
29 ታህሳስ 2023, 08:13 EAT
የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሜይን ግዛት በቀጣዩ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተሳታፊ እንዳይሆኑ ታገዱ።
ትራምፕ ከጥቂት ቀናት በፊት በኮሎራዶ ግዛት በተመሳሳይ ከፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በግዛቱ ፍርድ ቤት መታገዳቸው ይታወሳል።
የሜይን ግዛት ከፍተኛ የምርጫ ኃላፊ የሆኑት ሼና ቤልዎስ የቀድሞ ፕሬዝዳንት በካፒሎል ሂል አመጽ ላይ ተሳትፎ ስለነበራቸው የምርጫ ዕጩ ሆነው መቅረብ አይችሉም በሚል መታገዳቸውን ይፋ አድርገዋል።
ትራምፕ ላይ የተላለፈው ባለ 34 ገጽ የእግድ ትዕዛዝ “በአመጽ የተሳተፈ” ስልጣን መያዝ እንደማይችል የአገሪቱን ሕገ መንግሥት ይጠቅሳል።
ከፍተኛ የምርጫ ኃላፊዋ እና የሜይን ግዛት ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ቤልዎስ ከካፒቶል ሂል አመጽ በፊት ቀደመው በነበሩት ወራት ትራምፕ የምርጫ ሂደቱን የተመለከቱ ሐሰተኛ መረጃዎችን ሲያስተጋቡ ቆይተው ደጋፊዎቻቸው ወደ ካፒቶል ሂል እንደሚያመሩ አድርገዋል ብለዋል።
ከጥቂት ቀናት በፊት ትራምፕን በኮሎራዶ ያገዱት የግዛቷ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኖች እንዲሁ የእግዱ ምክንያት ትራምፕ ከሦስት ዓመታት በፊት በተከሰተው በካፒቶል ሂል አመጽ ተሳትፈዋል የሚል ነው።
ይህ የሁለቱ ግዛቶች ውሳኔ በ2024 የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዕጩ ሆኖ ለመቅረብ ያቀዱትን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሙሉ በሙሉ ከተወዳዳሪነት የሚያግድ ባይሆንም በሁለቱ ግዛቶች እንዳይወዳደሩ በማገድ ለተቀናቃኞቻቸው የተሻለ የማሸነፍ ዕድልን ይሰጣል።
- አማራ ክልል፡ጥሰቶችን ያዳፈነው እና የበርካቶችን የእንጀራ ገመድ የበጠሰው የኢንተርኔት መቋረጥ29 ታህሳስ 2023
- ነፍሰጡር እናቶችን እና ጽንሳቸውን የሚያጠቃው “ድብቁ የአኒሚያ ወረርሽኝ”29 ታህሳስ 2023
- ለ17 ወራት ባልተከፈለ ውዝፍ ደመወዝ ምክንያት የቀጠለው የመቀለ መምህራን የስራ ማቆም አድማ28 ታህሳስ 2023
ቤልዎስ ውሳኔያቸውን በተመለከተ ለቢቢሲ ሲናገሩ “ከዚህ ቀደም ፕሬዝዳንታዊ ዕጩን ከምርጫ ያገደ የግዛት ሥራ አስፈጻሚ እንደሌላ እገነዘባለሁ። በተጨማሪም ከዚህ ቀደም በአመጽ ተግባር ላይ የተሳተፈ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ እንደሌላም አውቃለሁ” ካሉ በኋላ የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ትራምፕን በመላ አገሪቱ በመጪው ምርጫ እንዳይሳተፉ እግዱን ያሰፋል የሚል እምነት አለኝ ብለዋል።
ይህን የሜይን ግዛት ውሳኔን የትራምፕ ምርጫ ቅስቀሳ ቡድን የሥራ አስፈጻሚዋ ውሳኔ ለጆ ባይደን ፓርቲ ያደላ ነው ሲል አጥብቆ ተችቷል።
የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ቃል አቀባይ ስቲቨን ቼኡንግ ውሳኔውን በሜይን ግዛት ይግባኝ እንደሚሉ አስታውቀዋል።
የትራምፕ ጠበቆች ከዚህ ቀደም በኮሎራዶ ፍርድ ቤት የተላለፈውን ውሳኔ አጥብቀው ተችተው፣ ጉዳዩን ወደ ፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንወስደዋለን ብለው ነበር።
ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ትራምፕን በኒው ሃምፕሻየር፣ በሚኒሶታ እንዲሁም ሚሺጋን ግዛቶች በምርጫ እንዳይወዳደሩ ለማገድ የተደረጉ ጥረቶች ሳይሰምሩ ቀርተዋል።
አንዳንድ የሕግ ተንታኞች ሜይን እና ኮሎራዶ ግዛቶች የቀድሞ ፕሬዝዳንት በምርጫ እንዳይሳተፉ ቢያግዱም ውሳኔያቸው በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የመጽነቱ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው ይላሉ።
የቀደሞ የፌደራል ዐቃቤ ሕግ ጆ ሞሬኖ ለቢቢሲ ሲናገሩ የግዛቶቹ ውሳኔ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚጸናበት ምንም አይነት ሕጋዊ መሠረት የለም ይላሉ።
ወግ አጥባቂ ዳኞች ቁጥር ትልቅ ድርሻ ባለበት ጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ ዳኞች ለትራምፕ ይፈርዳሉ የሚል ግምት እንዳላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።