
29 ታህሳስ 2023, 14:18 EAT
የሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርተፊሻል ኢንተለጀንስ) ቴክኖሎጂ ውጤቶች እየመጠቁ እና እየተበራከቱ ናቸው።
የሰው ልጆችን ሥራ አጥ ሊያደርጉ ይችላሉ የሚሉ ስጋቶችን እስከሚፈጥሩ ድረስ ያልገቡበት ዘርፍ ጥቂት ነው።
በቅርቡ ደግሞ ኤሌክትሮኒክ አፍንጫዎች (e-nose sensors) መበልጸጋቸው ተሰምቷል።
ቴክኖሎጂው የሰው ልጅ አፍንጫን እና የማሽተት ችሎታን የተካ ነው ተብሎለታል።
አፍንጫችን ወደ 400 የሚጠጉ የመዓዛ ተቀባዮች ያሉት ሲሆን፣ ይህም ወደ አንድ ትሪሊዮን የሚጠጉ የተለያዩ ጠረኖችን መለየት ይችላል።
ይህንን አስደናቂ ተፈጥሯዊ ችሎታ በሳይንሳዊ መሣሪያ መተካት ቀላል ባይሆንም፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) አማካኝነት ኤሌክትሮኒክ አነፍናፊ አፍንጫዎች ተሰርተዋል።
እነዚህ አፍንጫዎች የአንድን ነገር ሽታ መለየት እና ማሽተት የሚችሉ ሲሆን፣ በፍጥነታቸው እና በትክክለኝነታቸው የማሽተት አቅምን አሻሽለዋል ተብሏል።
የፈጠራው አስተዋዋቂዎች እነዚህ አነፍናፊዎች የምግብ ደኅንነትን ያሻሽላሉ ብለዋል።
‘ሴንሲፊ’ የተባለውን ኤሌክትሮኒክ አፍንጫ ካበለጸጉት አንዱ እና በእስራኤል በቤን ጎሪዮን ዩኒቨርሲቲ የኬሚስትሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ራዝ ጀሊንክ እንደሚሉት፣ ሳልሞኔላ እና ኢ ኮሊ የተባሉ ገዳይ የሆኑ እና የተለመዱ ምግብ ወለድ ባክቴሪያዎች የራሳቸው ኤሌክትሪካዊ ባህርይ እና ምልክት (Signal) አላቸው።
ታዲያ እነዚህ በካርቦን ቅንጣጢቶች (ፓርቲክልስ) የተሸፈኑ ኤሌክትሮድስን የያዙት እና በእስራኤል ኩባንያ የተሠሩት ኤሌክትሮኒክ አፍንጫዎች፣ በባክቴሪያ አማካኝነት የተፈጠሩ ወይም በትነት መልክ የሚወጡ ጋዞችን ጠረን ይለያሉ።
- ሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) የሰው ልጆች መጥፊያ ይሆናል?26 ሰኔ 2023
- የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ምንነት አጭር ማብራሪያ20 ሀምሌ 2023
- ከቀዶ ሕክምና እስከ ሕዋ አሰሳ፡ አስደናቂው ሮቦቲክስ23 ህዳር 2022
የተለያዩ የባክቴሪያ ዝርያዎች የተለያየ የትነት አሻራ ያላቸው ሲሆን፣ ይህም በሴንሲፊ መሣሪያው የተለያየ የኤሌክትሮኒክ ምልክት (ሲግናል) ይፈጥራል። ከዚያም በሰው ሰራሽ አስተውሎት ሶፍትዌር ሥርዓት ከተመዘገበ በኋላ ተጠቃሚዎቹን ያሳውቃል።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ይፋ የተደረገው ሴንሲፊ፣ በተለይ በምግብ ኢንዱስትሪዎች የሚከሰቱ በሽታዎችን ለማስቀረት የሚደረገውን ጥረት ያሳድጋል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል።
የፈጠራ ሥራው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሞዲ ፕሌድ፣ ምግብ አምራቾች በአንዳንድ ሁኔታዎች ለምርመራ የምግብ ናሙናዎችን ወደ ቤተ ሙከራ መላክ እና ውጤቱ እስከሚመጣም ለብዙ ቀናት መጠበቅ ይጠበቅባቸው እንደነበር አውስተዋል።
ሆኖም ሴነሲፊ የተሰኘው ሰው ሰራሽ አፍንጫ እዚያው በምግብ ተቋማቱ ውስጥ ጥቅም ላይ መዋል እንደሚችል እና ውጤቱንም ከአንድ ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ እንደሚያሳውቅ ተናግረዋል።
የዚህ አፍንጫ ዋጋ ምን ያህል እንደሆነ ይፋ ያልተደረገ ቢሆንም፣ በዝቅተኛ ዋጋ እንደሚቀረብ ተነግሯል። ኩባንያው አብዛኛውን ገቢውን ለማግኘት ያሰበው ከምዝገባ ክፍያ (ሰብስክሪፕሽን) ነው።
“በምግብ ኢንደስትሪ ውስጥ ጥራት የሚፈተሽበት መንገድ ላለፉት 40 እና 50 ዓመታት ተመሳሳይ ሆኖ ነው የቆየው” የሚሉት ፕሌድ፣ እስካሁን ድረስ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ወደዚህ ዘርፍ አልገባም ነበር” ብለዋል።

የምግብ መመረዝ ዓለም አቀፋዊ ችግር ነው። በአሜሪካ በየዓመቱ ከስድስት ሰዎች አንዱ ወይም 48 ሚሊዮን ሰዎች በምግብ ወለድ በሽታ ይታመማሉ። ከእነዚህ መካከል 128 ሺህ የሚሆኑት ሆስፒታል የሚገቡ ሲሆን 3 ሺህ ሰዎች ይሞታሉ።
በዩናይትድ ኪንግደም ደግሞ በየዓመቱ 2.4 ሚሊዮን የምግብ መመረዝ ክስተቶች የሚመዘገቡ ሲሆን፣ 180 ሰዎች እንደሚሞቱ ይገመታል።
ፕሌድ እንደሚሉት ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ከሥጋ፣ ከዶሮ እና ከዓሳ ምግቦች ደኅንነት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይጠቀሳል። ሆኖም ባለፉት ከአምስት እስከ አስር ዓመታት በአሜሪካ የምግብ ኢንዱስትሪ ውስጥ ትልቁ ገዳይ ‘ሮሜን’ የተባለው ሰላጣ ነው።
የምግብ ገበያው ኢንደስትሪ ላይ የተመሠረተ በሆነ ቁጥር ለበሽታ አምጭ ተህዋስያን ይበልጥ ተጋላጭ ይሆናል።
ይህንን ለማስወገድ ሲባልም ነው መሰል ፈጠራዎች ብቅ ብቅ እያሉ ያሉት።
ኤንቲቲ ዳታ ቢዝነስ ሶሊዩሽን የተባለው የጀርመን ድርጅትም አነፍናፊ አፍንጫውን በቡና እያሰለጠነ ይገኛል።
በአንድ ሙከራ ላይ ባለሙያዎቹ፣ በአነፍናፊዎቹ አጠገብ ወዲያው የተዘጋጀ የቡና ዱቄት በማስቀመጥ ሦስት ቀናትን አሳልፈዋል።
ሰው ሰራሽ አስተውሎቱ የትኛው ጥሩ ቡና፣ መጥፎ ቡና፣ በኮምጣጤ የታሸ ቡና እንዲሁም ቡና አለመኖሩን መለየት ይጠበቅበት ነበር።
“ሽታ ጋዝ ብቻ አይደለም የተለያዩ የጋዞች ውህድ ነው” የሚሉት የድርጅቱ የፈጠራ ሥራ አስኪያጅ አንድሪያ ኮስትርዝ፤ ብዙ ጊዜ የነገሮች ሽታ፣ የበዛ ልዩነት አሊያም በጣም ትንሽ ልዩነት ይኖረዋል ይላሉ።
የኤንቲቲ አነፍናፊዎች በሰው አፍንጫ ቅርፅ ባለ ሦስት አውታር (3ዲ) ተደርገው የተሰሩ ሲሆኑ፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎቱን ቡና እና ሌሎች ምግቦችን በመጠቀም ትኩስ እንዲሁም ጥሩ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን ማወቅ እንዲችሉ እየሰለጠኑ ነው።

ኤንቲቲ የሠራው የኤሌክትሮኒክ አፍንጫ የሚያገለግለው በሽታ አምጭ ተህዋሲያንን ለመለየት ብቻ አይደለም።
ምግቡ ምን ያህል ትኩስ አሊያም የቆየ ነው የሚለውንም ለመለየት ያገልግላል። ይህም ሱፐርማርኬቶች እና ካፍቴሪያዎች የመጠቀሚያ ጊዜው ሳያበቃ የትኛውን መጀመሪያ መሸጥ እንዳለባቸው እንዲያውቁ ይረዳል።
የምግቦቹን ሽታ በማወቅ የምግብ ኢንዱስትሪው ምርቶቹን፣ ማሸጊያውን እንዲሁም ምርት መሰብሰቢያውን እና ማቀነባበሪያ ጊዜውን ለማስተካከል እንደሚጠቅምም ኮስትርዝ ተናግረዋል።
ሆኖም አንዳንድ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ባለሙያዎች አዲስ የተሠራው ኤሌክትሮኒክ አፍንጫ በትክክል ከሠራ፣ የምግብ ድርጅቶች በዋጋው ምክንያት ለመጠቀም ስለማይበረታቱ ብዙ ፈላጊ ላይኖራቸው ይችላል ይላሉ።
ተቀማጭነቱን አሜሪካ ያደረገው የሰው ሠራሽ አውተውሎት ድርጅት ኢንኽሪታንስ ኤአይ መሥራች እና ዋና ዲዛይነር ቪንሴንት ፒተርስ፣ አነስተኛ አነፍናፊዎችን በዓለም ዙሪያ ማሰራጨት የሚታሰብ ከሆነ የንግድ ሥርዓቱ ላይ ምን ዓይነት ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል ሲሉ መክረዋል።
“ይህን ቴክኖሎጂ ሥራ ላይ ማዋል ካለብን ንግድ ይኖራል ወይ? የግብይት ሰንሰለቱ ይተገብረዋል ወይ? ያዋጣል ወይ?” ሲሉም ይጠይቃሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሳንፋራንሲስኮ ተቀማጭነቱን ያደረገው ዶሚኖ ዳታ ላብራቶሪ ውስጥ የኤአይ ባለሙያ የሆነው ክጀል ካርልሰን “ኤሌክትሮኒክ አፍንጫዎች፣ ለሚሰሩበት እያንዳንዱ ሥርዓት ውስብስብ የሆነ መቀየሪያ ያስፈልጋል። ይህም ለአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እንግዳ ለሆነው ኢንዱስትሪ ከባድ ሥራ ነው” ብሏል።
ሆኖም እንዲህ ዓይነት ጥርጣሬዎች አንዳንድ ሥራ ፈጣሪዎችን ከሥራቸው አላደናቀፈም።
በኒውዚላንድ ሴንቲያን ባዮ የተባለ ኩባንያም የነፍሳትን አንቴና በመኮረጅ ሥነ ሕይወታዊ እና ኬሚካላዊ ውህዶችን ውጤትን ለመለየት የሚያስችል ባዮ አነፍናፊ (ባዮ ሴንሰር) ሰርቻለሁ ብሏል።
የድርጅቱ መሥራች እና የቴክኖሎጂ ባለሙያው አንድሪው ክራሊሴክ በዚህ ባዮ ቴክኖሎጂ ምክንያት አነፍናፊ መሣሪያው ከውሻ አፍንጫ በሺዎች እጥፍ የማሽተት አቅም አለው” ብሏል።
ጨምሮም ይህን ባዮሴንሰር ላይ የተሠመረተ ቴክኖሎጂ፣ የምግብ ደኅንነትን እና ጣዕም ለመቆጣጠር፣ የምግብ በሽታ አምጪ ተህዋስያን እና ተዛማች በሽታን ለመለየት እንዲሁም ዘላቂነት ያለውን እርሻ እና የአካባቢ ደኅነንትን ለመቆጣጠር በየትኛውም ቦታ በኢንተርኔት አማካኝነት መጠቀም ይቻላል ብሏል።