EthiopianReporter.com 

ሰላማዊት መንገሻ

December 27, 2023

ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት (FDI) ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መሆኑን፣ በዓለም ላይ ካሉ ትልልቅ ፕሮፌሽናል አገልግሎቶች ኔትወርክ አንዱ የሆነው የኧርነስት ኤንድ ያንግ አፍሪካ ሪፖርት አስታወቀ፡፡

‹ኧርነስት ኤንድ ያንግ አፍሪካ አትራክቲቭ› እስከ 2014 ዓ.ም. ድረስ በአፍሪካ አገሮች የነበረውን የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በተመለከተ ሰኞ ታኅሳስ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ሪፖርት እንዳስታወቀው፣ ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ዓመታት በአማካይ ከሦስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ስታገኝ የነበረው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ወደ 600 ሚሊዮን ዶላር ዝቅ ሲል፣ ለ600 ዜጎች ብቻ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡

በአንፃሩ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የ2014 ዓ.ም. ሪፖርት እንደሚያሳየው ከ163 የአምራች፣ የግብርናና የአገልግሎት ዘርፍ ፕሮጀክቶች ሦስት ቢሊዮን ዶላር መሳብ ተችሏል፡፡

የውጭ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች መዋዕለ ንዋያቸውን የማፍሰስ ፍላጎታቸው ዝቅ ማለቱን የጠቀሰው የኧርነስት ኤንድ ያንግ ሪፖርት፣ ኡጋንዳና ኬንያ ከፍተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት እያስመዘገቡ ነው ብሏል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በጥር 2012 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርት፣ በምሥራቅ አፍሪካ የውጭ ቀጥተኛ መዋዕለ ንዋይ ፍሰትን በመሳብ፣ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ የምትገኝ አገር መሆኗን መጥቀሱ ይታወሳል፡፡

በኢትዮጵያ በ2012 ዓ.ም. 2.5 ቢሊዮን ዶላር ያስመዘገቡ 34 የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች እንደነበሩ፣ በ2014 ዓ.ም. ስድስት ፕሮጀክቶች ብቻ መሳብ እንደተቻለ የኧርነስት ኤንድ ያንግ ሪፖርት ገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች መቀነስ ዋነኛ ምክንያቶች፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የዩክሬንና የሩሲያ ጦርነት፣ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትና የውስጥ የፀጥታ ሥጋቶችን ጨምሮ የተለያዩ ምክንያቶች ለውጭ ኢንቨስትመንት መቀነስ አስተዋጽኦ አድርገዋል ሲል ሪፖርቱ አስታውቋል።

አሜሪካ ከሰጠችው የቀረጥ ነፃ ዕድል (AGOA) ኢትዮጵያ መውጣቷ፣ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የዕዳ መጨመር ሌሎች ምክንያቶች ናቸው ብሏል።

በተጨማሪም የአፍሪካ አገሮች በአሥር ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ መግባታቸው በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

ናይጄሪያ፣ ጋና፣ ኬንያ፣ ዛምቢያ፣ ሞዛምቢክ፣ ኢትዮጵያና ኬንያ ከጥቅል  አገራዊ ምርታቸው በአማካይ 77 በመቶ የሚሆነው የውጭ ዕዳ እንደሆነ ሪፖርቱ ገልጿል፡፡

ይህም እየጨመረ ካለው የዋጋ ግሽበት ጋር ተዳምሮ መዋዕለ ንዋይን በአገሮቹ ላይ ማፍሰስ ለሚመጡ ባለሀብቶች ሥጋት መፍጠሩ በሪፖርቱ ተካቷል፡፡

ከኮቪድ ወረርሽኝ እያገገመ ያለው የአፍሪካ ኢኮኖሚ በማዝገም ለውጥ ላይ መሆኑ ለኢንቨስተሮቹ ፈተና መሆኑ በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያ በተለይም በቴሌኮም ዘርፍ ትኩረት በመስጠት ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ፣ የማበረታቻ ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደምትገኝ ሪፖርቱ ገልጿል፡፡

በአጠቃላይ የአፍሪካ አገሮችን በተመለከተ ይፋ በተደረገው ሪፖርት አሥር በከፍተኛ ደረጃ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መዋዕለ ንዋይ ፍሰት ፕሮጀክቶችን ከተቀበሉ አገሮች ውስጥ ግብፅ 107 ቢሊዮን ዶላር ያስመዘገቡ 149 ፕሮጀክቶ በመሳብ፣ እንዲሁም ለ61 ሺሕ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር የመጀመሪያ ደረጃ ይዛለች ብሏል፡፡

ደቡብ አፍሪካ 27 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ 157 ፕሮጀክቶች በመሳብ ለ15,500 ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠች ሲሆን፣ በሦስተኛ ደረጃ የተቀመጠችው ሞሮኮ 21 ቢሊዮን ዶላር 71 ፕሮጀክቶን በመሳብ ለ21 ሺሕ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥራለች ብሏል፡፡

ኡጋንዳ በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ዕድገት ማሳየቷን የገለጸው ሪፖርቱ፣ እ.ኤ.አ. በ2022 ብቻ ከ10.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማስመዝገቧንና ይህም ከምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ከፍተኛው መሆኑን አስታውቋል፡፡

ኡጋንዳ በዚህ የኢንቨስትመንት ዕድገት ከ6,300 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደቻለች ገልጿል።

የፈረንሣይ ቶታል ኢነርጂና የቻይና ናሽናል ኦፍሾር ኦይል ኮርፖሬሽን (CNOOC) ከኡጋንዳና ከታንዛኒያ ጋር ድፍድፍ ነዳጅ ለማልማት፣ የአሥር ቢሊዮን ዶላር ስምምነት በማድረጋቸው ኡጋንዳን ቀዳሚ ተጠቃሚ አድርጓታል ሲል ሪፖርቱ ያብራራል።

በተመሳሳይ ኬንያ ከፍተኛ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗን የገለጸው ሪፖርቱ፣ በ63 ፕሮጀክቶች ሁለት ቢሊዮን ዶላር ያህል የካፒታል ኢንቨስትመንት ከሰባት ሺሕ በላይ የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላት ተጠቅሷል።

አሜሪካ በኬንያ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት በማድረግ ከ700 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው 14 ፕሮጀክቶች መጀመሯ ተገልጿል።

በተለይም ከአሜሪካ የተገኘ የመድኃኒት ፕሮጀክት ትልቁን የካፒታል ፍሰት ማድረጉ ተገልጿል።

በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ አገሮች በ2014 ዓ.ም. በአጠቃላይ ከ114 ፕሮጀክቶች 14.5 ቢሊዮን ዶላር የካፒታል ኢንቨስትመንት በመሳብ፣ 22 ሺሕ ያህል ሥራዎችን መፍጠር እንደተቻለ በሪፖርቱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በኧርነስት ኤንድ ያንግ አፍሪካ ሪፖርት ላይ ያለውን አስተያየት ለማካተት ጥረት ቢደረግም ምላሽ ማግኘት አልተቻለም፡፡