
ከ 4 ሰአት በፊት
እስራኤል በእግረኛ ጦሯ የምታደርገው ጥቃት በማዕከላዊ ጋዛ በሚገኙ የፍልስጤም የስደተኞች መጠለያ ስፍራዎችን ኢላማ ማድረጉ ተገለጸ።
እስራኤል ከሐማስ ጋር እያደረግኩት ነው ያለችው ጦርነትም ለወራት እንደሚቆይ ማስጠንቀቂያ እየሰጠች ትገኛለች።
በቅርቡ ቡሬጅ፣ ኑሴይራት እና ማግሃዚ በተሰኙት የስደተኞች መጠለያዎች ጦሩ ባደረሰው ጥቃት በርካታ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ተከትሎም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስጋቱን እየገለጸ ይገኛል።
በደቡባዊ ጋዛ በምትገኘው ኻን ዩኒስም ውጊያው መፋፋሙ እየተነገረ ነው።
የፍልስጤም ግዛት ፕሬዚዳንት እስራኤል በጋዛ እየፈጸመችው ያለውን “ፍጹም ውድመት እና እልቂት” ነው ሲሉም ነው የገለጹት።
ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በግዛቲቱ ቢያንስ 195 ሰዎች መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።
እስራኤል በባለፉት 11 ሳምንታት በፈጸመቻቸው ጥቃቶች ከ21 ሺህ 100 በላይ ፍልስጤማውያን የተገደሉ ሲሆን ከነዚህም አብዛኛዎቹ ህጻናት እና ሴቶች መሆናቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
የቅርቡ ጦርነት መነሻ የተቀሰቀሰው ሐማስ በደቡባዊ እስራኤል በፈጸመው ጥቃት 1 ሺህ 200 ሰዎች መገደላቸውን እና 240 ታጋቾች መወሰዳቸውን ተከትሎ ነው።
የፍልስጤም መገናኛ ብዙኃን የአካባቢው ባለስልጠናትን እና የዓይን እማኞችን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ተጠናክሮ በቀጠለው የእስራኤል ጥቃት በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ነው።
በመካከለኛው ጋዛ የሚገኙት በተለይም ቡሬጂ፣ ማግሃዚ እና ኑሴይራት የስደተኞች መጠለያ ስፍራዎች የከበዱ ጥቃቶችን አስተናግደዋል ተብሏል።
- 12 ወንዞችን ተሻግራ ኡጋንዳ የደረሰችው ኤርትራዊቷ ስደተኛ የመከራ ጉዞከ 5 ሰአት በፊት
- ላምፓዲና ኤአይ፡ በአማርኛ እና በትግርኛ የሚሠራው ቻትቦትከ 6 ሰአት በፊት
- ሰላም ሚኒስቴር በአቶ ታዬ ደንደአ እና በዶ/ር ስዩም መስፍን ቦታ ሁለት ሚኒስትር ዲኤታዎች ተሾሙለት27 ታህሳስ 2023
በኑሴይራት የእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች የናስር እና የሃዙኪ ቤተሰቦችን ኢላማ በማድረግ በርካታ ሰዎች የገደሉ መሆናቸውን እንዲሁም ብዙ ሰዎችንም ማቁሰላቸውን ዋፋ የተሰኘው የዜና ወኪል ዘግቧል።
በተጨማሪም በማግሃዚ የሴቶች ትምህርት ቤት ላይ በተፈጸመ ጥቃት አምስት ሰዎች መገደላቸውንም ሳፋ የተሰኘው ሌላኛው የዜና ወኪል ዘግቧል።
ከቡሬጅ ወረዳ በስተምስራቅ እና በሰሜን እንዲሁም በአቅራቢያዋ በምትገኘው ጁህር አል ዲክ መንደር ከባድ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑንንም ሮይተርስ ከነዋሪዎች ሰምቷል።
በቅርብ እየተፈጸመ ስላለው ጥቃት ከእስራኤል መከላከያ ኃይል በኩል የተሰጠ አስተያየት ባይኖርም ነገር ግን ቃለ አቀባዩ ዳንኤል ኃጋሪ ማክሰኞ ማምሻውን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ጦሩ “ውጊያውን ወደ ማዕከላዊ ካምፖች ማስፋታቸውን” ተናግረዋል።
ከጦርነቱ በፈት ቢያንስ ወደ 90 ሺህ የሚጠጉ ፍልስጤማውያን በነዚህ የስደተኛ መጠለያዎች ይኖሩ እንደነበር ከተባበሩት መንግሥታት የተገኘው መረጃ ያስረዳል። በተጨማሪም ከጦርነቱ በኋላ ከሰሜን ጋዛ እንዲፈናቀሉ የተደረጉ ወደ 61 ሺህ የሚጠጉ ስደተኞችን የሚያስተናግዱ ስድስት መጠለያዎችም ጥቃቱን ካስተናገዱት መካከል ናቸው።
