፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣናን ለመቀላቀል የዕቃዎች ንግድ ታሪፏን (Tariff Offer) በኅዳር ወር በማስገባት ያከናወነች መሆኗን፣ የአፍሪካ የንግድ ሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያን ታሪፍ ከሁለት ሳምንታት በፊት እንዳፀደቀው፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ አቶ ገብረ መስቀል ጫላ ማክሰኞ ታኅሳስ 16 ቀን በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

ቀጣይ ሒደቱም የሙከራ ንግድ ትግበራን ማካሄድ ሲሆን፣ ለሙከራ የሚሆኑት ዕቃዎችንና ከኢትዮጵያ ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት (Bilateral Agreement) ግንኙነት ካላቸው አገሮች መካከል የመምረጥ ሥራውን፣ ከግሉ የንግድ ማኅበረሰብ ጋር በመሆን ‹‹በአጭር ጊዜ›› እንደሚከናወን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

‹‹የሚቀረን ነገር ቢኖር የተወሰኑት አገሮች የጀመሩትን የሙከራ ትግበራ በሁለትዮሽ ውይይት ለማስጀመር ውይይት ማድረግ ነው፤›› ሲሉ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በመጀመሪያ ከግሉ ዘርፍ ጋር ግንኙነት በማድረግ ምርቶችን መምረጥ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

ምርቶችን በመምረጥ በይበልጥ የሚፈለግ ምርት በአንድ አገር ካለ ስምምነት በመፍጠር በሙከራ ደረጃ የሚጀመር መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹በሁለትዮሽ ስምምነት አብረውን የሚሠሩ አገሮች ስላሉን እነሱን ታሳቢ ያደረገ የሙከራ ትግበራ ነው፤›› በማለት የግሉን ዘርፍ በማማከር እንደሚካሄድ አብራርተዋል፡፡ ‹‹ትግበራውም ጥቂት የዝግጅት ጊዜ የሚፈልግ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በአፍሪካ የነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት መሠረት በታሪፍ መዝገብ (Tarrif Book) ከሚጠቀሱት 6,475 ምርቶች ውስጥ 90 በመቶ (5,828 ምርቶች)፣ በአሥር ዓመታት (ሦስት ዓመታት ስላለፉ በቀሪዎች ሰባት ዓመታት) ታሪፋቸው ዜሮ ይሆናል፡፡

ኢትዮጵያም ሦስት ዓመታት አሳልፋ ያስገባቸውን ታሪፍን ‹‹ክርክር ሳይገጥመን ነው በሙሉ ድምፅ ያፀደቅነው፤›› ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡ የአፍሪካ የንግድ ሚኒስትሮች ምክር ቤት እ.ኤ.አ. ከታኅሳስ 6 እስከ 7 ቀን 2023 ባካሄደው ስብሰባ ነው የኢትዮጵያን 90 በመቶ ታሪፍ ያፀደቀው፡፡

በተጨማሪም ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል ለረዥም ዓመታት ስትሠራ የቆች መሆኗን፣ ዋና የንግድ ተደራዳሪውና ሚኒስትሩ አቶ ገብረ መስቀል ገልጸው፣ በቀጣይ ሦስት ዓመታት ሒደቱን በማጠናቀቅ እ.ኤ.አ. በ2026 ዓ.ም. ኢትዮጵያን ለመቀላቀል በጥንካሬ እየተሠራ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተዋቀረ የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነትንና ቀጣናዊ ትስስር ድርድሮችን በበላይነት የሚመራ ኮሚቴም በዕለቱ በስካይ ላይትሆቴል ምክክር አድርጎ ነበር፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ደኤታው ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣ የጉምሩክ ኮሚሽነሩ አቶ ደበሌ ቃበታ፣ የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ፈቃዱ ደግፌ፣ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በየነ ጴጥሮስ (ፕረፌሰር)፣ የንግድ ሚኒስትሩ አቶ ገብረ መስቀል ጫላ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ ምሥጋኑ አርጋ (አምባሳደር)፣ እንዲሁም የኢንስትመንት ኮሚሽንን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት ኃላፊዎች  የተገኙበት ኮሚቴ ነው በኢትዮጵያ የንግድ ድርድሮች ላይ የመከሩት፡፡