
29 ታህሳስ 2023, 11:34 EAT
በአውሮፓውያኑ 2022 የተጀመረው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ሦስተኛው የካሌንደር ዓመት ውስጥ ሊገባ ጥቂት ቀናት ቀርተውታል።
ባለፉት ጥቂት ወራት የጦርነቱ ግንባሮች ብዙም አልተቀየሩም። ነገር ግን ከቀናት በኋላ በሚገባው 2024 የጦርነቱ መልክ ሊቀየር ይችላል?
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪ በጸደይ ወራት ያካሄዱት የማጥቃት ዘመቻ የተጣለበትን ተስፋ ያልህ ስኬታማ እንዳልሆነ አምነዋል። ሩሲያ አሁንም ድረስ 18 በመቶ የሚሆነውን የዩክሬን ግዛት እንደተቆጣጠረች ነው።
በቀጣዮቹ 12 ወራት ውስጥ ጦርነቱን በተመለከተ ምን አይነት ክስተቶች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ሦስት ወታደራዊ ተንታኞችን ጠይቀናል።
“ጦርነቱ ይቀጥላል ነገር ግን መቋጫ የሌለው አይሆንም”
በለንደን ኪንግስ ኮሌጅ የወታደራዊ ግጭቶች ጥናት መምህርት የሆኑ ባርባራ ዛንኬታ ጦርነቱ ለጊዜው ቢቀጥልም መቋጫ የለውም ማለት ግን አይደለም ይላሉ።
በዩክሬን ያለውን ጦርነት ለመቋጨት ያለው ተስፋ አሁንም የጨለመ ነው። ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ቭላድሚር ፑቲን ከወታደራዊ ይልቅ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ ሆኗል።
በጦርነት ግንባሮች ያለው ሁኔታም የሚያስተማምን አይደለም። ዩክሬን በቅርቡ የጀመረችው የመልሶ ማጥቃት ዘመቻም የተቋረጠ ይመስላል። በሩሲያም በኩል ቢሆን ግን ይሄ ነው የሚባል እርምጃ አልታየም። ከመቼውም ጊዜ በላይ በአሁኑ ሰዓት የጦርነቱ ውጤት በጦርነት ግንባሮች ሳይሆን በፖለቲካዊ ውሳኔ ላይ የተንጠለጠለ ሆኗል። ውጤቱ ከጦርነት ግንባሮች ይልቅ በዋሽንግተን እና ብራሰልስ የሚወሰን ይመስላል።
የምዕራቡ ዓለም በ2022 ያሳየው አስደናቂ አንድነት በ2023 የሚወላውል ሆኗል። አሜሪካ ለዩክሬን ልትልክ የነበረው ወታደራዊ ድጋፍ ከዋሽንግተን ማለፍ ቀላል አልሆነለትም። የአውሮፓ ኅብረት ሊያቀርብ የነበረው ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ እጣፋንታም ቢሆን አላስማማ ባለው የሀንጋሪ አቋም ላይ የሚመሰረት ሆኗል።

ምዕራባውያኑ ሀገራት ላይ የሚታየው ማንገራገር የፑቲንን መተማመን ጨምሮታል። በቅርቡ ለህዝብ በቀረበ ወቅት እንዳመላከተው ሩሲያ ለረጅም ጊዜ እዚህ ጦርነት ውስጥ ለመቆየት ዝግጁ ነች።
ይሁንና የአውሮፓ ህብረት ለኪዬቭ እያደረገ ያለው የቀጠለ ድጋፍ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ሙሉ የሆነ ድል እንድትቀናጅ የሚያደርግ አይደለም።
በምዕራባውያኑ በኩል እየታየ ያለው መቀዛቀዝ 2024 ለዩክሬን ይበልጥ አስቸጋሪ ይሆናል።
ጦርነቱ በ2024 በሙሉ የሚቀጥል ቢሆንም እስከመቼውም መቋጫ የማያገኝ አይሆንም። ፑቲንን የሚያስወግድ መፈንቅለ መንግሥት ስጋት ወይም ከጤና ጋር የተያያዘ ችግር የለም። ስለዚህም አሁን ላይ በብቸኝነት የሚታየው መፍትሄ እስካሁን ሁለቱም ሀገራት ትኩረት ያልሰጡት ድርድር ነው።
“በ2024 የጦርነቱ ሂደት የሚወሰነው ዋሽንግተን፣ ብራሰልስ፣ ቴህራን ወይም ቤይጂንግ ነው”
የሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ኢንስቲትዩት የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ማይክል ክለርክ በ2024 የጦርነቱ ሂደት የሚወሰነው በአውደ ውጊያዎች ሳይሆን በዋሽንግተን ወይም ቤይጂንግ ነው ይላሉ።
በ2022 ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችው ወረራ ትልቅ ጦርነት ወደ አህጉረ አውሮፓ እንዲመለስ አድርጓል። በ2023 የታየው የጦርነቱ ሂደት የዘመነ ኢንዱስትሪ ጦርነት መመለሱንም አሳይቷል።
የዘመነ ኢንዱስትሪ የሚባለው አይነት ጦርነት ከፍተኛ የሆነው የኢኮኖሚ ክፍል ወይም ሙሉ በሙሉ ኢኮኖሚው ለጦር መሳሪያዎች ምርት ቅድሚያ የሚሰጥበት ነው። ከ2021 ወዲህ የሩሲያ የመከላከያ በጀት በሶስት እጥፍ አድጓል። በቀጣዩ ዓመት ደግሞ ከመንግሥት ውጪ ውስጥ 30 በመቶውን ይወስዳል።
ይህም ካለፈው ክፍለ ዘመን አጋማሽ አንስቶ በአውሮፓ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በዩክሬን ያለውን ጦርነት ረጅም ያደርገዋል። መጪው ዓመት ሩሲያ እና የጦር መሳርያ አቅራቢዎቿ ወይም ዩክሬን እና ደጋፊዎቿ ምዕራባውያን ይህ የዘመነ ኢንዱስትሪ ጦርነት የሚጠይቀውን ከፍተኛ ፍላጎት ለማሟላት የሚችሉ መሆን አለመሆናቸው የሚፈተንበት ነው።
በጦርነት ግንባሮች ዩክሬን ያላት ተስፋ ተሟጧል ማለት ስህተት ይሆናል። ነገር ግን ሁለቱም ወገኖች ትርጉም ያለው ለውጥ በማያመጣ ጦርነት ውስጥ በመቆየት አጋጣሚውን ሲያገኙ ስልታዊ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል አቅም አላቸው።
የሩሲያ ኃይሎች ቢያንስ የዶንቦስ ግዛትን በሙሉ ለመያዝ በማሰብ የጦርነት ግንባሩን ወደ ፊት ለመግፋት መሞከራቸው አይቀርም። ዩክሬን በምዕራባዊ የጥቁር ባህር አካባቢ እና ወሳኝ በሆነው የቦስፎረስ የንግድ ኮሪደር ላይ ያላትን ቁጥጥር በማጠናከር ረገድ ያገኘችውን ስኬት ትጠቀምበታለች።

በተጨማሪም የምትፈጽማቸውን ድንገተኛ ወታደራዊ ጥቃቶች በመጨመር ሩሲያ በወረራ የያዘቻቸው አንዳንድ ቦታዎች ላይ ያላትን ቁጥጥር ልትፈትን ትችላለች።
2024 ኪዬቭ እና ሞስኮ ራሳቸውን የሚያጠናክሩበት ዓመት ይመስላል። ሩሲያ ስልታዊ የሆነ ጥቃት ለመፈጸም የሚያስች መሳሪያ እና የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት አለባት። ይህ እጥረት ቀረበ ቢባል ከ2025 በፊት አይቀረፍም።
ዩክሬን ደግሞ ነጻ የሚያወጣትን ጥቃት በተከታታይ ለመፈጸም በሚያስችል ሁኔታ ጥንካሬዋን እያሳደገች ጦርነቱ ውስጥ ለመቀጠል የምዕራባውያን የፋይናንስ እና ወታደራዊ ድጋፍ ያስፈልጋታል።
በ2024 የጦርነቱ ሂደት የሚወሰነው አስከፊ ጦርነት ባስተናገዱት ግንባሮች ይልቅ በሞስኮ፣ በኪዬቭ፣ በዋሽንግተን፣ በብራሰልስ፣ በቤጂንግ፣ ቴህራን እና በፒዮንግያንግ ነው።
“የአሜሪካ የጦር ጀቶች ልዩነት ሊፈጥሩ ይችላሉ”
በአውሮፓ የአሜሪካ ጦር የቀድሞ አዣዥ የሆኑት ቤን ሀጅስ በዚህ ጦርነት የአሜሪካ የጦር ጀቶች ልዩነት ሊፈጥሩ ይችላሉ ይላሉ።
ሩሲያ በአሁኑ ወቅት ዩክሬንን በጦር ሜዳዎች ለማንበርከክ ወሳኝ አቅም ስለሌላት አሁን የያዘችውን አስጠብቃ ለመቆየት የምትችለውን ታደርጋለች። ሩሲያ፤ ምዕራባውያኑ ዩክሬንን እየደገፉ ለመቀጠል ያላቸው ፍላጎት እንደማይኖራቸው ተስፋ እያደረገች ጊዜውን መከላከያዋን ለማጠናከር ትጠቀምበታለች።
ነገር ግን ዩክሬን አትገታም። ህልውናዋን ለማስጠበቅ ጦርነት ላይ ያለችው ዩክሬን እርምጃዋን ካቆመች ሩሲያ ምን እንደምታደርግ ትረዳለች። አሜሪካ ለዩክሬን ስለምታደርገው ድጋፍ ውሳኔ ለማሳለፍ እየተዳከመች ነው ብለው የሚያስቡት አውሮፓውያን ሀገራት የሚሰጠው እርዳታን በተመለከተ ንግግር እያደረጉ ነው።
ይሁንና በአዲሱ ዓመት መጀመሪያ ላይ አሜሪካ ስልታዊ ጥንካሬዋን መልሳ በማግኘት ኮንግረሱ ታህሳስ ወር ላይ እንዲዘገይ ያደረገውን ወታደራዊ ድጋፍ ለመላክ ይወስናል ብዬ እጠብቃለሁ። ይሄንን ተከትሎም በተከታዮቹ ወራት ዩክሬን አራት እርምጃዎችን ትወስዳለች የሚል ግምት አለኝ።
ቀዳሚው እርምጃ የሚሆነው፤ ለወራት ውጊያ ውስጥ በመቆየታቸው የተዳከሙትን የጦርነት ክፍሎች ማጠናከር ነው። እንደ አዲስ ጥቃት ለመክፈት ይህ እርምጃ አስፈላጊ ነው።

በሀገር ውስጥ የሚገኘውን የሰው ኃይል እስከመጨረሻው ለመጠቀም የምልመላ ስርዓቷን ማሻሻል ሌላኛው ተጠባቂ እርምጃ ነው።
የመሳሪያ እና የተተኳሽ ምርቷን መጨመርም ዩክሬን ልትወስድ የምትችለው እርምጃ ነው። ዩክሬን፤ ጠንካራ የሆነውን የሩሲያ የኤኬክትሮኒክ ጦርነት አቅም ለመገዳደር አቅሟን ማሳደግም አለባት።
በክረምቱ ወራት መጀመሪያ ላይ ዩክሬን አሜሪካ ሰራሾቹን ኤፍ-16 የጦር ጄቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ታገኛለች። ዩክሬን እነዚህ ጄቶች ማገኘች የሩሲያን አውሮፕላኖች የመከላከል እንዲሁም የራሷን የአየር የመከላከል አቅም እንደሚያሳድግ ተስፋ አላት።
ዩክሬናውያን በተለይ ከፍተኛ የጦር መሳሪያ ተተኳሾች እና የረጅም ርቀት መሳሪያዎች አቅርቦታቸውን ገደብ ያለበት ነው። ነገር ግን የሩሲያ ወታደሮች አቋም በከፋ ሁኔታ ውስጥ ነው። ጦርነት ፍላጎት እና የሎጂስቲክስ አቅርቦት የሚፈተንበት ነው። የሩሲያ የሎጂስቲክስ ስርዓት ደካማ እና በዩክሬን የማያቋርጥ ጫና ውስጥ ያለ ነው።