አፉአ አሳንቴዋ

30 ታህሳስ 2023, 11:19 EAT

የጋና ሚዲያ ላይ ስሟ የገነነው ጋዜጠኛ፣ የቲቪ ፕሮዲውሰር እና ስራ ፈጣሪ የሆነችው አፉአ አሳንቴዋ፣ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በማንጎራጎር የዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ ስሟን ለማስፈር ጥረት ማድረጓ ተሰማ።

ለ126 ሰዓታት ያለማቋረጥ ከዘፈነች በኋላም፣ በጎርናና ድምጽ የጋናን ባንዲራ ለብሳ በዚህ ጥረት ውስጥ አብረዋት የነበሩትን በሙሉ አመስግናለች።

የ33 ዓመቷ አፉአ አምስት ቀን ዘፍና ስታጠናቅቅ እጅግ ከመድከሟ የተነሳ፣ ዕለቱ ምን አንደሆነ እንኳ ማስታወስ አትችልም ነበር ተብሏል።

ከፈረንጆቹ የገና ዋዜማ ጀምሮ በሌላ ግለሰብ 24 ሰዓት በመዝፈን የተያዘውን ክብረወሰን ለመስበር ጥረት ያደረገች ሲሆን፣ ድካሟ ፍሬ ማፍራቱን ለማወቅ ግን መታገስ ይኖርባታል።

አሳንቴዋ የተካፈለችበትን የሙዚቃ ማራቶን ያዘጋጁት አካላት ለ126 ሰዓታት ከ52 ደቂቃ ያለማቋረጥ ማንጎራጎሯን መስክረዋል።

በጊነስ የዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ መመርያ መሰረት በእያንዳንዱ ሰዓት መካከል አምስት ደቂቃ እረፍት እንድታደርግ ይፈቀድላታል።

አሳንቴዋ በአጠቃላይ በአምስት ሰዓታት ውስጥ ለ20 ደቂቃዎች ብቻ እረፍት አግኝታለች ማለት ነው።

አፋአ አሳንቴዋ በድካም ጎርንኖ በተዘጋ ድምጿ፣ ይህ የሙዚቃ ማራቶን “ለሁሉም ሴቶች ከምቾት ክበባቸው ወጥተው አዳዲስ እድሎችን እንዲሞክሩ ሰበበ መነሳሳት ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። . . . ጠቅላላ ትኩረታቸንን በዚያ ላይ ካደረግን ማሳካታችን አይቀረም” ስትል ተናግራለች።

ከዚህ ቀደም በስራ ፈጠራ እና በቁንጅና ተወዳዳሪነት የምትታወቀው ይህች ወጣት፣ ያካሄደችው የማንጎራጎር ማራቶን በተለይ በገና ዕለት የበርካቶችን ቀልብ ስቦ ነበር።

አሳንቴዋ ስታንጎራጎር ለመታደም መጥተው ከነበሩት ዝነኛ የጋና ድምጻውያን መካከል፣ ስቶንብዎይ፣ ሻታ ዋሌ እና ሳርኮዲ ይገኙበታል።

የአገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳነት የሆኑት ማሃመዱ ባዉሚያ ጨምሮ ዝነኛ የአገሪቱ ተዋንያን እንዲሁም በማሕበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ተገኝተው ነበር።

አሳንቴዋ በአምስቱ ቀናት በጋና በተለያዩ ዘርፎች የተቀነቀኑ 125 ሙዚቃዎችን ማንጎራጎሯም ተገልጿል።

መንፈሳዊ መዝሙሮች፣ እንዲሁም የሀገረሰብ እና ሞቅ ያሉ ሙዚቃዎች ካንጎራጎረቻቸው መካከል ናቸው።

ይህም የአገሪቷን ባህል የማስተዋወቅ አንዱ አካል ተደርጎ ተቆጥሮላታል።

አሳንቴዋ ሙዚቃውን ስትጫወት ከጀርባዋ ዲጄ አብሯት የነበረ ሲሆን፣ ነገር ግን በሙዚቃዎች መካከል የሰላሳ ሰከንድ ወይም ከዚያ ያነሰ አፍታ ብቻ ትወስድ እንደነበር ሁኔታውን የተከታተሉ ተናግረዋል።

አሳንቴዋ ስታንጎራጉር በርካቶች ተገኝተው የነበረ ቢሆንም፣ የታዳሚው ጩኸት እንዳይረብሻት ከመስታወት ጀርባ ቆማ ማንጎራጎሯም ተገልጿል።

ለጊነስ የዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ የሚሰጥ ሙሉ የአምስቱም ቀን እንጉርጉሮዋ የተቀረጸ ሲሆን ምስክሮችም ከሪፖርቱ ጋር ቃላቸውን አካትተዋል።

በዚህ ዓመት የጋና ጎረቤት አገር በሆነችው ናይጄርያ፣ ከ90 ሰዓት በላይ ምግብ በማብሰል የዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ ስሟን ለማስፈር የቻለች ሼፍ ነበረች።