ጋዛ

29 ታህሳስ 2023, 08:23 EAT

የእስራኤል ሠራዊት ወደ ስደተኛ መጠለያዎች መጠጋቱን ተከትሎ 150 ሺ የሚሆኑ ፍልስጤማዊያን ከማዕከላዊ ጋዛ አካባቢዎች ተገደው እየተሰደዱ መሆኑን የመንግሥታቱ ድርጅት አስታወቀ።

የዓይን እማኞችና የሀማስ ወታደራዊ ክንፍ ታንኮች በቡሪጅ መጠለያ ጣቢያ ምስራቃዊ ክፍል መድረሳቸውን ተናግረዋል።

የእስራኤል ጦር በቅርቡ የምድር ጥቃቱን እያስፋፋ የቡሪጅ እና በአቅራቢያው የሚገኙ ኑሱሪያት እና ማጋዚ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎችን ዒላማ አድርጓል።

በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚንስቴር እንዳለው የእስራኤል ጦር ሐሙስ ዕለት በፈጸማቸው የቦንብ ድብደባዎች በርካቶች ተገድለዋል።

የእስራኤል እና ሐማስ ጦርነት መስከረም 26 በደቡባዊ እስራኤል የሐማስን ድንገተኛ ድንበር ተሻጋሪ ጥቃት ተከትሎ መጀመሩ ይታወቃል።

በጥቃቱ 1,200 ሰዎች በአብዛኛው ንጹሃን ሲገደሉ፤ 240 ሰዎች ደግሞ ታግተው ወደ ጋዛ ተወስደዋል።

እንደ የገዛ ጤና ሚንስቴር መረጃ ለ11 ሳምንታት በዘለቀው ውጊያ 21,300 ሰዎች በአብዛኛው ህጻናትና ሴቶች በጋዛ ተገድለዋል።

የእስራኤል ጦር የቡሪጅ እና ኑሱሪያት የስደተኛ መጠለያዎችን ጨምሮ ነዋሪዎች ማዕከላዊ ጋዛን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

ጦሩ 90 ሺህ ነዋሪዎችና 61 ሺህ ተፈናቃዮች ወደ ደቡብ ደሪ አል-ባላ ከተማ እንዲያመሩ አሳስቧል።

ይሁን እንጂ ተመድ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮችን ያስጠለለው ደሪ አል-ባላ በመጨናነቁ በማዕከላዊ ጋዛ ያሉት ሰዎች መሄጃ የላቸውም ብሏል።

የተመድ የእርዳታ ኤጄንሲ የጋዛ ዳይሬክተር ቶም ዋይት በርካታ ሰዎች ከደቡባዊ የጋዛ ከተማ ራፋ እየተገፉ እየወጡ ነው ብለዋል።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል አል-ቡርጂ ከተማ “የሐማስ ዋነኛ የሽብር ማዕከል” ናት ይላል።

የእስራኤል ጦር ቃል አቀባዩ ሪር አድሚራል ዳንኤል ሃጋሪ በአካባቢው ጦሩ ለሦስተኛ ቀን እየተዋጋ መሆኑን ጠቅሰው፤ “በርካታ ሽብርተኞችን እየደመሰስንና የሽብር መሠረተ ልማቶችን እያወደምን ነው” ብለዋል።

ነዋሪዎች ለሮይተርስ የዜና ወኪል የእስራኤል ወታደሮች በርካቶች ወደሚኖሩበት አካባቢ በሁለት አቅጣጫዎች እየተቃረቡ መሆኑን ተናግረዋል።