የቡርኪና ፋሶ ወታደራዊ መሪ ካፒቴን ኢብራሂም ትራኦሬ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር
የምስሉ መግለጫ,የቡርኪና ፋሶ ወታደራዊ መሪ ካፒቴን ኢብራሂም ትራኦሬ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር

29 ታህሳስ 2023, 10:50 EAT

ሩሲያ ከ30 ዓመታት በፊት ዘግታ የነበረውን የቡርኪና ፋሶ ኤምባሲዋን ዳግም ከፈተች።

ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ቡርኪና ፋሶ ከቅኝ ገዢዋ ፈረንሳይ ጋር የጠበቀ ግንኙነት የነበራት ቢሆንም በአገሪቱ እአአ 2022 ላይ መፈንቅለ መንግሥት ከተደረገ በኋላ ፊቷን ወደ ሩሲያ አዙራለች።

በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን የያዘው ጁንታ የፈረንሳይ ዲፕሎማቶችን ከአገር አበሯል እንዲሁም ፈረንሳይ በበኩርኪና ፋሶ የነበራትን ወታደራዊ ጦር ሰፈር ዘግቶ ከሩሲያ ጋር ያለውን ግንኙነት እያጠናከረ ነው።

ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሐምሌ 2015 ዓ.ም. በሴንት ፒተርስበርግ ከተማ በተካሄደው የሩሲያ-አፍሪካ ስብሰባ ላይ ሞስኮ ኤምባሲዋን ዳግም በኦጋዱጉ እንደምትከፍት ተናግረው ነበር።

ሞስኮ ከቀዝቃዛው ጦርነት እና ከሶቪዬት ሕብረት መፍረስ በኋላ እአአ 1992 ላይ በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ያላትን እንቅስቃሴዋን በመቀነስ ኤምባሲዋን ዘግታለች።

የሩሲያ ዜና ወኪል ታስ እንደዘገበው በቡርኪና ፋሶ መዲና ኦጋዱጉ በተካሄደ ስነ-ስርዓት የሩሲያ ኤምባሲ በይፋ ተከፍቷል።

ፑቲን ለቡርኪና ፋሶ አምባሳደር እስኪሾሙ ድረስ በአይቮሪ ኮስት የሩሲያ አምባሳደር የሆኑት ኤልክሲ ሳለተይኮቭ ሚሽኑን ይመሩታል ሲል ኤኤፍፒ ዘግቧል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ፑቲን አገራቸው በአፍሪካ የነበራትን ተጽእኖ ፈጣሪነት መልሶ ለማግኘት ትልቅ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።

በመፈንቅ መንግሥት ስልጣን የተቆጣጠረው የቡርኪና ፋሶ መንግሥት ወታደራዊ አቅሙን ለማጠናከር ፊቱን ወደ ሞስኮ አዙሯል።

የአገሪቱ መከላከያ ሚንስትር ኮሎኔል ካሱም ኩሊባሊ ከአንድ ወር በፊት ከሩሲያ አቻቸው ጋር ተገናኝተው ንግግር ካደረጉ በኋላ “ንግግራችን ተግባሯዊ የሚሆንበት ደረጃ ላይ ደርሷል” ብለው ነበር።

ቡርኪና ፋሶ እንዲሁም ጎረቤት አገራት ኒጀር እና ማሊ እስላማዊ ጽንፈኛ ኃይሎችን እየተዋጉ ይገኛሉ።

ማሊ የፈረንሳይ ወታደሮችን ከአገሯ አባራ እስለማዊ ቡድኖችን ለመዋጋት የሩሲያውን ቅጠረኛ ተዋጊ ቡድን ቫግነር ጋብዛለች።

ቡርኪና ፋሶ ከወታደራዊ ድጋፍ በተጨማሪ የኃይል አቅርቦቷን ከፍ ለማድረግ ከሩሲያ ጋር የኒውክለር ኃይል ማመንጫ ለመገንባት ከስምምነት ደርሳለች።

ባለፈው ወር በቡርኪና ፋሶ የተከሰተውን የደንጊ እና ቺኩንጉኒያ ወረርሽኝ ለማከም ሩሲያ ሐኪሞችን ልካ ነበር።