ፕሬዝዳንት ፑቲን እና ኪም ጆንግ ኢን

ከ 9 ሰአት በፊት

ያለፉት 12 ወራት በዓለም አቀፍ የፖለቲካ መድረክ ላይ ገናና በሆኑት አሜሪካ፣ አውሮፓ እና በሌሎች ዋና ዋና የዴሞክራሲ አገሮች በርካታ ውድቀቶች ታይተዋል።

ለጊዜውም ቢሆን የትኛውም አስከፊ አልነበረም። ነገር ግን ለዓመታት ሲንከባለሉ ከቆዩት የአሜሪካ የበላይነት እና ምዕራባውያን እሴቶች የኃይል ሚዛኑ እየራቀ መሄዱን ይጠቁማሉ።

በብዙ ግንባሮች ንፋሱ ከምዕራባውያን ፍላጎት በተቃራኒ እየነፈሰ ነው። ለምን እንደሆነ እና በሂደት ላይ ካሉ ለውጦች አሁንም ምን ጥቅሞች ሊመጡ እንደሚችሉ እነሆ፦

በሩስያ እና በዩክሬን መካከል የሚካሄደው ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ነው

ዩክሬን

በአውሮፓ ምስራቃዊ ድንበር ላይ ያለው ጦርነት ለዩክሬን አልሰመረላትም።

ይህም ማለት ለዩክሬን ጦርነት እና ምጣኔ ሃብት አስር ቢሊዮን ዶላሮችን ለከሰከሱት ኔቶ እና አውሮፓ ህብረት በከፋ ሁኔታ እየሄደ ነው ማለት ነው።

ባለፈው ዓመት በዚህ ወቅት በኔቶ ላይ ከፍተኛ ተስፋ ነበረ፣ የዩክሬን ጦር በምዕራባውያን ሀገራት ዘመናዊ ወታደራዊ ትጥቅ እና ከፍተኛ ስልጠና ታግዞ፣ በዛ በልግ የሩሲያን ጦርን ከያዘው ብዙ ግዛት ማስወጣት ይችላል የሚል ተስፋ ነበር።

ያ ተስፋ ግን እንደ ጉም በኗል።

ችግሩ ከጊዜ ጋር ተሽቀዳድሞ ውሳኔ የማሳለፍ ጉዳይ ነው።

ኔቶ ሀገራት ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ወደ ችኩል አፀፋዊ ምላሽ እንዲወስዱ ሊያደርጓቸው የሚችሉ ዘመናዊ ውጊያ ታንኮችን ወደ ዩክሬን ለመላክ ለመወሰን ረጅም ጊዜ ወስዶባቸዋል።

በመጨረሻም ምዕራባውያን ታንኮቹን ለዩክሬን አደረሱ።

ፕሬዚዳንት ፑቲን ያደረጉት ነገር አልነበረም። ነገር ግን በሰኔ ወር በጦር ሜዳ ላይ ለመሰማራት በተዘጋጁበት ጊዜ የሩሲያ ጦር አዛዦች ካርታውን ተመልክተው የዩክሬን ዋና ጥረት የት እንደሚሆን በትክክል ገምተው ነበር።

እ.ኤ.አ. በ2022 የሩስያ ጦር ኪየቭን ለመያዝ ባደረገው ሙከራ አጸያፊ ተግባር ፈጽሞ ሊሆን ይችላል፣ ነገር ግን መከላከል ላይ የላቀ ነው።

በ2023 የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ የዩክሬን ብርጌዶች በብሪታንያ እና በሌሎች ቦታዎች ሰልጥነው በነበሩበት እና ታንኮቹ ወደ ምስራቅ አቅጣጫ እየተጓጓዙ በነበረበት ወቅት ሩሲያ በዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ትልቁን እና ሰፊውን የመከላከያ ምሽግ እየገነባች ነበር።

ፀረ-ታንክ ፈንጂዎች፣ ፀረ-ሰው ፈንጂዎች፣ ቦንከር፣ ቦዮች፣ ታንክ ወጥመዶች፣ ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና መድፍ ተደማምረው የዩክሬንን እቅድ ማክሸፍ ችለዋል።

ብዙ ሲነገርለት የነበረው የመልሶ ማጥቃት ከሽፏል።

ለዩክሬን እና ለምዕራቡ ዓለም፣ልኬቶቹ ከሞላ ጎደል ሁሉም ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ እየሄዱ ነው።

ዩክሬን እጅጉን የጠመንጃ እና ወታደሮች እጥረት እያጋጠማት ነው።

የነጩ ቤተ መንግስት ለዩክሬን የ50 ኢሊዮን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ ለመቸር እያደረገ የዓለው ሙከራ በአሜሪካ ኮንግረስ ገታ ተደርጓል። ሃንጋሪ የአውሮፓ ህብረት 50 ቢሊዮን ዩሮ የእርዳታን አዘግይታለች።

ሁለቱም አሊያም አንደኛው ድጋፍ ለዩክሬን ሊደርስ ይችላል።

ነገር ግንያ በጣም ዘግይቶ ሊሆን ይችላል። የዩክሬን ኃይሎች ወደ መከላከል እያዘነበሉ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሞስኮ ኢኮኖሚዋን በጦርነት መሰረት በማድረግ ከብሔራዊ በጀቷ አንድ ሶስተኛውን ለመከላከያ በማውጣት በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን እና በሺዎች የሚቆጠሩ መድፍ በዩክሬን ጦር ግንባር ላይ እያሰለፈች ነው።

ቭላድሚር ፑቲን

የሩሲያው ፕሬዝዳንት በንድፈ ሀሳባ ደረጃ ተፈላጊ ሰው ናቸው።

እ.ኤ.አ. በመጋቢት 2023 በሄግ በሚገኘው ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ከህፃናት መብት ኮሚሽነሩ ጋር በዩክሬን ህጻናት ላይ በፈጸሙት የጦር ወንጀል ተከስሰዋል።

ምዕራባውያን ይህ ከዓለም አቀፉ መድረክ የተገለሉ እስርን እና ወደ ዘ ሄግ መተላለፈን ፈርተው በሀገራቸው ብቻ እንዲወሰኑ ያደርጋቸዋል የሚል ተስፋ ነበራቸው። ይህ ግን አልሆነም።

ከዚያ ክስ ጀምሮ፣ ፕሬዚዳንት ፑቲን ወደ ኪርጊስታን፣ ቻይና፣ ኤምሬትስ እና ሳዑዲ አረቢያ በመሄድ በእያንዳንዱ ጊዜ የቀይ ምንጣፍ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የብሪክስ ጉባኤ ላይም ተሳትፈዋል።

ተደጋጋሚ የአውሮፓ ህብረት ማዕቀቦች የሩስያን ኢኮኖሚ በማንበርከክ፣ፑቲን ወረራውን እንዲቀለበሱ ማድረግ ነበረባቸው።

ሆኖም ሩሲያ እነዚህን ማዕቀቦች በሚያስደንቅ ሁኔታ የመቋቋም አቅሟን አሳይታለች፣ብዙ ምርቶችን እንደ ቻይና እና ካዛክስታን ባሉ አገሮች በኩል እያገኘች ነው።

እውነት ነው፣ ምዕራባውያን ከሩስያ ነዳጅ እና ጋዝ መግዛት አቁመዋል፤ ነገር ግን ሞስኮ በቅናሽ ዋጋ ቢሆንም ሌሎች ፈቃደኛ ደንበኞችን አግኝታለች።

እስራኤል ከመስከረም ወር መጨረሻ ጀምሮ በጋዛ ሰርጥ ወታደራዊ እርምጃ እየወሰደች ትገኛለች።

ጋዛ

የእስራኤል እና ሐማስ ጦርነት ለጋዛውያን እና በመስከረም 26 የሐማስ ጥቃት ለተጎዱ እስራኤላውያን አስከፊ ነበር፤ ለምዕራቡ ዓለምም መጥፎ ነበር።

መላው ዓለም ፊቱን በዚህ ክረምት የሩሲያን ግስጋሴ ለመግታት ስትታገል ከቆየችው ዩክሬን ወደ እስራኤል እና ሐማስ ጦርነት አዙሯል።

የአሜሪካ የጦር መሳሪያንም ከኪየቭ እንዲርቅ አድርጎ ለእስራኤል ጥቅም እንዲውል አድርጓል።

ከሁሉም በላይ ግን በብዙ ሙስሊሞች እና በዓለም ላይ ባሉ ሌሎች ሰዎች እይታ፣ አሜሪካ እና እንግሊዝ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስራኤልን በመጠበቅ በጋዛ ጥፋት ተባባሪ እንዲመስሉ አድርጓል።

የአየር ኃይሉ በሶሪያ አሌፖ ከተማ ላይ የቦምብ ድብደባዎችን ሲያደርግ የነበረው ሩሲያም፣ ከመስከረም 26 ጀምሮ በመካከለኛው ምስራቅ ክምችቷ እየጨመረ መጥቷል።

ጦርነቱ ከወዲሁ ወደ ደቡባዊ ቀይ ባህር ተዛምቶ በኢራን የሚደገፉ ሁቲዎች፤ ፈንጂ፣ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እና ሚሳኤሎችን ወደ መርከቦች በማስወንጨፋቸው የሸቀጦች ዋጋ እንዲንር አድርጓል።

ኢራን

ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያን በድብቅ በማዘጋጀት ትታማለች።

ሆኖም ምዕራባውያን በርካታ ጥረቶች ቢያደርጉም፣ በምታሰለጥናቸው፥ በምትደግፋቸው እና በምታስታጥቃቸው ሚሊሻዎች አማካኝነት ወታደራዊ መሰረቷን በኢራቅ፣ ሶሪያ፣ ሊባኖስ፣ የመን እና በጋዛ እያስፋፋች ነው።

በዚህ ዓመት ከሞስኮ ጋር የጠበቀ ጥምረት መፍጠር የቻለች ሲሆን፣ ይህም ያለገደብ የሻሄድ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በዩክሬን ከተሞች ለመምታት ስታቀርብ ቆይታለች።

በበርካታ ምዕራባውያን ሀገራት እንደ ጠበኛ የተፈረጀችው ኢራን በመካከለኛው ምስራቅ የፍልስጤም ጉዳይ ደጋፊ በመሆን ከጋዛ ጦርነት ተጠቃሚ ሆናለች።

በኒጀር በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን የተቆጣጠሩት ወታደራዊ አዛዦች

የአፍሪካ ሳህል

በምዕራብ አፍሪካ የሳህል ክልል ሀገራት አንድ በአንድ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት እየተሸነፉ ነው።

ይህ ብቻም ሳይሆን፣ በአካባቢው ያለውን የጂሃዲስት አማጽያን ለመዋጋት ይረዱ የነበሩትን የአውሮፓ ኃይሎች በማባረር ላይ ናቸው።

የቀድሞ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛቶች የማሊ፣ቡርኪናፋሶ እና የመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ቀደም ሲል በአውሮፓውያን ላይ ፊታቸውን አዙረዋል።

ሌላ መፈንቅለ መንግሥት ለምዕራቡ ዓለም ስስ ልብ የነበራቸውን የኒጀር ፕሬዝዳንት ከመንበራቸው አውርዷል።

ምንም እንኳን 600 የአሜሪካ ወታደሮች በሁለት ካምፖች ውስጥ ቢቆዩም የመጨረሻው የፈረንሳይ ጦር አሁን ሀገሪቱን ለቆ ወጥቷል።

የሩስያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ቫግነር የፈረንሳይ እና የዓለም አቀፍ ኃይሎችን እየተካ ነው።

ምንም እንኳን መሪው ኢቭጄኒ ፕሪጎዚን በነሐሴ ወር በአውሮፕላን አደጋ ህይወቱ ቢያልፍም ትርፋማ በሆነው የንግድ ስምምነቱ ላይ ተጣብቆ መቆየት ችሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአንድ ወቅት የምዕራቡ ዓለም ወዳጅ ተደርጋ ትታይ የነበረችው ደቡብ አፍሪካ ከሩሲያና ከቻይና የጦር መርከቦች ጋር በጋራ የባህር ኃይል ልምምዶችን ስታደርግ ቆይታለች።

ሰሜናዊ ኮሪያ

የኮሪያ ዲሞክራሲያዊ ህዝባዊ ሪፐብሊክ በተከለከለው የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እና የባሊስቲክ ሚሳኤል ፕሮግራም ምክንያት ጥብቅ ዓለም አቀፍ ማዕቀብ ሊጣልባት ይገባ ነበር።

በዚህ ዐዓመት ግን ከሩሲያ ጋር የጠበቀ ግንኙነት የፈጠረች ሲሆን መሪዋ ኪም ጆንግ ኡን የሩስያ የጠፈር ጣቢያን ሲጎበኙ ሰሜን ኮሪያ በዩክሬን ውስጥ ለሚዋጉት የሩሲያ ኃይሎች አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ጠመንጃዎችን ልካለች።

ሰሜን ኮሪያ በርካታ አህጉር አቋራጭ ባሊስቲክ ሚሳኤሎችን ሞክራለች፣ እነዚህም አሁን ወደ አብዛኛው አሜሪካ ክፍሎች ሊደርሱ ይችላሉ ተብሎ ይታመናል።

ቻይና

በተወሰነ ደረጃ፣ በ2023 በቤጂንግ እና በዋሽንግተን መካከል ያለው ውጥረት እየቀለለ መጥቷል።

በአሜሪካዋ ሳንፍራንሲስኮ በፕሬዝዳንት ባይደን እና በዢ ጂንፒንግ የተሳካ ስብሰባ ተካሂዷል።

ነገር ግን ቻይና በአብዛኛዎቹ የደቡብ ቻይና ባህር ላይ የምታቀርበውን የይገባኛል ጥያቄ ለመተው ምንም አይነት ምልክት አላሳየችም።

የይገባኛል ጥያቄዋን እስከ በርካታ የእስያ-ፓሲፊክ ሀገራት የባህር ዳርቻ ድረስ የሚዘረጋ አዲስ “መደበኛ” ካርታ አውጥታለች።

እንዲሁም አስፈላጊ ከሆነ በኃይል “ለመመለስ” ቃል የገባችውን ታይዋን ላይ ያለውን የይገባኛል ጥያቄም አልተወችም።

የብሩህ ተስፋ ምክንያቶች?

በምዕራቡ ዓለም ላይ ያጠላው ደመና ተገፍፎ ብራ ይሆናል ብሎ ተስፋ ማድረግ ከባድ ሊሆን ይችላል።

ነገር ግን ለምዕራቡ ዓለም በጎ ጎኑ የዩክሬንን በሩስያ መወረር ተከትሎ የኔቶ ጥምረት መከላከያ ዓላማውን እንደገና አግኝቷል።

ምንም እንኳን አንዳንድ ስንጥቆች አሁን መታየት የጀመሩ ቢሆንም፣ እስካሁን የሚታየው የምዕራቡ ዓለም አንድነት ብዙዎችን አስገርሟል።

ነገር ግን ከፍተኛ የመሻሻል አቅም ያለው በመካከለኛው ምስራቅ ነው። ያ የሆነውም በከፊል በጋዛ-እስራኤል ድንበር በሁለቱም በኩል በተከሰቱት አሰቃቂ ክስተቶች ምክንያት ነው።

ከመስከረም 26 በፊት የፍልስጤም የራሳቸውን ነጻ ሀገር እና መንግሥት የመመስረት ጥያቄ፣ መፍትሄ ፍለጋ ቸል ተብሎ ነበር።

እስራኤል ከፍልስጤማውያን ጋር የምታደርገው ግንኙነት፣ ለፍልስጤማውያን የራሳቸውን መንግሥት ለመመስረት፣ ከባድ እርምጃ ሳይወሰድ በደህንነት እርምጃዎች ብቻ መፍትሄ ሊበጅለት የሚችል ነው የሚል እምነት አለ።

ያ ቀመር አሁን ለሞት የሚያጋልጥ ጉድለት እንዳለበት ታይቷል።

የዓለም መሪዎች ፍልስጤማውያን ተመሳሳይ ነገር ማድረግ እስካልቻሉ ድረስ፣ እስራኤላውያን በሚገባቸው ሰላምና ደህንነት መኖር እንደማይችሉ አውጀዋል።

ሰፊ ታሪካዊ ዳራ ላላው ችግር ፍትሃዊ እና ዘላቂ መፍትሔ መፈለግ እጅግ በጣም ከባድ ነው።

ፍሬ እንዲያፈራም ከሁለቱም ወገን እጅግ አስቸጋሪ መስዋትነትን ይሻል።

አሁን ግን በመጨረሻም ቢሆን የዓለምን ትኩረት አግኝቷል።