EthiopianReporter.com 


ማኅበራዊ
ሚድሮክ ኢትዮጵያ የባህር ዳር ስታዲየም ሁለተኛ ዙር ግንባታን በተያዘለት ጊዜ ማጠናቀቅ አልቻለም

አበበ ፍቅር

ቀን: December 27, 2023

ሚድሮክ ኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን የባህር ዳር ስታዲየም ሁለተኛ ዙር ግንባታ እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ሠርቶ ለማስረከብ የተፈራረመ ቢሆንም በውጭ ምንዛሪ እጥረትና በክልሉ ባለው አለመረጋጋት ምክንያት አለመጠናቀቁን የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

በውለታው መሠረት ጥቅምት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ይጠናቀቃል የተባለ ቢሆንም፣ ሜድሮክ ኮንስትራክሽን የገጠመው የውጭ ምንዛሪ እጥረትና በክልሉ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት የግንባታ ዕቃዎቹ በወቅቱ መግባት ስላልቻሉ፣ ተጨማሪ 135 ቀናት መሰጠቱን የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ምስክር ሰውነት ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ሁለተኛ ዙር ግንባታውን ለማጠናቀቅ 1.8 ቢሊዮን ብር ተመድቧል ያሉት አቶ ሰውነት፣ 52 ሺሕ ወንበሮችን ለመግጠም ወንበር የማምረት ሥራ ሊጀመር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለዚህም ሜድሮክ ኮንስትራክሽን ፕላስቲክ ወንበሮችን ለማምረት ጥሬ ዕቃዎችን ወደ አገር ውስጥ ማስገባቱን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

ይገጠማሉ ከተባሉት ወንበሮች መካከል አራት ሺሕ የሚሆኑት በልዩ ሁኔታ ከውጭ የሚገቡ ናቸው ተብሏል፡፡ የመዋኛ ገንዳዎች፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ የመጫወቻ ሜዳዎችን ጨምሮ ሁለት የመለማመጃ ሜዳዎች፣ የመብራት ገጠማና ሌሎች ቴክኒካል ሥራዎች በሁለተኛ ዙር ግንባታው የተካተቱ መሆናቸውን አቶ ምስክር ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት ሌሎች ተቋራጮች ወንበሮችን እንዲገጥሙ ተሞክሮ ነበር ያሉት አቶ ምስክር፣ ነገር ግን ያቀረቧቸው ማቴሪያሎች ከደረጃ በታች በመሆናቸው ውድቅ ተደርገዋል፡፡

ከዚህ በመማር ሚድሮክ ኮንስትራክሽን ከሚያቀርባቸው ማቴሪያሎች የተወሰኑ ወንበሮች ተገጥመው ሙከራ እንደሚደረግባቸው የቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጎረቤት አገር ስታዲየም በውሰት የሚጫወተው፣ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ስታንዳርድን የሚያሟላ ስታዲየም ባለመኖሩ እንደሆነ ገልጸው፣ ይህንን ለማሟላት እየሠሩ መሆናቸውን አቶ ምስክር አብራርተዋል፡፡

ሁለተኛ ዙር ግንባታው እንደተጠናቀቀ ሦስተኛ ዙር የጣሪያ ገጠማ ሥራው እንደሚጀምር የቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ለዚህም መንግሥትና ሕዝብ ዕገዛ እንዲያደርጉ ከወዲሁ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡