
31 ታህሳስ 2023, 08:46 EAT
በቱሪስት መዳረሻነቷ የምትታወቀው የጣሊያኗ ቬነስ ከተማ ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ጎብኚዎች የሚደርስባትን ጫና ለመቀነስ የቡድን ተጓዦችን እና ድምጽ ማጉያዎችን ልታግድ መሆኑ ተነገረ።
የከተማዋ አስተዳደር ከስድስት ወራት በኋላ ተፈጻሚ በሚሆነው መመሪያ ከ25 በላይ ሆነው የሚመጡ ጎብኚዎች በከተማዋ አይስተናገዱም።
ከዚህ በተጨማሪም ድምጽ ማጉያዎች “የከተማዋን ጸጥታ ስለሚረብሹ” ጥቅም ላይ መዋል አይችሉም ተብሏል።
በአውሮፓ በከፍተኛ ደረጃ ከሚጎበኙ ቀዳሚ መዳረሻዎች መካከል አንዷ የሆነችው ቬነስ፤ ከፍተኛ የጎብኚ ቁጥር ጫና የሚያሳድርባት ከተማ ናት።
- “ካሳ ሳይተላለፍልን መሬታችን እየታረሰ ነው” – በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት ከይዞታቸው የሚነሱ የሐይቅ ከተማ አርሶ አደሮች30 ታህሳስ 2023
- “የመሻገር ሲቃ ከጻፍኳቸው መጻሕፍት ሁሉ በጣም የተሻለ እና እኔንም የሰራኝ መጽሐፍ ነው” ደራሲ እና ሃያሲ ያዕቆብ31 ታህሳስ 2023
- ‘ሰይጣን እናስወጣለን’ የሚለው የዩናይትድ ኪንግደም ቤተ ክርስትያን31 ታህሳስ 2023
የከተማዋ ስፋት 7.6 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ብቻ ቢሆንም በዓመት በአማካይ እስከ 28 ሚሊዮን ቱሪስቶችን ታስተናግዳለች።
የከተማዋ ምክር ቤት ከዚህ ቀደም የጎብኚዎችን ቁጥር ለመቆጣጠር ሲል ከ14 ዓመት በላይ የሆናቸው ጎብኚዎች ወደ ከተማዋ ለመግባት የ5 ዩሮ ክፍያ እንዲፈጽሙ የሚያስገድድ ሕግ አውጥቶ ነበር።
የቬነስ ከተማ የጸጥታ ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑት ኤልሳቤታ ፔሴስ በቡድን የሚመጡ ጎብኚዎችን ቁጥር መገደብ ያስፈለገው ታሪክ ቦታዎች በሚጎበኙባቸው ቦታዎች የሰዎችን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር በማሰብ ነው ብለዋል።

ከጥቂት ወራት በፊት የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) የአየር ንብረት ለውጥ እና ከፍተኛ የጎብኚ ቁጥር ቬነስ ከተማ ላይ ሊቀለበስ የማይችል አደጋ ስለጋረጡ ከተማዋ ለአደጋ የተጋለጠች የዓለም ቅርስ ስፍራ ተብላ መመዝገብ አለባት ብሎ ነበር።
ድርጅቱ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የባሕር ጠለል ከፍታ መጨመር ለከተማዋ አስጊ ነው ያለ ሲሆን በጎብኚዎች ቁጥር መጨመር ምክንያት ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች መገንባታቸው እንዲሁም የመሠረተ ልማቶች መስፋፋታ የከተማዋን ታሪካዊነት እና ውበት የሚያጠፋ ነው ይላል።