ኒው ዮርክ ታይምስ

ከ 3 ሰአት በፊት

የአሜሪካ የዜና ድርጅት የሆነው ኒውዮርክ ታይምስ የቻት ጂፒቲ ባለቤት ኦፕንኤአይ (OpenAI) የተሰኘውን ሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ለማሰልጠን የቅጂ መብቴን ጥሷል በሚል ክስ መሰረተ።

ማይክሮሶፍትን እንደ መልስ ሰጪ (ተከሳሽ) የሰየመው ክሱ ድርጅቶቹ ለ “ቢሊዮኖች ዶላሮች” ጉዳት ተጠያቂ መሆን አለባቸው ብሏል።

ቻትጂፒቲ እና ሌሎች ትልልቅ የቋንቋ ሞዴሎች (LLMs) ብዙ ጊዜ በበይነ መረብ (ኢንተርኔት) ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው መረጃ በመተንተን “ይማራሉ”።

ቢቢሲ ኦፕንኤአይ እና ማይክሮሶፍትን አስተያየት ጠይቋል።

ክሱ በኒውዮርክ ታይምስ የሚታተሙ “በሚሊዮን የሚቆጠሩ” ጽሑፎች ቻትጂፒትን የበለጠ ለማላቅ እና የማሰላሰል ችሎታውን ለመጨመር ያለፈቃድ ጥቅም ላይ ውለዋል ይላል። ይህ መሳሪያ አሁን እንደ ታማኝ የመረጃ ምንጭ ከጋዜጣው ጋር እየተፎካከረ ነው ሲልም አክሏል።

ስለ ወቅታዊ ሁኔታዎች ሲጠየቅ፣ ቻት ጂፒቲ አንዳንድ ጊዜ ከኒውዮርክ ታይምስ መጣጥፎች “ቃል በቃል የተቀነጨበ” ምላሽ እንደሚያመነጭ፣ እነዚህ መጣጥፎች ለደንበኝነት ሳይከፍሉ ሊገኙ እንደማይችሉም ይከሳል።

በክሱ መሰረት፣ ይህ ማለት አንባቢዎች የኒውዮርክ ታይምስ ይዘቶችን ሳይከፍሉ ማግኘት ይችላሉ ማለት ነው – ይህም ማለት ከምዝገባ ገቢ እና ድረ ገጹን ከሚጎበኙ ሰዎች የማስታወቂያ እያጣ ነው።

ማይክሮሶፍት በኦፕንኤአይ ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ (£7.8 ቢሊዮን) ኢንቨስት አድርጓል።

ረቡዕ እለት በማንሃተን የፌደራል ፍርድ ቤት የቀረበው ክስ፣ ኒውዮርክ ታይምስ በቅጂ መብቱ ላይ “ሰላማዊ መፍትሄ” ለመፈለግ በሚያዝያ ወር ከማይክሮሶፍት እና ከኦፕንኤአይ ጋር መነጋገሩን ያሳያል።

ተደራራቢ ክሶች

የኒው ዮርክ ታይምስ ክስ የኦፕንኤአይ ተባባሪ መስራች እና ዋና ስራ አስፈጻዒ ሳም አልትማን ከስራ ከተባረረ እና ድጋሚ ከተቀጠረ በኋላ ከተፈጠረ ትርምስ በኋላ ነው የመጣው።

የእሱ መባረር የኢንዱስትሪውን የውስጥ አዋቂዎችን አስደንግጦ ወደ ስራው እስካልተመለሰ ድረስ ሰራተኞች በጅምላ ለመልቀቅ አስፈራርተውም ነበር።

ነገር ግን እንደ ውስጣዊ ጉዳዮች ሁሉ፣ ድርጅቱ አሁን በ2023 የተከሰቱት በርካታ ክሶች እያጋጠሙት ነው።

በመስከረም ወር ላይ ተመሳሳይ የቅጂ መብት ጥሰት ጉዳይ በአሜሪካ ደራሲያን ቡድን ጌም ኦፍ ትሮንስ ደራሲ ጆርጅ አር አር ማርቲን እና ጆን ግሪሻም ቀርቧል።

ይህ የደራሲዎቹ ክስ ሐምሌ ወር ላይ ኮሜዲያን ሳራ ሲልቨርማን የወሰደችውን ህጋዊ እርምጃ እንዲሁም በተመሳሳይ ወር በደራሲዎች ማርጋሬት አትውድ እና ፊሊፕ ፑልማን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ኩባንያዎች ስራቸውን በመጠቀማቸው ካሳ እንዲከፍላቸው ለመጠየቀ የተፈረመውን ደብዳቤ ተከትሎ የመጣ ነው።

በተጨማሪም ኦፕንኤአይ ከማይክሮሶፍት – እና የፕሮግራሚንግ ጣቢያ ከሆነው ጊትሃብ ጋር በኮምፒውተር ባለሙያዎች ክስ ተመስርቶበታል።

ባለሙያዎቹ ክሱን የመሰረቱት ኮፒሎት የተባለውን ሰው ሰራሽ አስተውሎት ለማሰልጠን ኮዳቸው ያለፈቃዳቸው ጥቅም ላይ መዋሉን በመጥቀስ ነው።

ከእነዚህ ክሶች መካከል አንዳቸውም እስካሁን አልተፈቱም።