

ዜና በደኅንነት ሥጋት ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የቀይ ባህርና የኤደን ባሕረ ሰላጤ የመርከብ ጉዞ…
በደኅንነት ሥጋት ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የቀይ ባህርና የኤደን ባሕረ ሰላጤ የመርከብ ጉዞ ሊጀመር ነው
ቀን: December 27, 2023
የሁቲ አማፅያን በሚሰነዝሩት የድሮንና የተወንጫፊ የጦር መሣሪያዎች ሥጋት ምክንያት አቋርጦት የነበረውን የቀይ ባህርና የኤደን ባህረ ሰላጤ የጉዞ መስመርን ዳግም ሊጀምር መሆኑን ግዙፉ የዴንማርክ የመርከብ ጭነት ማጓጓዣ ድርጅት መርስክ አስታወቀ።
ቢቢሲ ትናንት ማምሻውን እንደዘገበው፣ መርስክን ጨምሮ በርካታ የመርከብ ጭነት አጓጓዥ ድርጅቶች፣ የሁቲ አማጽያን በቀይ ባህር ዕቃ ጫኝ መርከቦችን ዒላማ ማድረጋቸውን ተከትሎ የጉዞ መስመር መጠቀም አቁመው ነበር።
‹‹መርስክ በቀይ ባህርና ኤደን ባህረ ሰላጤ በኩል ጉዞ ለመጀመር ዝግጅት ላይ ነኝ፤›› ያለው በቀጣናው የሁቲ አማጽያን የሚያደርሱትን ጥቃት ለመመልከት ዓለም አቀፍ ወታደራዊ ዘመቻዎች መጀመራቸውን ተከትሎ እንደሆነ ዘገባው ያስረዳል።
ሃፓግሎይድ የተባለ የጀርመን የመርከብ ጭነት ማጓጓዣ ድርጅትም የጉዞ መስመሩን ዳግም ስለመጠቀም ውሳኔ አስተላልፋለሁ ማለቱም ተጠቅሷል።
ሰፊ የየመን ግዛትን ተቆጣጥረው የሚገኙት የሁቲ አማጽያን ከእስራኤልና ከሐማስ ጦርነት መቀስቀስ ወዲህ፣ በቀይ ባህር በኩል በሚያልፉ ግዙፍ የጭነት መርከቦች ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ መቆየታቸው ይታወቃል።