
30 ታህሳስ 2023, 09:02 EAT
ደቡብ አፍሪካ እስራኤል በጋዛ “የዘር ማጥፋት ድርጊቶች እየፈጸመች ነው” ስትል በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ክስ መሰረተች።
የተከፈተው መዝገብ እስራኤል በዘር ማጥፋት ኮንቬንሽን ስር የተቀመጡትን ጥሳለች በሚል መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ችሎት አረጋግጧል።
እስራኤል ይህንን ውንጀላ “መሰረተ ቢስ” በማለት አጥብቃ ተቃውማለች።
የእስራኤል ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር “እስራኤል ደቡብ አፍሪካ ስሟን በደም ልታጠለሸው የምታደርገውን ጥረት አጥብቃ ታወግዛለች” ሲል ተናግሯል።
መቀመጫውን ኔዘርላንድስ ሔግ ያደረገው የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት (ICJ)፣ የተባበሩት መንግሥታት የሕግ አስፈጻሚ አካል ነው።
ይህ ፍርድ ቤት አገራት መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ሲቀርብለት ምርመራ አድርጎ ብይን ይሰጣል፤ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ሕግ ነክ ጉዳዮች ላይ ምክር ይሰጣል።
- “ካሳ ሳይተላለፍልን መሬታችን እየታረሰ ነው” – በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት ከይዞታቸው የሚነሱ የሐይቅ ከተማ አርሶ አደሮች30 ታህሳስ 2023
- ከ24 ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያን በኦሊምፒክ የወከለው ፅጋቡ ግርማይ ከብስክሌት ሕይወት ራሱን አገለለ30 ታህሳስ 2023
- “በትግራይ ያንዣበበውን ረሃብ ለመግታት የፌዴራል መንግሥቱ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል” – አቶ ጌታቸው ረዳ29 ታህሳስ 2023
የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ለዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ያስገባውን ማመልከቻ ተከትሎ በሰጠው መግለጫ ላይ አገራቸው “የዘር ማጥፋት እንዳያከሰት የመከላከል” ግዴታ እንዳለባት ተናግረዋል።
“ደቡብ አፍሪካ እስራኤል በጋዛ ሰርጥ በምትፈጽማቸው የዘፈቀደ ጥቃቶች እና በግዴታ ከመኖሪያ ቀያቸው የማፈናቀል ድርጊት በተመለከተ ሰላማዊ ዜጎች የሚያሰሙት የድረሱልኝ ጥሪ እጅጉን ያሳስቧታል” ስትል በመግለጫዋ ላይ አክላለች።
“በተጨማሪም እየወጡ ያሉ ሪፖርቶች ዓለም አቀፍ ወንጀሎችን የሚስተካከሉ፤ በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች እና የጦር ወንጀሎች መፈጸማቸውን፤ እንዲሁም የዘር ማጥፋት ወይም ተዛማጅ ወንጀሎችን የሚስተካከሉ ወንጀሎች መፈጸማቸውን እና ምናልባትም አሁንም በጋዛ እየተካሄደ ያለውን እልቂት ተከትሎ እየተፈጸመ እንደሆነ የሚጠቁሙ ናቸው” ብለዋል።
በ84 ገጽ ተዘርዝሮ የቀረበው የክስ ዶሴ እንደሚያስረዳው “በእስራኤል የተፈጸሙ ወንጀሎች እና ሆን ተብለው እንዳልታየ የታለፉ በድርጊታቸው የዘር ማጥፋት ጠባይ አላቸው። ምክንያቱም ፍልስጤምን እና ፍልስጤማውያንን ሁሉ ይኹነኝ ተብሎ ለማውደም እና ለማጥፋት የታቀደ ተግባር ስለሆነ” ይላል።
የቀረበው ማመልከቻ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት በሚቀጥለው ሳምንት ጉዳዩን እንዲመለከተው የሚጠይቅ ሲሆን፣ አክሎም በችሎቱ “መወሰድ ያለባቸውን እርምጃዎች” ያላቸውን፣ እስራኤል ማንኛውም ወታደራዊ እንቅስቃሴ በጋዛ እንድታቆም የሚጠይቀውን ጨምሮ፣ አንድ በአንድ ዘርዝሯል።
የእስራኤል የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ በበኩላቸው፣ ደቡብ አፍሪካ ለፍርድ ቤቱ ያቀረበችው ጥያቄ “ አስነዋሪ፣ በንቀት የተመላ እና የችሎቱን ጊዜ የሚያባክን” ብለውታል።
አክለውም ደቡብ አፍሪካ “እስራኤልን ለማጥፋት ጥሪ ከሚያቀርብ አሸባሪ ድርጅት ጋር እየተባበረች ነበር” ካሉ በኋላ ሐማስ “ በጋዛ ሰርጥ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን እንደ ምሽግ በመጠቀም እና፣ ለእነርሱ የቀረበን ሰብዓዊ እርዳታዎችን በመስረቅ ተጠያቂ ነው” ሲሉ ኮንነዋል።
“እስራኤል ዓለም አቀፍ ሕጎችን የምታከብር እንዲሁም በሕጎቹ መሰረት የምትንቀሳቀስ ናት፤ ወታደራዊ ጥረቶችን ሁሉም አሸባሪ ድርጅት የሆነው ሐማስ እና ከእርሱ ጋር የሚተባበሩ ላይ ብቻ ያነጣጠሩ ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል።
“እስራኤል በጋዛ የሚኖሩ ዜጎች ጠላት አለመሆናቸውን ግልጽ ያደረገች ሲሆን በግጭቱ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችንም በተቻለ መጠን ለመቀነስ እንዲሁም እርዳታ በጋዛ ሰርጥ እንዲገባ ፈቅዳለች”
ደቡብ አፍሪካ እስራኤል በጋዛ የምታካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ላይ የሰላ ትችት ደጋግማ ታቀርባለች።
በሕዳር ወር በእስራኤል የሚገኙ ዲፕሎማቶቿን የጠራች ሲሆን በምላሽም እስራኤል በፕሪቶሪያ የነበሯትን ዲፕሎማቶች አስወጥታለች።
በተጨማሪም የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ጉባኤ አገሪቱ ከእስራኤል ጋር ያላትን ማንኛውም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች እንዲያቋርጥ ወስኗል።
መንግሥት ግን ለዚህ የጉባዔው ውሳኔ ምንም ዓይነት ይፋዊ ምላሽ እስካሁን አልሰጠም።
ደቡብ አፍሪካ ከዚህ በፊትም ለዓለም አቀፉ የወንጀል ችሎት እስራኤል በጋዛ የፈጸመችውን የጦር ወንጀል በተመለከተ ክስ አቅርባ ነበር።
ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በበኩሉ ምርመራ ያደረገ ሲሆን ከዘር ማጥፋት፣ የጦር ወንጀሎች እንዲሁም ሰብዓዊነት ላይ ስማቸው የተነሱ ግለሰቦች ላይ ምርመራ አድርጓል።
እስራኤል ግን የዓለም አቀፉን የወንጀል ፍርድ ቤት አትቀበለውም።
እስራኤል በጋዛ ሰርጥ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ የጀመረችው እኤአ ጥቅምት 7 ሐማስ ደቡባዊ እስራኤል ላይ ጥቃት ከፍቶ 1200 ሰዎች ከሞቱ እና 240 ከታገቱ ወዲህ ነው።
በጋዛ እስራኤል እየወሰደች ባለው እርምጃ 21ሺህ 500 ሰዎች፣ በአብዛኛው ሴቶች እና ሕጻናት፣ መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር ገልጿል።