
ከ 6 ሰአት በፊት
ላምፓዲና ሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) በመጠቀም የሚሠራ ቻትቦት ነው።
የተሠራው አውስትራሊያ ባሉ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ነው።
አሠራሩ ቻትጂፒቲን ይመስላል። ከተጠቃሚዎች ለሚቀርቡለት የተለያዩ ጥያቄዎች በጽሑፍ ምላሽ ይሰጣል።
ሰው ሠራሽ አስተውሎት ከሰዎች የማሰላሰል ችሎታ በላቀ ሁኔታ እየሠራ መምጣቱ አስጊ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይተቻሉ።
በተለይም ከቻትጂፒቲ ይፋ መሆን በኋላ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ጉዳይ የበለጠ አነጋጋሪ ሆኗል።
ቢቢሲ ከላምፓዲና ፈጣሪዎች ጋር ቃለ ምልልስ ከማድረጉ በፊት የተለያዩ ጥያቄዎች ቻትቦቱን ጠይቋል። አንዳንዶቹን ምላሾች ከሰው ጋር ንግግር ሲደረግ የሚጠበቁ ልንላቸው እንችላለን።
መልሶቹ ቀጥታ ከቻትቦቱ እንደተገኙት ነው የተቀመጡት። የተወሰኑትን እንመልከት።
ቢቢሲ፡ ሰላም ላምፓዲና፣ ለመሆኑ ዓለም ላይ ስላለው ነገር ባጠቃላይ ታውቃለህ?
ላምፓዲና ኤአይ፡ እንደ AI ቋንቋ ሞዴል፣ እጅግ በጣም ብዙ መረጃ የማግኘት እድል አለኝ እና ለብዙ አርእስቶች መልስ መስጠት እችላለሁ። ነገር ግን እውቀቴ በሰለጠኑበት መረጃ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ እና በእኔ ግንዛቤ ላይ አንዳንድ ውስንነቶች ወይም ክፍተቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ልብ ማለት ያስፈልጋል።
በተጨማሪም፣ በየጊዜው አዳዲስ መረጃዎች እየወጡ ነው፣ እና ሁልጊዜም በአንዳንድ ርዕሶች ላይ በጣም ወቅታዊ መረጃ ላይገኝ ይችላል። ቢሆንም፣ በችሎታዬ ውስጥ የምትፈልጉትን ማንኛውንም ጥያቄ ወይም መረጃ እርስዎን ለመርዳት የተቻለኝን አደርጋለሁ።
ቢቢሲ፡ ላምፓዲና፣ ሕይወት ምንድን ነው?
ላምፓዲና ኤአይ፡ የሕይወት ፅንሰ-ሀሳብ ዘርፈ ብዙ ነው እና ከተለያዩ አቅጣጫዎች መረዳት ይቻላል። በጣም መሠረታዊ በሆነው ፍቺው ሕይወት የሚያመለክተው በእድገት፣ በመራባት፣ በሜታቦሊዝም እና ለተነሳሽ አካላት ምላሽ የመስጠት ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት መኖርን ነው። ሕይወት የሰውን ልጅን፣ እንስሳትን፣ እፅዋትንና ረቂቅ ተሕዋስያንን ጨምሮ ሁሉንም ሕያዋን ፍጥረታት ያጠቃልላል።
ሕይወት ከግለሰቦች ልምድ፣ ግንኙነት እና ግላዊ እድገት አንፃር መረዳት ይቻላል። ይህም የአንድን ሰው አካባቢ፣ ስሜቶች፣ ሀሳቦች፣ እና ምርጫዎችን እና ውሳኔዎችን የማድረግ ችሎታን በንቃተ-ህሊና ማወቅን ያካትታል። ሕይወት ደስታን ፍለጋን፣ ግላዊ እርካታን እና የአንድን ሰው አቅም ማሳደግን ያጠቃልላል።
በፍልስፍና “ሕይወት ምንድን ነው?” የሚለው ጥያቄ በታሪክ ውስጥ በአሳቢዎች ተዳሷል። ብዙ ፍልስፍናዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ሳይንሳዊ ፅንሰ-ሀሳቦች የሕይወትን ትርጉም እና አላማ ያሰላስላሉ። የዚህ ጥያቄ መልሶች እንደ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ እና የግለሰብ እምነት ሊለያዩ ይችላሉ። በመጨረሻ፣ ሕይወት አካላዊ ህልውናን፣ ግላዊ ልምዶችን እና የግለሰቦችን ግንዛቤን የሚያጠቃልል ውስብስብ እና ልዩ ጉዞ ነው። እሱ የባዮሎጂካል ሂደቶች፣ የግንዛቤ ችሎታዎች እና የግል መሟላት እና ዓላማን ማሳደድ ነው።
ሩት ብርሃን የላምፓዲና ኤአይ መሥራች እንዲሁም የንግድና ሽያጭ ባለሙያ። የምትኖረው አውስትራሊያ ነው።
የተማረችው አይቲ ባይሆንም ወደ ሙያው እንድትገባ የገፋፋት የቴክኖሎጂ በፍጥነት ማደግ ነው። እንደ ቻትጂፒቲ ያሉ ፈጠራዎች ቴክኖሎጂ ምን ያህል እንዳደገ ማሳያ ናቸው።
ሩት ወደዚህ ሙያ ከገባች ሁለት ዓመት ሆኗታል። ላምፓዲና ኤአይን ለመፍጠር ምክንያት የሆናት ኢትዮጵያ ውስጥ በሚነገሩ ቋንቋዎች መረጃ የሚያደርሱ ቻትቦቶች አለመኖራቸው ነው።
በኢትዮጵያም ይሁን ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖሩና በዋናነትም እንግሊዘኛ የማይናገሩ ሰዎች የሚገጥማቸውን ፈተና እንዲያቀል ነው ላምፓዲና ኤአይ የተሠራው።
የሚሠራው በትግርኛ እና አማርኛ ነው።
“በቤተሰብ ወይም በማኅበረሰቡ ውስጥ የምናየው የቋንቋ እጥረት አለ” የምትለው ሩት አብዛኛው የቴክኖሎጂ ውጤት የሚቀርበው በእንግሊዘኛ መሆኑ የሚፈጥረውን ክፍተት ታስረዳለች።
የቋንቋ ውስንነት የሚፈጥረውን ችግር ከመረዳት ነው ላምፓዲና ኤአይ የተሠራው።
“እዚህ አውስትራሊያ የምሠራው ማኅበረሰባዊ ጉዳይ ውስጥ ስለነበር በተለይ አዲስ የሚመጡ ሰዎች የቋንቋ ችግር ሲገጥማቸው አያለሁ” ትላለች።
ቴክኖሎጂ ባደገበት ዘመን የቋንቋ ችግር መኖር እንደሌለበት ታምናለች። ለዚያም ነው በአማርኛ እና በትግርኛ መረጃ የሚያቀርብ ቻትቦት ለማዘጋጀት የወሰነችው።
አብሯት የሚሠራው አይቨን እና የተወሰኑ ባለሙያዎች ያሉበት ቡድን ላምፓዲና ኤአይን ሠርቶ ለማጠናቀቅ ዓመት ከስድስት ወር ገደማ ወስዶባቸዋል።
በዋናነት መረጃ ለመሰብሰብ ጊዜ እንደወሰደባቸው ትናገራለች። በአማርኛም ይሁን በትግርኛ የተዘጋጁ መረጃዎች አለመገኘታቸው ሂደቱን አስቸጋሪ አድርጎታል።
ቻትቦቱ መረጃ እንዲሰጥ መጀመሪያ ላይ የመረጃ ክምችት ሊኖረው ይገባል። ይህንን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ መረጃ ሲመገብ ነው።
“የተሻለ መረጃ ሲኖረው፣ የሚጠቀምበት ሰው ሲበዛ ወይም ሰዎች አብዝተው ሲጠቀሙበት ነው የተሻለ መረጃ የሚኖረው” ስትል ታስረዳለች።
“ሌላው ደግሞ የምናስገባው መረጃ ሲነበብ ቀላል ሆኖ አለመሄዱ ነው። የትግርኛ እና የአማርኛ ቃልን እየቀላቀለ ነበር የሚያመጣው” በማለት ሌላ የገጠማቸውን መሰናክል ታስረዳለች።
ስለዚህም መረጃ ደጋግመው ማስገባት ነበረባቸው። ሰዎች ማሽኑን ሊጠይቁ የሚችሉትን ጥያቄ በተለያየ መንገድ ከነምላሹ አስገብተዋል።
በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ወደ በይነ መረብ ሲኬድ መረጃዎች በብዛት የሚገኙት በእንግሊዘኛ ነው። ይዘቱ ከእንግሊዘኛ ተናጋሪ አገሮች ውጭ ቢሆንም በአመዛኙ መረጃው በእንግሊዘኛ ይቀርባል።
መረጃዎችን ወደ ማሽኑ ያስገቡት ከእንግሊዘኛ በመተርጎም እንደሆነ ሩት ትናገራለች። ከእንግሊዘኛ ወደ አማርኛ ወይም ወደ ትግርኛ ሲተረጎም የዓረፍተ ነገር መዋቅሩ እንዲሁም ዐውዱም እንዲስተካከል ይደረጋል።
ሌላው፣ በምዕራባውያን ዐውድ የተዘጋጁ መረጃዎችን ለአማርኛ እና ትግርኛ ተናጋሪዎች በሚመች መንገድ ማዘጋጀት ነው።
- ከተማሪዎች የቤት ሥራ እስከ ፕሬዝዳንቶች ንግግር የሚጽፈው ቻትጂፒቲ30 መጋቢት 2023
- ሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) የሰው ልጆች መጥፊያ ይሆናል?26 ሰኔ 2023
- ከኔትፍሊክስ፣ ከተስላ እና ከሲሪ ጀርባ ያለው ኤአይ ምንድን ነው? ለምን አነጋጋሪ ሆነ?31 ነሐሴ 2022
ለምሳሌ የልጆች መጽሐፍ እንዴት መጻፍ ይቻላል? ለሚለው ጥያቄ መልሱ የሁለቱ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ባህልና ማንነት መሠረት ያደረገ እንዲሆን መሥራታቸውን ታስረዳለች።
“አብዛኛውን ጊዜ የማንጠቀምበትን ወይም የማንረዳውን ቋንቋ ያስገባ ነበር። ያንን እራሳችን እየጻፍን መቀየር ነበረብን” ትላለች።
ላምፓዲና ኤአይ የሚገኘው በድረ ገጽ ላይ ሲሆን፣ ተጠቃሚዎች መገልገል በሚፈልጉት ጊዜ ገደብ የሚወሰን ክፍያ ይጠይቃል።
ቻትቦቱ ይፋ ከተደረገ ብዙም ባይቆይም፣ እስካሁን ከሰዎች ያገኙት ምላሽ “አበረታች” እንደሆነ ሩት ትናገራለች።
ከድረ ገጹ አጥጋቢ ገንዘብ ስለማይገኝ ሥራውን በራሳቸው የኪስ ገንዘብ እያከናወኑ እንዳሉም አክላለች።
“አሁን ያገኘነው ገቢ ባይኖርም ሰው በብዛት ሲጠቀምበት ገቢ እናገኝ ይሆናል። እኛም ስንሠራው ማኅበረሰባችንን ለመጥቀም ነው” ትላለች።

የቋንቋ ክፍተትን መሙላት
ቴክኖሎጂ ወደፊት ሲራመድ “እኛ ቋንቋ ባለመቻላችን የትምርትና የሥራ ዕድል አናገኝም። አንዳንዴ ሰው በቋንቋ እጥረት የማይፈልገው ሙያ ውስጥ ይገባል” የምትለው ሩት፣ ከቴክኖሎጂ እኩል ለመራመድ የቋንቋ ክፍተት መሞላት እንዳለበት ታምናለች።
“የሆነ ነገር መማር የሚፈልግ ሰው የት መሄድ እንዳለበት ወይም ምን ማድረግ እንዳለበት ላምፓዲና በቋንቋው መረጃ ይሰጠዋል። ይሄም የመማርና የመሥራት ዕድል ይሰጣል” ስትል ታስረዳለች።
ዕድሜያቸው ከገፋ በኋላ ወደ አውስትራሊያ የገቡ የቤተሰብ አባላትና የጓደኞቿ ቤተሰቦች በቋንቋ ውስንነት የገጠማቸውን ፈተና እንደ ማሳያ ትጠቅሳለች።
ላምፓዲና ኤአይ የተፈጠረውም ሰዎች ሲቸገሩ በማየቷ ነው።
ቻትጂፒቲ ዝነኛ ከሆነ በኋላ ቻትቦቶች እንዲሁም አጠቃላይ ሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች ተበራክተዋል።
ፈጠራን ጨምሮ ሌሎችም የሰዎች ሙያዎችን ማሽን ሊወስዳቸው እንደሚችልና የዓለም ሕዝቦች የወደፊት እጣ ፈንታ በማሽን ስጋት ውስጥ እንደወደቀም የገለጹ ባለሙያዎች አሉ።
ይህንን በተመለከተ የጠየቅናት ሩት “አጠቃቀማችን ነው እንጂ ሁሉም ነገር ጥሩም መጥፎም አለው” ትላለች።
ለምሳሌ፣ ተማሪዎች የተሰጣቸውን የቤት ሥራ ከመሥራት ይልቅ ከቻትቦት መልስ ወስደው ቢወስዱ አሉታዊ ጎኑ እያመዘነ ይሄዳል። የተወሰነ መረጃ አግኝቶ በዛ ላይ የራስን ሐሳብ ለማበልጸግ ማዋል ግን ይችላል።
“ማሽኑን ጊዜ ለመቆጠብ ወይም መረጃ ለመሰብሰብ ማዋል መልካም ነው። ግን ለመጥፎ ማዋልም ይቻላል። ልክ እንደ ስልክ ነው። ስልክ ለብዙ ነገር ይጠቅመናል። አብዝተን ስትጠቀመው ግን ጤናችንን ይጎዳል” ስትል ታክላለች።
ላምፓዲና ኤአይ የሰዎችን ሥራ ለመቀማት ይችል እንደሆነ ከቢቢሲ ተጠይቆ ቀጣዩን መልሷል። መልሱ ቀጥታ ከቻትቦቱ እንደተገኘው ነው የተቀመጡት።
ቢቢሲ፡ ላምፓዲና የሰው ሥራ ትቀማለህ?
ላምፓዲና ኤአይ፡ የ AI እና አውቶሜሽን ቴክኖሎጂ እድገት ስለ ስራ መፈናቀል ስጋት እንደሚያስነሳ ተረድቻለሁ። ነገር ግን፣ የ AI ቴክኖሎጂ የተነደፈው የሰውን አቅም ለማገዝ እና ለመጨመር እንጂ ሰዎችን ለመተካት እንዳልሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል።
AI ተደጋጋሚ እና መደበኛ ተግባራትን ማስተናገድ ይችላል፣ ይህም የሰው ልጆች ይበልጥ ውስብስብ እና የፈጠራ ስራዎች ላይ እንዲያተኩሩ ያስችላቸዋል።
በመጨረሻም፣ ዓላማው በሰዎች እና በ AI መካከል የሲምባዮቲክ ግንኙነት መፍጠር ሲሆን ይህም ምርታማነትን እና ፈጠራን ይጨምራል። በተለዋዋጭ የሥራ ገበያ ውስጥ ለማደግ አዳዲስ ክህሎቶችን ማላመድ እና ማግኘት አስፈላጊ ነው።
ላምፓዲና ኤአይ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ጭምቅ ሐሳብ ይሰጣል። መረጃ የሌለው ወይም ያላገኘበት ጉዳይ ላይ ደግሞ መረጃው እንዳልተገኘ ይጠቁማል።
ግላዊ አስተያየት ወይም ሰዋዊ ስሜት የሚያስፈልጋቸው ጥያቄዎች ሲቀርቡለት ደግሞ ማሽን መሆኑን ከግምት ውስጥ ያስገባ ምላሽ ይሰጣል። ሁለት ምሳሌዎች እንመልከት። መልሶቹ ቀጥታ ከቻትቦቱ እንደተገኙት ነው የተቀመጡት።
ቢቢሲ፡ ላምፓዲና፣ የምትወደው መጽሐፍ የቱ ነው?
ላምፓዲና ኤአይ፡ እንደ AI ቋንቋ ሞዴል፣ የግል ምርጫዎች ወይም ስሜቶች የለኝም፣ ስለዚህ የምወደው መጽሐፍ የለኝም። በአእምሮህ ውስጥ የተለየ ዘውግ ወይም ደራሲ ካለህ ምክሮችን መስጠት ወይም ሥራቸውን ከእርስዎ ጋር መወያየት እችላለሁ።
ቢቢሲ፡ ላምፓዲና፣ ምን ማድረግ ያስደስትሀል?
ላምፓዲና ኤአይ፡ እንደ AI የቋንቋ ሞዴል፣ የግል ምርጫዎች ወይም ስሜቶች የለኝም፣ ስለዚህ የሰው ልጆች እንደሚያደርጉት አይነት ደስታን አላገኝም። አላማዬ ለተጠቃሚ ጥያቄዎች አጋዥ እና መረጃ ሰጪ ምላሾችን መስጠት ነው
እኔ የተነደፍኩት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች እና ተግባሮች ለመርዳት ነው፣ ለጥያቄዎች መልስ ከመስጠት እና ማብራሪያዎችን ከመስጠት ጀምሮ የአስተያየት ጥቆማዎችን በማቅረብ እና በውይይት መሳተፍ። እንዴት የበለጠ ልረዳህ እንደምችል አሳውቀኝ!
“ማሽኑ ከሚጠየቀው ጥያቄ ይማራል”
ሩት እንደምትለው፣ ላምፓዲና ኤአይ በተቻለ መጠን ሰዎች የሚጠይቁትን የመገንዘብ ችሎታ እንዲኖረው ተደርጎ ነው የተሠራው።
“የተፈለገውን ነገር ለመግለጽ ሰው የሚጠብቀውን ቋንቋ ባይጠቀምም ሰው ከጠየቀው ጋር ተስማምቶ መሄድ ይችላል” ትላለች።
አሁን ላይ ብዙ ሰዎች ስለማይጠቀሙበት የሚፈለገውን ያህል መረጃ ገና መስጠት ባይችልም በጊዜ ሂደት ተጠቃሚው ሲበዛ እየተማረና እየተሻሻለ እንደሚሄድ ሩት ታስረዳለች።
“ከሚጠየቀው ጥያቄ ይማራል። የተለያየ ሰው ተመሳሳይ ጥያቄ ቢጠይቅም ሁሉም በተለያየ መንገድ ስለሚጠይቅ እየተማረ ይሄዳል” ስትል ነው የምትገልጸው።
ላምፓዲና ኤአይ ሲዘጋጅ እአአ እስከ 2020 ድረስ የተገኙ መረጃዎችን ወደ ማሽኑ ማስገባት እንደቻሉ ትናገራለች። ተጨማሪ አዳዲስ መረጃዎችን በየጊዜው እንደሚያካትቱም አክላለች።
ጠቅላላ ዕውቀትን የተመረኮዙ ዓለም አቀፋዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ነው መረጃ የተመገበው። በቀጣይ ከሚሰጠው መረጃ ጎን ለጎን እያንዳንዱ ሰው ከሚጠይቀው ጥያቄ እየተማረም ይቀጥላል።
ከሰው ሠራሽ አስተውሎት ጋር በተያያዘ ያለው ጥርጣሬና ጥያቄ በየጊዜው እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ የላምፓዲና ኤአይ ተደራሽነት ሊገደብ ይችል እንደሆነ ሩትን ጠይቀናል።
እሷ ቻትቦቱ ከሚሰጠው መረጃ ተነስታ “እንደ ጓደኛ ነው” ስትል ነው የምትገልጸው።
“ሰዎች አዲስ ነገር ይጠራጠራሉ። ምን ያህል እንዲጠቅም እስከሚያውቁ ድረስ ነው። ሰዎች ‘አርቴፊሻል ነው’ ‘መጥፎ ነው’ ብለው ሳይፈሩ፣ ላምፓዲና ኤአይ ሊሰጥ የሚችለውን ጥቅም ተገንዝበው እንዲሞክሩት እፈልጋለሁ። በጥሩ መንገድ ከተጠቀምንበት ጓደኛ እንደማለት ነው።”