የልዋም የስደት ጉዞ

ከ 5 ሰአት በፊት

ባለፈው አስር ዓመት ከኤርትራ ወደተለያዩ ጎረቤት አገራት እየተሰደዱ ያሉ ወጣቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽነር ያወጣቸው ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

በተለያየ ምክንያት ከተሰደዱት ኤርትራውያን መካከል ጥቂቶቹ በዘመድ እና በቤተሰብ ድጋፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወዳለሙት መዳረሻ ሲደርሱ ሌሎች ደግሞ የሚረዳቸው ስለማይኖር የደረሰቡት ጎረቤት አገራት ውስጥ ዕለታዊ ኑሮአቸውን ሲመሩ ይታያሉ።

እንደዛም ሆኖ ግን በሚኖሩባቸው ሀገራት በሚፈጠር ያልተረጋጋ እና ተለዋዋጭ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ችግሮች ዳግመኛ ለስደት ይጋለጣሉ።

ሱዳን ውስጥ በተቀሰቀሰው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ያፈሩትን ንብረት ጥለውና ጨርቄን ማቄን ሳይሉ የትውልድ አገራቸው ያክል የሚያስቧትን ሱዳንን ለቀው እየሸሹ ነው።

አንዳንዶቹ በመንገድ ላይ ሲሞቱ ሌሎቹ ደግሞ የራሳቸውን ዘግናኝና አሳሳቢ ታሪኮችን ይናገራሉ።

የስደት ጉዞ

የልዋም የስደት ጉዞ

ይህ ታሪክ ከሱዳን ጦርነት ለማምለጥ ብዙ ውጣ ውረዶችን ስላሳለፈችው ኤርትራዊቷ ልዋም ነው።

ከስድስት ዓመት በፊት ከከረን ኤርትራ ወደ ሱዳን ተሰደደች። መጀመሪያ ወደ ከሳላ፣ ከዚያም ወደ ሸገራብ ከዛ ደግሞ ካርቱም ገባች።

በወቅቱ ሱዳን ውስጥ ወጥቶ የሚገባበት አንጻራዊ ሰላም ስለነበር፣ ካርቱም ውስጥ በሚገኝ ኩባንያ ውስጥ ስራ ጀመረች።

በሱዳን ተፋላሚዎች መካከል ጦርነት እስኪነሳ ድረስ በሱዳናዊ ድርጅት ውስጥ እንግዳ ተቀባይ ሆና ትሰራ ነበር።

ልዋም ኑሮዋን ለማሸነፍ ብትታገልም፣ የሱዳን የፀጥታ ሁኔታ እየተባባሰ በመምጣቱ፣ የጸጥታ ኃይሎች “በሁለት ሺህ ሰማንያ ጂኔ” በሚባል ይለፍ ወረቀት አሳበው በስደተኞች ላይ ጫና መፍጠር ሲጀምሩ እሷም ከባድ ፈተና ሆነባት።

አንድ ቀን ረፋድ ላይ ወደ ስራ ስትሄድ ከመኪና አውርደው እንዳሰሯት እና 1,000 ዶላር ከፍላ እንደወጣች ትናገራለች።

“በተለይ ኤርትራዊያን ገንዘብ ከፍለው መውጣት ይችላሉ ስለሚሉ በምንኖርበት አካባቢ በብዛት ተበታትነው ይገፋሉ። አንዳንድ ያልታደሉት ሁለት ሶስት ጊዜ ተይዘው አንድ ሺ አንድ ሺ ዶላር የከፈሉ ነበሩ። ከፍለው ከፖሊስ ጣቢያ መውጣት የማይችሉትን ደግሞ ወደ ሌላ ማረሚያ ቤት ያዘዋውሯቸዋል።”

የፋሲካ ዋዜማ

የሱዳን ግጭት

ባለፈው አመት እሷ እና ጓደኞቿ በፋሲካ ዋዜማ ቤተክርስትያን ውስጥ እያሉ በድንገት ከፍተኛ የተኩስ ድምጽ መሰማት ጀመረ።

ተኩሱ ቶሎ የሚበርድ መስሏትም ነበር። ለዚያም ነው በተኩሱ ምክንያት ወደ ስራ መሄድ እንደማትችል ለአለቃዋ ለማሳወቅና ፈቃድ ለመጠየቅ ስትል ስልክ ደወለች።

ሱዳናዊው አለቃዋ ሁኔታውን ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ‘ይህ በወንድማማቾች መካከል የሚደረግ ጠብ ነውና ከባድ ስለሆነ ተጠንቀቂ። እኛ እስክንደውልልሽ ድረስ ወደዚህ አትምጪ፣ እናም አደራ አትውጪ’ ሲል አስጠነቀቃት።

ከዚያ በኋላ ሁኔታው ተባብሶ በከተማ ውስጥ መኖር በጣም አስቸጋሪ ሲሆን ሁኔታው እስኪረጋጋ ድረስ ዞር ለማለት ወደ ካሳላ አቀናች።

እንደጠበቀችው ሳይሆን ቀርቶ ታላታ አሸር የተባለ የመጨረሻ የፍተሻ ኬላ ሲደርሱ፣ የሱዳን ወታደሮች ፓስፖርትም ሆነ የስደተኛ ወረቀት የሌላቸውን ብዙ ኤርትራውያንን እናንተ ወደ አገራችሁ መግባት አለባችሁ ብለው ለብቻቸው ለዩዋቸው።

ይህንን ያስተዋለችው ልዋም ወደ ኤርትራ ከተመለሰች ገፈፋ እና ውትድርና እንደሚጠብቃት ስለሰጋች የ8 ዓመት ህጻን ከሚገኝባቸው ዘጠኝ ሰዎች ጋር ከጠዋቱ 1፡30 ላይ ሽንታቸውን የሚሸኑ መስለው ሸሽተው ከሳላ እንደገቡ ትገልጻለች።

ከሳላ ውስጥ ምንም እንኳን ከካርቱም የተሻለ አንጻራዊ ሰላም ቢኖርም ፍርሃት ስላደረባቸው ተደብቀው በከሰል ምግብ እያበሰሉ ለሦስት ወራት ያህል ቆዩ።

በኋላ ግን ከሳላ ውስጥ ለብዙ ዓመታት የኖረች ኤርትራዊት ሴት አንድ ቤት ከነሙሉ ንብረቱ በተመጣጣኝ ስታገኝላቸው እፎይ አሉ።

ይሁን እንጂ ያኔም ቢሆን ጦርነቱ እየተባባሰ በመሄዱ እፎይ ብለው መቀመጥ አልቻሉም።

ከድንበር ሸሽተው በከሳላ አብረዋት ከነበሩት 10 ሰዎች መካከል የተወሰኑት ወደ ግብፅ፣ ሌሎቹ ደግሞ ወደ አዲስ አበባ ሲበታተኑ ልዋምም በገዳሪፍ አድርጋ ወደ መተማ አቀናች።

ጉዞ ወደ መተማ

የልዋም የስደት ጉዞ

ጉዞው በሙሉ በደላሎች እና በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች የሚካሄድ በመሆኑ ሁሌም ፍርሃትና ስጋት አለ። ኢትዮጵያውያን መስለው መንገድ ላይ ጉቦ እየሰጡ ከገዳሪፍ መተማ ገቡ።

ነገር ግን በመተማ ብዙ ኤርትራውያን ስለነበሩና እየመዘገቡ ወደ ኩመር ካምፕ ይወስዷቸው ስለነበር፣ ልዋምና ጓደኞቿ 600 ዶላር ከፍለው ከአራት ቀናት በኋላ አዲስ አበባ ደረሱ።

“በእርግጥ ፈርቼ ነበር” ትላለች የጉዞውን ክብደት ስታስታውስ። “እንደ አገሬው ስላልሆንን መንገድ ላይ ሰዉ ወርዶ ቁርስ ሲበላ እኛ ፈርተን አንበላም ነበር። አንዳንዶቹ ከየት እንደሆንክ ይጠይቃሉ፤ ኢትዮጵያዊ ነኝ ትላቸዋለህ ግን ስለምናስታውቅ እና የቋንቋ ችግርም ስላለብን በጣም ከባድ ነበር።” ትላለች

አዲስ አበባ ውስጥ ተረጋግታ ለመኖር አስባ የነበረ ቢሆንም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ ኤርትራውያን እና ስደተኞች የመኖሪያ ፈቃድ በሚመለከት ቀጣይ ችግር ሲገጥማቸው ስለታዘበች በኬንያ በኩል ወደ ኡጋንዳ ለመሻገር ወሰነች።

ከዚያም በጓደኛዋ እርዳታ ከአንድ ደላላ ጋር በ2000 ዶላር ተዋዋለች። ጉዞው ሶስት ቀን እንደሚወስድ ተነግሯት ማታ 2፡00 ሰዓት አካባቢ ከአዲስ አበባ ተነስተው እሮብ ጠዋት በጭነት መኪና ቡሌ ሆራ (ሀገረ ማርያም) ደረሱ።

በማግስቱ ጉዞ ለመቀጠል እያሰቡ ሳለ፣ ጉዞው በጣም አደገኛ መሆኑን ከእርሷ በፊት ከተጓዙ ሰዎች ሰማች።

ደላላዎቹ አንድ ሞተር ሳይክል ላይ አምስት ሰው ጭነው በፍጥነት የፍተሻ ኬላዎች ጥሰው እንደሚያሻግሯቸው ሲነገራት “በስምምነታችን መሰረት የይለፍ ወረቀት አድርጋችሁ በአስተማማኝ መንገድ ለምን አትወስዱንም?” ስትል ጠየቀች። ‘ወረቀቱ መንገድ ላይ ይደርስልናል’ የሚል ምላሽ ሰጥተው ጉዞውን አስቀጠሏቸው።

ይሁን እንጂ መረጃው ትክክል ስላልነበረ እሷና አብረዋት የሚጓዙት ሰዎች ከሀገረ ማርያም 100 ኪሎ ሜትር እንደሄዱ ተያዙ።

ፓስፖርት ወይም የስደተኛ ወረቀት ሲጠየቁ ፍርሃትና እስካሁን ያሳለፈችው ስቃይ ተደባልቆ እያለቀሰች ‘ከሱዳን ግጭት የተረፈች እንደሆነች፣ ሰነዶቿ በሙሉ ቤታቸው ላይ ባረፈዉ የቦምብ ፍንዳታ አመድ እንደሆኑ’ ስትነግራቸው አዘኑላት። ለደህንነታቸው ሲባል ፖሊስ መጥቶ በዋስ እንዲወስዳቸው ብለው ወደ መጀመሪያው የፍተሻ ጣቢያ መለሷቸው። የሚያሻግራቸው ህገ ወጥ ደላላም ሰው ልኮ አስመለጣቸውና እንደገና ይዟቸው ጉዞን ቀጠለ።

ከረዥም ጉዞ በኋላ የኢትዮጵያ እና የኬንያ ድንበር ላይ ሞያሌ ደረሱ።

የቀጠለው የመከራ ጉዞ

የልዋም የስደት ጉዞ

ሞያሌ መድረሷ ትንሽም ቢሆን እፎይታ ተሰምቷት ነበር ‘ተመስገን፣ አሁንስ ተቃርበናል!’ ብላ አለች።

ነገር ግን ቆይታ የተሰጣት የይለፍ ወረቀት ሀሰተኛ (ፎርጅድ) እንደሆነ ተገነዘበች። ከፍርሃት አልወጣችም፤ ልዋምን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ተያዙ። እዚያም ግን ደላሎቹ ጉቦ ከፍለው አስመለጧቸው። እንደነሱ በህገ ወጥ መንገድ ሊሻገሩ ካሰቡ 49 ኤርትራውያን ጋር ለዘጠኝ ቀናት አንድ ቤት ውስጥ ተደበቁ።

“ለምን እንደዘገየን እና የት እንዳለን ስንጠይቅ እንዳንሸሽ ብለው አይነግሩንም። ነገር ግን የሚያሻግራችሁ [ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪ] (ሳምሳሪ) ደውሎልን ነበር። ጭቃ ስላለ መጓዝ አንችልም እያሉ ሰበብ ይሰጡን ነበር። ስለዚህ በአንድ ቤት 36፣ በሁለተኛው 34፣ በሦስተኛው 14 እና በሌላው 7 ነበርን።”

ነገር ግን ከዘጠኝ ቀናት በኋላ 46 የሚሆኑ ያኔ ከተጨመሩ ሌሎች 17 ጋር በሞተር ሳይክል ረጅም መንገድ እንደወሰዷቸው እና ቀሪውን መንገድ በሙሉ በእግር እንደተጓዙ ታስታውሳለች።

ምንም ምግብ አልነበራቸውም፤ በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ሩዝ ይሰጣቸዋል።

በአካባቢው ለሳምንት ያህል ቀንና ሌሊት ያለማቋረጥ ይዘንብ ስለነበር ጎርፍ አጋጠማቸው። በአጋጣሚ አብረዋቸው መዋኘት የሚችሉ ተጓዦች ስለነበሩ አንገታቸው ላይ የሚደርሰውን ጎርፍ አሻገሯቸው።

“ለጥቂት ሰዓታት እንደተጓዝን ሌላ ወንዝ ሞልቶ ጠበቀን። እንደበፊቱ ሞተር ብስክሌቶችን አስቀድመው እኛን በእግር አሻገሩን። ጎርፉ አንዳንድ አከባቢ እስከ ጭንቅላታችን፣ ሌላ አካባቢ ደግሞ እስከወገባችን ይደርሳል። እሱንም ግን በስንት መከራ ነው የተሻገርነው። ደረቅ መሬት ደርሰን ለጥቂት ሰዓታት እንደተጓዝን ደግሞ ሌላ ኃይለኛ ጎርፍ ጠበቀን። አንዳንድ ሴቶች በጎርፉ ሊወሰዱ ነበር ግን እንደ እድል ሆኖ እሱንም ተሻገርን” በማለት አደገኛ ጉዞዋን ትተርካለች።

መንገድ ላይ 46 የሚጠጉ ኤርትራውያን እና 100 ኢትዮጵያውያን ተቀላቀሏቸው። ወደ 200 የሚጠጉ ሰዎች ከባድ ጭቃ ላይ እየወደቁ እና እየተነሱ ከተጓዙ በኋላ ለ6ኛ ግዜ ጎርፍ አጋጠማቸው። ይሁን እንጂ ሕገወጥ ደላሎች ለሕይወታቸው ደንታ ሳይሰጡ ለራሳቸው ብቻ ያደርጉ ስለነበር የበለጠ አደጋ ውስጥ እንደከተታቸው ልዋም ታስረዳለች።

“በጣም አስቸጋሪ ወቅት ነበር። አንዳንዶቹ ከአባታቸው ጋር፣ አንዳንዶቹ ከእናታቸው ጋር፣ አንዲት የ3 ዓመት፣ አንዱ አንድ ዓመት ተኩል ሌላ ደግሞ የ11 ዓመት ልጅ አብረውን ነበሩ። እኛ ግን ወጥተን ጉዞ ጀመርን። ግራ እና ቀኝ አይተን ብንጮህ ሰሚ የለንም፤ ስለዚህ ወደ ፊት ከመሄድ ሌላ አማራጭ አልነበረንም” ስትል ታስታውሳለች።

12 ወንዞችን ተሻገርን

የልዋም የስደት ጉዞ

የየተስማሙበት ሌላ፤ የጠበቃቸው ሌላ ሲሆንባቸው ምንድን ነው? ብለው ሲጠይቁ ‘ክረምቱ አሁን ነው የጀመረው፤ ገና ስለሚቀጥል እናንተን ቁጭ አድርገን መቀለብ አንችልም። እና እዚህ የምታዩት ጭቃ ውስጥ ደግሞ ምንም አይነት መኪና እንዲመጣላችሁ አትጠብቁ። እኛም ስራችንን እየሰራን ነው። ስለዚህ መንገዳችሁን ቀጥሉ’ የሚል መልስ እንደተሰጣቸው በትካዜ ትናገራለች።

በዚህ መልኩ ለ16 ቀናት በእግር ተጓዙ፤ ፈጣሪ ዳኑ ሲላቸው ግን በመካከላቸው መዋኘት የሚችሉ ስለነበሩ እርስበርስ እየተረዳዱ መዋኘት የማይችሉትን እያሻገሩ መንገዳቸውን ቀጠሉ።

በረሃብና በመራር ሁኔታ የተናደዱት ወጣቶቹ ከዚህ የከፋ ነገር አይደርስብንም ብለው ስላሰቡ ተቀብለው ወንዝ ካሻገሯቸው ሰዎች ጋር ስምምነታችን እንዲህ አልነበረም፣ ገንዘብ ከፍለን ስናበቃ በረሃብና ለሕይወት በሚያሰጋ መንገድ እየወሰዳችሁን ነው የሚል ከፍተኛ ጭቅጭቅ እንደተፈጠረ ልዋም ታስታውሳለች።

ደላሎቹ ኢትዮጵያውያኖቹን ይደበድቧቸዋል፤ ኤርትራውያኖችን ደግሞ ለማስፈራራት ጥይት ይተኩሳሉ። ኤርትራውያኖቹ ‘እዚህ ያለው ሁሉ ወታደር ነው፤ እያደረጋችሁት ያላችሁት ነገር አያስፈራንም’ ብለው መልሰው ሲጨቀጭቋቸው የተወሰነ ምግብ እንደሰጧቸው ትናገራለች።

“ሴቶቹን 12ቱን በአንድ ገበታ ይሰጡን ነበር። ወንዶቹ ግን ትንሽ እንደሚሰጧቸውና እንደማያጠግባቸው ስለምናውቅ ከኛው ላይ አስተርፈን እንሰጣቸው ነበር። ሁላችንም ሴቶች ከሞላ ጎደል ከመንገዱ ርዝመት የተነሳ ጭናችን ስለተላላጠ እያነከስን እንጓዝ ነበር” ትላለች ልዋም።

ሴቶች እንደመሆናቸው መጠን ጉዞ ላይ ከወር በላይ ሲቆዩ ከመካከላቸው የወር አበባቸው ሲመጣ የንጽህና መጠበቅያ እየተካፈሉ ይጠቀሙ ነበር፤ ነገር ግን ዝናብ ሲዘንብና ጎርፍ ሲሻገሩ ይቸገሩ ነበር።

መጠለያ ስላልነበራቸው ቀንና ሌሊት የሚዘንበው ዝናብ በላያቸው ላይ ያርፍ ነበር። በዚህ ምክንያት ብዙዎቹ እግሮቻቸውን ቆስሎ፣ በቅዝቃዜ ምክንያት ታምመው እና ጎኖቻቸው ሰቅዟቸውና በጣም ተዳክመው ነበር።

“አንዳንድ ጊዜ ሁኔታዎች ከአቅምህ በላይ ይሆናሉ። በተለይ ጉዞው ህይወትን የሚፈትን ነበር። 12 ወንዞችን ስንሻገር ተደናቅፈው ጥፍራቸው የተቆረጠ፣ ጭናቸው የተላላጠ፣ እግሮቻቸው ውሃ የቋጠሩ፣ ሰውነታቸውም የሚያሳክካቸው እህቶች ነበሩን። እኔ ራሴ እበጥ ወጥቶብኝ ተሠቃይቻለሁ። ጭቃና እንዲሁም ዝናብና ጎርፍ ስላስቸገረን ‘አምላኬ ሆይ አንተው ጠብቀን’ እያልን እንሄድ ነበር” በማለት አስከፊውን ሁኔታ ትገልጻለች።

ከ16 ቀን የእግር ጉዞ በኋላ የኬንያ ኔሮ ከተማ ደርሰው በትናንሽ መኪኖች ወደ ናይሮቢ ገቡ። ኬንያ ለ4 ቀናት ከቆዩ በኋላ እንደገና ወደ ኡጋንዳ አቀኑ።

ጉዞው በመኪና ቢሆንም ከረሃብና ከጥም ግን አልተገላገሉም። ሹፌሩ አዝኖ ሩዝ፣ ኮካና ዳቦ ሰጣቸው። በመጨረሻም ከሌሎች 17 ሰዎች ጋር ካምፓላ ደረሱ።

ከዚህ ፈታኝ ሁኔታ በኋላ ልዋም ጤንነቷን እየተከታተለች ቁስሏን እያስታመመች ትገኛለች።

እሷና አብረዋት የነበሩት በሰላም ቢገቡም የተወሰኑ ወጣቶችን በጎርፍ፣ በውሃ ጥም እና በረሃብ ምክንያት መንገድ ላይ እንደተዋቸው፣ አንዳንድ ቤተሰቦችም የልጆቻቸውን ደህንነት ባለማወቃቸው ከባድ ጭንቀት ውስጥ እንደሚገኙ እንዲሁም ጉዞው ለወንድም ለሴትም በጣም ፈታኝ መሆኑን ትናግራለች።