mali

ከ 7 ሰአት በፊት

ከአስር ዓመታት በኋላ የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ኃይል በአገሪቱ ወታደራዊ መንግሥት ትዕዛዝ ከማሊ መውጣት ጀመረ።

ተመድ ባለፉት አስር ዓመታት በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ማሊ አሰማርቷቸው የነበሩ የሰላም አስከባሪ ወታደሮች ዛሬ እሁድ ከሀገሪቱ ጠቅልለው እየወጡ ነው።

በሀገሪቱን ለማረጋጋት የተቀናጀ ተልዕኮ የተሰጠው ይህ ኃይል እ.አ.አ በ2013 የተሰማራው ታጣቂ ቡድኖች፤ በትጥቅ የታገዘ አመጽ መጀመራቸውን ተከትሎ ነበር።

በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን ላይ የወጣው ወታደራዊ መንግሥት፤ ሀገሪቱን መምራት ከጀመረ ወዲህ ግን ወታደሮቹ ሀገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ ሲጠይቅ ቆይቷል።

የተበሩት መንግሥታት ተልዕኮ ኃላፊ በሀገሪቱ የተሰማራው ኃይል ብዙ ተግባራትን ቢያከናውንም እቅዱን አለማሳካቱን ተናግረዋል።

310 ገደማ የሰላም አስከባሪ ኃይሎች የተገደሉበት የማሊ ስምሪት፤ ከሊባኖስ ቀጥሎ ብዙ ወታደሮች የተገደሉበት የተባበሩት መንግሥታት ተልዕኮ ነው።

ባለፈው የክረምት ወቅት ማሊ 12 ሺህ ሰላም አስከባሪዎች እንዲወጡ በመጠየቋ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤትን ተልዕኮውን ለማቋረጥ ወስኗል።

ባለፉት ወራት ደረጃ በደረጃ ከማሊ ሲወጡ ለቆዩት ኃይሎች፤ ጠቅልሎ ለመውጣት የተቀመጠው ቀነ ገደብ ዛሬ ታኅሣሥ 21/2016 ዓ.ም. ነው።

የሰላም ማስከበር ተልዕኮው እስካሁን ሳይስተላልፍ የቆየውን እና ዋነኛ የሆነውን በሰሜን ቲምቡክቱ ግዛት የሚገኝ ካምፕ ከቀነ ገደቡ አስቀድሞ ማስረከቡን ባለፈው አርብ ዕለት እንዳስረከበ አንድ የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግቦ ነበር።

ከቀነ ገደቡ መጠናቀቅም በኋላ ክፍት ሆነው እንዲቆዩ ታስበው ከነበሩ ሶስት አካበቢዎች ውስጥ አንዱ ቲምቡክቱ የሚገኝበት ቢሆንም በአካባቢው ታጣቂዎች መኖራቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ላይ ስጋት እንደፈጠረ ሪፖርት አመላክቷል።

የተልዕኮው ኃላፊ የሆኑት ኤል ጋሲም ዌን በሰጡት መግለጫ “እንድናከናውን በተሰጠን ኃላፊነት እና ማከናወን በቻልነው መካከል ልዩነት አለ” ሲሉ ተደምጠዋል።

“ብዙ ሰርተናል ነገ ግን ከጠበቅነው እና ከሚያስፈልገው በታች ነው” ሲሉም አክለዋል።

የእስላማዊ እና የነጻ አውጪ ቡድኖች እንቅስቃሴ የሚገኙባት ማሊ የጸጥታ ሁኔታዋ አስጊ የሚባል ነው።

ምዕራባውያን ሀገራት በማሊ ላይ ያላቸው ተጽእኖ እየቀነሰ መምጣቱን ተከትሎ የሀገሪቱ መንግሥት የሩሲያ ቅጥረኛው ተዋጊ ቡድን ቫግነርን በማስገባት ጭምር ከሩስያ ጋር ያለው ቀረቤታ እያጠናከረ ነው።

ዛሬ ጠቅልሎ እየወጣ ያለው የሰላም አስከባሪ ኃይል ከ10 ዓመት በፊት በማሊ የተሰማራው ተገንጣይ አማጽያን እና ኢስላማዊ ተዋጊዎች በአንድ ላይ ሆነው ሰሜናዊ ማሊን ተቆጣጥረው ሌላ ሀገር ለመመስረት በመንቀሳቀሳቸው ነበር።

በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የተገደሉት እና በአስር ሺዎችን ያፈናቀሉት ኢስላማዊ ታጣቂዎች የሚፈጥሩት ስጋት ባለፉት ዓመታትም ቀጥሏል።

የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ በሀገሪቱ ከተሰማራ በኋላም ቢሆን የሚደርሱ የሽብር ጥቃቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ጨምረዋል።