December 28, 2023 – Getachew Shiferaw 

በኦሮሞ ብልፅግና ፍላጎት ብቻ ነው የምንለው በምክንያት ነው!

ከትህነግ/ህወሓት ጋር ሆኖ ዋግኸምራና አካባቢው ላይ ጥቃት ሲፈፅም የነበረ ቡድን ስምምነት መፈራረሙ ተሰምቷል። ይህ ቡድን ከየት መጣ ብለው የሚገረሙ ሰዎች ይኖራሉ። እነ ብርሃኑ ጁላና ጌታቸው ጉዲና ሲሰሩት የከረሙትን ለማመን ነው የሚከብደው።

ከአንድ አመት በፊት ጎንደር ኤርፖርት ላይ ከፍተኛ የቅማንት ኮሚቴ አመራር ይያዛል። ሰውየው በግል ሳይሆን በእነ ብርሃኑ ጁላ ጋባዥነት ነበር ወደ አዲስ አበባ የሚሄደው። በመከላከያ በግልፅ ደብዳቤ ፅፈው፣ ቀጥታ ሽፋን ሰጥተው እንዳይወስዱት ቡድኑ አልታረቀም። ከመከላከያ ጋር ጦርነት ላይ ነበር። ስለሆነም ባላቸው ትስስር ሊያግዙት ሲሞክሩ በአካባቢው ሰው ጥቆማ ተያዘ። ጥናት ሲደረግ ከዚህ ሰው በፊት የሄዱት ጦር ኃይሎች ግቢ እየተመላለሱ ነው የሚውሉት። በዚህ መሰረት አማራው ላይ የተደራጁ ቡድኖችን በሙሉ ወደ አዲስ አበባ ወስደው ያነጋግሯቸዋል። የሰሞኑ ስምምነት ላይ መከላከያ በማያገባው አደራዳሪ የተባለው አማራውን የሚወጉትን ወደ አዲስ አበባ ወስዶ የእነ ሽመልስ አብዲሳ ቡድን እንዲያደራጅ ስላደረገ ነው። የትኛውም አካል ስብሰባ በማይፈቀድለት ሁኔታ እነዚህ ቡድኖች ናዝሬትና አዲስ አበባ መግለጫ ሲሰጡ ነው የከረሙት።

ነባራዊ ሁኔታው ከሆነ ይህ ቡድን የሰቆጣ ወጣቶችም አንይህ የሚሉት ነው። ይህ ነው የሚባል አቅም የለውም። የኦሮሞ ብልፅግና ስለሚፈልገው ብቻ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራር ጋር ሲደራደር ሰንብቷል። በመላ አማራ ክልል የናጣቸውን ፋኖ ደግሞ በመንደር ሽማግሌ “እጅ ስጥ” ይሉታል።

ነባራዊ ሁኔታው ፋኖ መከላከያ ሲቆረጥ ጭምር ያዳነው፣ አብሮት የደማ ኃይል ነው። የትናንቱ ቡድን ደግሞ ከትህነግ ጋር ሆኖ የመታው ኃይል ነው። የኦሮሞ ብልፅግና ፍላጎት ስለሆነ ብቻ ህዝቡ ላይ የሌላ ኃይል ፍላጎት ይዞ የመጣው ጋር መከላከያ አደራዳሪ ሲሆን ፋኖ ላይ ደግሞ እየሆነ ያለው ግልፅ ነው!

የአማራ ክልል ካድሬ የሚሰራው በነባራዊ እውነታው አይደለም። አማራ ክልል ላይ “ሰላም” ወዘተ ሲባል በኦሮሞ ብልፅግና ፍላጎት ብቻ ስለመሆኑ የሰሞኑ ስምምነትና ፋኖን በሰፈር ሽምግልና እጅ ስጥ የሚሉበት ጥሩ ማስረጃ ነው።

ሙሉ መዋቅሩ ወደ አዲስ አበባ የፈረጠጠው የአማራ ብልፅግና አንድ ቀበሌ ካልያዘ ቡድን ጋር የተደራደረው በነባራዊ እውነታው አይደለም። በኦሮሞ ብልፅግና ፍላጎት ብቻ ነው! ሙሉ መዋቅሩን ያሽመደመደው ፋኖን በተራ ብሽሽቅ “ሰላም እንፍጠር” የሚለው በኦሮሞ ብልፅግና ፍላጎት ነው! አቅም ያለውን “እጅ ስጡ” እያሉ የት እንዳለ የማይታወቅን ቡድን ጊዜ ወስደው የተደራደሩት በኦሮሞ ብልፅግና ፍላጎትና ቀጭን ትዕዛዝ ነው። የኦሮሞ ብልፅግና ከፈለገ የአማራ ክልል ካድሬን በትዕዛዝ ትዳሩን ሊያስፈታው ይችላል።