የመቀለ ከተማ

ከ 2 ሰአት በፊት

በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ የሚገኙ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች መምህራን የ17 ወራት ውዝፍ ደመወዝ ስላልተከፈላቸው የስራ ማቆም አድማ ከመቱ ሶስት ሳምንታት ተቆጠሩ።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ዶ/ር ኪሮስ ጉኡሽ በበኩላቸው በስራ ማቆም አድማ ላይ የተሳተፉ መምህራን ወደ ስራ ገበታቸው እንዲመለሱ አሳስበዋል።

የመምህራኑን አድማ ተከትሎ በ33 ገደማ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሂደቱ ተስተጓጉሏል። በከተማዋ አራት ክፍለ ከተሞች ገደማ ትምህርት ሙሉ በሙሉ መቆሙን የቢቢሲ ምንጮች ገልጸዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው መምህራን የ17 ወራት ውዝፍ ደመወዝ ስላልተከፈላቸው “ለከፍተኛ የኢኮኖሚ ፈተና” መጋለጣቸውን ያስረዳሉ።

አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ መምህር ባለፈው መስከረም ወር ከዚሁ የደመወዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ ከክልሉ ኃላፊዎች ጋር ስብሰባዎች መደረጋቸውን አስታውሰዋል።

መምህሩ አክለውም፤ “መስከረም ወር ከክፍለ ከተማ ወረዳ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች እስከ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በተካሄደው ስብሰባ ተስፋ ሰጪ ነገሮች ነበሩ” ሲሉ ከመስከረሙ ስብሰባ በኋላ ደመወዙ ይከፈላል የሚል እምነት እንደነበራቸው ገልጸዋል።

“ጥያቄያችንን ስርዓት ባለው መንገድ ስናቀርብ ቆይተናል [ነገር ግን] ተጨባጭ መልስ የለም” የሚሉት መምህሩ፤ “ከደደቢት ማይክሮፋይናንስ፥ መብራት ኃይል የሚነሱ ጥያቄዎች ግን የአስተማሪውን ህይወት እየፈተኑት ነው” ሲሊ የከተማዋን መምህራን አጣብቂኝ አብራርተዋል።

“ያለን አማራጭ ፈልሶ መሄድ ስለሆነ ነው ወደ አድማ የገባነው” ሲሉም አድማ የመቱበትን ምክንያት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የመምህራን ደመወዝ ወትሮም የማያወላዳ መሆኑን የገለጹ አንድ ሌላ መምህር በበኩላቸው፤ “መጨረሻ ላይ ትዕግስቱ አልቆ በኑሮ ውድነት፣ የቤት ኪራይ እና በየጊዜው የሚቀያየረው ገበያ ሊሸከመው አልቻለም። ታሞ መታከም የማይችልበት፣ ልጆቹን በአግባቡ ማሳደግ የማይችልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ ነው ወደ አድማ የገባው”ሲሉ ለቢቢሲ በምሬት ተናግረዋል።

መምህራኑ ባለፉት ዓመታት እንደ ደደቢት ማይክሮ ፋይናንስ ካሉ መንግስታዊ አበዳሪ ተቋማት የወሰዱትን ብድር ለመከፈል እጅ አጥሯቸዋል።

የቤት ኪራይ ውዝፍ ክፍያ እንዳለባቸው የሚያነሱት መምህራኑ ውዝፍ ደመወዛቸው ቢያንስ ቀስ በቀስ እንዲከፈላቸው በመማጸን ላይ ናቸው።

ተማጽኗቸው ጆሮ የተነፈገው አንዳንድ መምህራን ፊታቸውን ወደ ሌሎች የሙያ ዘርፎች እያዞሩ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል። አንድ መምህር “ሁኔታዎች አስገድደውት የስራ ዘርፍ የቀየረ፣ መንገድ ዳር ንግድ የጀመረ፣ የጉልበት ስራ የሚሰራ አስተማሪ አ። ምክንያቱም በዚህ ደመወዝ ኑሮ መግፋት ባለመቻሉ ብዙ ተስፋ የሚቆርጥበት ደረጃ ላይ ደርሷል” ሲሉ ሁኔታውን አስረድተዋል።

አንድ ሌላ መምህር በበኩላቸው፤ “ከዕህል መጋዘኖች ከቤተሰብ የተበደርነው ብድር ለመክፈል ደመወዙ አይበቃም። ይህንን መክፈል የምንችለበት መንገድ ቢፈጠር ሞራላችን ላይ እየደረሰ ያለው ጫና እቀንስልን ነበር። አሁን ግን የሚያማርር፣ የሚያዝን አስተማሪ ነው እየተፈጠረ ያለው። በዚህም ተማሪ እና ህብረተሰቡ ናቸው የሚጎዱት” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በጉዳዩ ላይ የሚመለከታቸውን የትግራይ ክልል ባለስልጣናት ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልሰመረም። ይሁን እንጂ የትግራይ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ከፌደራል መንግስት በጀት ባለመላኩ ምክንያት ባጋጠመ የ300 ሚሊዮን ብር የበጀት ጉድለት የሰራተኞችን ውዝፍ መወዝ መክፍል አለመቻሉን አስታውቋል።

የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ኪሮስ በበኩላቸው የስራ ማቆም አድማው የመቱት መምህራን ወደ ስራ ገበታቸው መመለስ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ዶ/ር ኪሮስ፤ “ጥያቄው ተገቢ ነው ጥያቄያችሁን ቀጥሉበት። ግን ደግሞ ‘ስራ አቁሜ ነው የምጠይቀው’ ከተባለ የምትጎዳው ትግራይ ናት፥ የደረሰብንን ጉዳት የማይበቃ ሆኖ ህጻናት ላይ ተጨማሪ ጥፋት እና ጉዳት ልንፈጽም አይገባም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናገረዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ችግሩን ለመቅረፍ ከፌደራል መንግስት ጋር ለመነጋገር ጥረት እያደረገ እንደሆነ መምህራኑ ተረድተው ወደ ስራ ገበታቸው እንዲመለሱ ዶ/ር ኪሮስ ጠይቀዋል።

የትግራይ ቴሌቪዥን የክልሉን የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ምህረት በየነን በመጥቀስ ለመጨረሻ ጊዜ ከፌደራል መንግስት በጀት የተላከው ከአራት ዓመታት በፊት መሆኑን ዘግቧል። ይህን ተከትሎም የሰራተኞችን ደመወዝ ለመክፈት ከፌደራል መንግስት ብድር መጠየቁንም በክልሉ ቴሌቪዥን ዘገባ ተጠቅሷል።