መጋቢ ላኮ በዳሶ፣ የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተክርስትያን ፕሬዝዳንት

30 ታህሳስ 2023, 09:46 EAT

የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን በኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድር ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ባለችው የሙሉ ወንጌል አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በደረሰው “ድንገተኛ ጥቃት” አባላቶቿ መገደላቸውን አወገዘች።

እንደ ቤተክርስትያኒቷ መግለጫ ከሆነ በጥቃቱ “ስምንት የቤተክርስትያኒቷ አባል የሆኑ ግለሰቦች” ተገድለዋል።

ጥቃቱ የተፈጸመው ታህሳስ 15 2016 ዓ.ም መሆኑን የተናገሩት የቤተክርስትያኒቷ ፕሬዝዳንት፣ መጋቢ ላኮ በዳሶ፣ አምስት ሰዎች ቆስለው ሆስፒታል እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለሮይተርስ የዜና ወኪል ጥቃቱ ምዕመናኑ ላይ መፈጸሙን አስተባብሏል።

የሆሮ ጉዱሩ አካባቢ የሙሉ ወንጌል ኃላፊ የሆኑት ፓስተር ተካልኝ ዳባ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ታሕሳስ 15 2016 የድሮን ጥቃት በቤተክርስትያኒቷ አባላት ላይ ሲፈጸም፣ ግለሰቦቹ በቤተክርስትያኒቱ ግቢ ውስጥ በሚገኝ የበቆሎ እርሻ ውስጥ ምርት በመሰብሰብ በላይ ነበሩ።

በጥቃቱ ሁለት የሦስተኛ እና የስድስተኛ ክፍል ተማሪዎች መገደላቸውን አክለው ተናግረዋል።

በድሮን ጥቃቱ የቤተክርስትያኒቷን መሪ ጨምሮ፣ ዲያቆናት፣ የጥበቃ ጓድ፣ የሙዚቃ መሳርያ ተጫዋቾች እና አባላት በአጠቃላይ ስምንት ሰዎች መገደላቸውን ፓስተር ተካልኝ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

መጋቢ ላኮ በዳሶ በመግለጫቸው “ድርጊቱ በየትኛውም አካል በምንም መልኩ ይፈጸም፤. . . .ጉዳዩ በማን እንደተፈጸመ ተጣርቶ ፍትህ እንዲሰፍን” እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

የመንግሥት ቃል አቀባይ ለገሠ ቱሉ፣ ባለፈው ሰኞ በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በባሮ ሙሉ ወንጌል ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ የተፈጸመውን የድሮን ጥቃት “ፍጹም ሐሰት” በማለት እንዳስተባበሉ ሮይተርስ ዘግቧል።

ቤተክርስትያኒቷ በዚህ መግለጫዋ ላይ “ገለልተኛ አካል የሆነው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና ሌሎች ተመሳሳይ ተቋማት ጉዳዩን በአንክሮ በማየት እንዲያጣራ” ጠይቃለች።

“በተመሳሳይ በአማራ ክልላዊ መንግሥት በዱር ቤቴ እንዲሁም በቡሬ ከተማ በአባሎቿ ላይ የሞት፥ የስደትና የንብረት ጉዳት” መድረሱን የቤተክርስትያኒቷ ፕሬዝዳንት በዚሁ መግለጫቸው ላይ አመልክተዋል።

በምዕራብ ኢትዮጵያም የአማኞችን ንብረት መውረስና መፈናቀል እየደረስ እንዳለ፣ ይህን የሰብዓዊ መብት መጣስና የዜጎችን ጉዳት የሚመለከተው አካል ሁሉ እንዲያጣራ ከፕሬዚዳንቱ ቢሮ የወጣው መግለጫ ጠይቋል።

በምዕራብ ኦሮሚያ በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ ግድያ ሲፈጸም ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም።

በሕዳር ወር በምዕራብ ኦሮሚያ ቄለም ወለጋ ዞን ጊዳሚ ወረዳ ጊዳሚ ከተማ በሚገኘው የመካነ ኢየሱስ ቤተ-ክርስቲያን ጸሎት ላይ የነበሩ ዘጠኝ ሰዎች በታጣቂዎች ተወስደው መገደላቸው ይታወሳል።

ከአንድ ዓመት በፊት በምሥራቅ ወለጋ ዞን ታጣቂዎች በአምልኮ ላይ በነበሩ ሰዎች ላይ በፈጸሙት ጥቃት 15 ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ አስታውቃ ነበር።

ባለፉት ዓመታት በምዕራብ ኢትዮጵያ በሚገኙ የኦሮሚያ አካባቢዎች ውስጥ በታጣቂዎች በሚፈጸሙ ጥቃቶች እና የመንግሥት ኃይሎች በሚወስዷቸው እርምጃዎች ሳቢያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸው ሲዘገብ ቆይቷል።

በተጨማሪም በርካቶች ለአካል ጉዳት ከመዳረጋቸው በተጨማሪ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ጥቃቶችን በመሸሽ ከቀያቸው ለመፈናቀል ተዳርገዋል።

መንግሥት ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር በታንዛንያ በሁለት ዙር ሲያደርገው የነበረው ድርድር ያለውጤት ከተጠናቀቀ ወዲህ በምዕራብ ኦሮሚያ የሚያካሄዳቸው ውግያዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ነዋሪዎች ይናገራሉ።