የቢቢሲ ጋዜጠኛ በቤተ ክርስቲያኑ ‘ሰይጣን የማውጣት’ ሥነ ሥርዓት ላይ ስትሳተፍ
የምስሉ መግለጫ,የቢቢሲ ጋዜጠኛ በቤተ ክርስቲያኑ ‘ሰይጣን የማውጣት’ ሥነ ሥርዓት ላይ ስትሳተፍ

31 ታህሳስ 2023, 08:07 EAT

‘ዩኒቨርሳል ቸርች ኦፍ ዘ ኪንግደም ኦፍ ጋድ’ የተባለ ቤተ ክርስትያን ከ16 ዓመት ታዳጊ ‘ሰይጣን ለማስወጣት’ ሲሞከር በምሥጢር ቪድዮ ቀርጿል።

የዚህ ቤተ ክርስቲያን የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ቅርንጫፍ ነው ቪድዮውን የቀረጸው።

የቤተ ክርስቲያኑ ፓስተር ‘ጠንካራ ፀሎት’ በማድረግ ታዳጊውን ከሰይጣን ነጻ ለማውጣት ሲሞክሩ ይታያል።

የቀድሞው የቤተ ክርስቲያኑ አባል በ13 ዓመቱ ከተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪነት ወደ ተቃራኒ ጾታ አፍቃሪነት ለማምጣት ‘ጠንካራ ፀሎት’ እንደተደረገለት ለቢቢሲ ፓናሮማ ገልጿል።

ቤተ ክርስትያኑ እንደሚለው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ‘ጠንካራ ፀሎት’ አይደረግላቸውም። ሰዎችን ወደ ተቃራኒ ጾታ አፍቃሪነት ‘ለመለወጥ’ ሙከራም አያደርጉም።

ቢቢሲ ፓናሮማ ባደረገው ምርመራ መሠረት፣ ቤተ ክርስትያኑ የአእምሮ ሕመም ያለባቸውን ሰዎች ከሰይጣን እንደሚያላቅቅ ለምዕመናኑ ይናገራል።

የቤተ ክርስትያኑ መሪ የሚጥል ሕመም ‘የመንፈስ መታወክ’ ነው ይላሉ።

ቤተ ክርስትያኑ በዩኬ ያሉትን 35 ቅርንጫፎች ጨምሮ በተለያዩ አገራት ቅርንጫፎች አሉት።

በአገሪቱ ከ10 ሺህ በላይ ተከታዮች እንዳሉት የሚገልጸው ቤተ ክርስትያኑ፣ ራሱን ክርስትያን ጴንጤቆስጣል ሲል ይገልጻል።

በበጎ አድራጎት ድርጅትነት ተመዝግቧል።

በክርስትና ዓለም ሰይጣንን ለማውጣት ፀሎት ማድረግ እንግዳ አይደለም።

የተለያዩ የክርስትና አካሄዶችን በአንድነት ለማምጣት የሚሞክሩት ዶ/ር ጆ አልደርድ “ቤተ ክርስትያኖች ሰይጣን እንደሚያወጡ ይገልጻሉ። ጥያቄው እንዴት ያከናውኑታል የሚለው ነው” ይላሉ።

የዩኬው ቤተ ክርስትያን ‘ጠንካራ ፀሎት’ የሚለው ፓስተር ምዕመናን ላይ እጁን ጭኖ ሰይጣን ከሰውነታቸው እንዲወጣ ሲያዝ ነው።

‘መንፈስ የማጽዳት’ ሥነ ሥርዓት በየሳምንቱ እንደሚካሄድ ቤተ ክርስትያኑ ይገልጻል። ይህም ‘ችግሮችን ከሥራቸው ነቅሎ ለመጣል’ እንደሆነ ይገልጻል።

የስምንት ዓመቷ ታዳጊ ቪክቶርያ ክሊምቢ በእናቷ አክስትና የወንድ ጓደኛ ተሰቃይታ ከተገደለች በኋላ ቤተ ክርስትያኑ ትችት በዝቶበታል።

እአአ በ2000 ቪክቶርያን ከቤተ ክርስትያኖቹ ቅርንጫፎች ወደ አንዱ ወስደዋት ነበር። በወቅቱ ጥቃት ደርሶባት እንደነበረ ምልክቶች ይታዩባት ነበር።

ቪክቶርያ ሰይጣን እንደያዛትና ‘ጠንካራ ፀሎት’ እንደሚያስፈልጋት አንድ ፓስተር ገልጸዋል። ይህ ከመካሄዱ በፊት ልጅቷ ወደ ሆስፒታል እንድትወሰድ ለእናትየው አክስት ፓስተሩ ነግረው ነበር።

ኋላ ላይ የወጣ ሪፖርት እንደሚለው ቪክቶርያ ከመሞቷ በፊት “የቪክቶርያ ሁኔታ አስጊ ነበር። ይህንንም አላስተዋሉም፣ ለሚመለከተው የበላይ አካልም አልገለጹም።”

ቤተ ክርስትያኑ ልጆችን የሚጠብቅ ፖሊስ የሌለው መሆኑ እንደሚያሰጋም ተመልክቷል።

‘ዩኒቨርሳል ቸርች ኦፍ ዘ ኪንግደም ኦፍ ጋድ’
የምስሉ መግለጫ,‘ዩኒቨርሳል ቸርች ኦፍ ዘ ኪንግደም ኦፍ ጋድ’

ከዚህ በኋላ ቤተ ክርስትያኑ ደኅንነት ለመጠበቅ ፖሊሲ አወጣ። ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ላይ ‘ጠንካራ ፀሎት’ ላለማድረግና እነሱ ባሉበትም ላለማከናወን ወስኗል።

ቢቢሲ ፓኖራማ በብሪክስተን የሚገኝ የቤተ ክርስቲያኑ የወጣቶች አገልግሎት ጎብኝቷል።

ቄስ ኤድር ማክዶ ናቸው መሪው።

በምሥጢር የተቀረጸው ቪድዮ ክፍሉ ውስጥ ያሉትን በዕድሜ ሲከፋፍሉ ያሳያል።

16 ዓመቱ እንደሆነ የገለጸ ተሳታፊ ‘ጠንካራ ፀሎት’ ሲደረግለት ይታያል።

“እግዚአብሔር የተደበቀውን የሰይጣን መንፈስ ያቃጥልልህ” ይላሉ ፓስተሩ።

ፓስተሩ የልጁን ጭንቅላት ይዘዋል። ሰውነቱ ውስጥ የገባው ሰይጣን እንዲወጣ ይፀልያሉ።

ቢቢሲ ይህንን ቪድዮ ገለልተኛ ለሆነው የሕጻናት ጥበቃ ቡድን ባልደረባ ጃኒ ዴቪስ አሳይቷል።

“ቪክቶርያ ከሞተች በኋላ ምን ያህል ቤተ ክርስትያኑ ትምህርት እንደወሰደ መጠየቅ ያስፈልጋል። ደኅንነት ለመጠበቅ ፖሊሲ ቢወጣም ካልተተገበረ ትርጉም አልባ ነው” ብላለች።

ቤተ ክርስትያኑ በሰጠው የጽሑፍ ምላሽ ይህ ሥነ ሥርዓት ከ19 ዓመት በታች ለሆኑ እንደማይሰጥና የደኅንነት ፖሊሲውንም እንዳልጣሰ ገልጿል።

የሰዎችን ሕይወት እንደሚለውጥ ቤተ ክርስትያኑ ይገልጻል።

ከ40 የቀድሞ የቤተ ክርስትያኑ አባላት ጋር ቃለ ምልልስ ተደርጓል። ከዓመታትና ከወራት በፊትም ነው ቤተ ክርስቲያኑን ለቀው የወጡት።

ሻሮን ለንደን ያለውን ቤተ ክርስትያን የተቀላቀለችው በ19 ዓመቷ ነው።

ድባቴ እንዳለባት ለፓስተር ብትናገርም ሕክምና እንድትወስድ ምክር እንዳልተሰጣት ትገልጻለች።

ከቤተ ክርስቲያኑ የደኅንነት ጥበቃ ፖሊሲ ጋር በሚጻረር ሁኔታ ‘ጠንካራ ፀሎት’ ተደርጎላታል።

ፖሊሲው የአእምሮ ሕሙማን ይህ ፀሎት እንደማይደረግላቸው ይደነግጋል።

“እኔን ዒላማ እያደረጉ እንደሆነ ስለተሰማኝ ወደነዚህ አገልግሎቶች መሄድ መፍራት ጀመርኩ” ትላለች ሻሮን።

ይህ አገልግሎት አስፈሪ ወይም ጎጂ እንዳልሆነ ቤተ ክርስቲያኑ ይገልጻል።

የአእምሮ ጤና እክል በሚገጥም ወቅት ወደ አማካሪ እንዲሄዱ ጥቆማ እንደሚሰጥም ገልጿል።

ማርክ (ስሙ ተቀይሯል) የተባለ የቀድሞ የቤተ ክርስትያኑ አባል ግን ከ13 ዓመቱ ጀምሮ ተቃራኒ ጾታ አፍቃሪ እንዲሆን ‘ጠንካራ ፀሎት’ እንደተደረገለት ይናገራል።

“ተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ መሆኔን ስነግራቸው ሰይጣን ነው እንደዛ ያደረገህ አሉኝ። ዘወትር አርብ እየሄድሙ ሰይጣን የማውጣት ሥነ ሥርዓት እንድካፈል ተነገረኝ” ይላል።

ፀሎቱ በየሳምንቱ ከአራት ሰዓት በላይ ይካሄድ እንደነበረ ይገልጻል።

ተቃራኒ ጾታ እንደሚማርከው ራሱን ለማሳመን ይሞክር እንደነበር ይናገራል።

“እያለቀስኩ እተኛ ነበር። ራሴን በጣም ጠልቼ ነበር” ይላል።

ቤተ ክርስትያኑ ግን ከጾታና የፍቅር ግንኙነት ምርጫ ጋር በተያያ ይህ ፀሎት እንደማይካሄድ ይገልጻል። ማንኛውም የጾታ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች እንደሚቀበልም ያክላል።

ቢቢሲ በምሥጢር በቀረጸው ‘ጠንካራ ፀሎት’ ላይ ፓስተር ጄምስ ማርከስ አንዳንድ ሕመሞች የክፉ መንፈስ ችግር እንደሆኑ ለምዕመናኑ ይናገራሉ።

የቢቢሲን ጋዜጠኛ “ድባቴ የመንፈስ ችግር ነው። ከጀርባው ያለው ክፉ መንፈስ ነው” ብለዋል።

“የሚጥል በሽታ ሕመም እንደሆነ እናውቃለን። መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ግን የሚጥል በሽታ የሚከሰተው በክፉ መንፈስ እንደሆነ ይገልጻል። አካላዊ ሳይሆን መንፈሳዊ ችግር ነው” ብለዋል።

ቤተ ክርስቲያኑ እንደሚለው ግን ‘ጠንካራ ፀሎት’ ሕክምናን በሚተካ መንገድ አይደለም የሚሰጠው።

የቀድሞ የቤተ ክርስትያኑ አባላት ለመውጣት ተቸግረው እንደነበር ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ከቤተ ክርስትያኑ ወጥታ ንቅናቄ የጀመረችው ሬቸል እንደምትለው፣ ለወጣቶች አደገኛ ነው።

“ከቤተ ክርስትያኑ የወጡ ሰዎች ተፋተዋል። ካንሰር ይዟቸዋል ይላሉ” ትላለች።

የቀድሞ አባል በሞተር ሳይክል አደጋ ሰውነቱ እጅግ ተጎድቶ የሚያሳይ አሰቃቂ ቪድዮ በማሳየት ማስፈራሪያ እንደሚሰጥም ታክላለች።

“ከቤተ ክርስትያኑ ስትወጡ ሰይጣን ነፍሳችሁን ይቀማችኋል ይላሉ” ትላለች።

ከቤተ ክርስቲያኑ ከወጡ በኋላ እናታቸው የሳምባ ካንሰር እንደያዛት በመግለጽ አንድ ሰባኪ ሲያስተምሩ ቢቢሲ በምሥጢር ቀርጿል።

ከዚያ ግን ወደ ቤተ ክርስቲያኑ እንደተመለሱና ‘ካንሰሩ እየጠፋ መምጣቱን’ ተናግረዋል።

ቤተ ክርስትያኑ በበኩሉ ሰዎችን እንደማያስፈራራና በምርጫቸው የሄዱን እንደሚቀበል ለቢቢሲ ገልጿል።

አባላቱ በጎ አገልግሎቱን እንደሚያደነቁም አክሏል።

ጥለው የወጡ አባላት ግን ፈጽሞ እንደማይመለሱ ይናገራሉ።