
31 ታህሳስ 2023, 08:07 EAT
ደራሲ፣ ተርጓሚ እና ሃያሲ ያዕቆብ ብርሃኑ በጣት የሚቆጠሩ መጻህፍትን ለሕትመት አብቅቷል። ሠልስቱ ጣዖታት (ብኩን ነፍሳት)፣ የካህሊል አማልክት፣ ከባዶ ላይ መዝገን (የዘመን ስንክሳር ቅንጣቶች)፣ የመሻገር ሲቃ (ከዐውሎ ነፋስ ጋር መደነስ) እንዲሁም በፍም እሳት ማቃመስ ከስራዎቹ መካከል ናቸው። ደራሲ እና ሃያሲ ያዕቆብ ለመጽሐፎቹ ሁለት ርዕስ በመስጠት ይታወቃል። እርሱም ይህንን የሚያደርገው “አንባቢን ከተጽዕኖ ነጻ ለማውጣት ነው” ይላል። ደራሲ ያዕቆብ በስራዎቹ ውስጥ ተመሳሳይ ጭብጦችን የሚያነሳ ሲሆን ሥነ ልቡና፣ ሥነ ተረክ (ሚቶሎጂ)፣ ታሪክ፣ ፍልስፍና ላይ ያተኩራል። ቢቢሲ ከደራሲ ያዕቆብ ጋር የመሻገር ሲቃ ስራው ላይ አጭር ቆይታ አድርጓል።
ቢቢሲ- እስካሁን ካነበብኳቸው ያንተ ስራዎች ተነስቼ ስለ ሥነ ልቡና፣ ሥነ ተረክ (ሚቶሎጂ)፣ ታሪክ፣ ፍልስፍና በማንበብ ለራስህ እና በዙርያህ ስላለው ዓለም ትርጉም እንደምትሰጥ አስተውላለሁ። ከዚህ በመነሳት የመሻገር ሲቃ የንባብህ፣ የተብሰልስሎትህ ውጤት ነው ማለት ይቻላል?
ያዕቆብ- ንባብ ጥቂት ነገር ነው የሚሰጥህ። ወይንም ደግሞ የንባብ ስሪት ብቻ ከሆንክ ልክ አይሆንም። ንባብ ውስጥህ ያለውን አቅም፣ ውስጥህ ያለውን ብርሃን እንድታወጣው ያደርግሀል። የራስህን ፍኖት እንድትሰራ እንድታረቅ ያደርግሀል ማለት ነው። አንዳንድ ሰዎች ንባብ አላቸው ተምሰልስሎት (Meditation) የላቸውም። ንባብ የሸክላውን አፈር እንደ መሰብሰብ ነው። ተምሰልስሎት ደግሞ የሸክላውን አፈር ቅርጽ ሰጥቶ አስውቦ ለሚፈለገው ዓለማ ማዋል ነው። ወይንም የምትፈልገው ዓይነት ሸክላ ማድረግ ነው፤ ጥበብ ነው። ስለዚህ ንባብ ብቻውን በቂ አይደለም። . . . እንግዲህ የመሻገር ሲቃ የንባብ ውጤት ነወይ ላልከው ጥያቄ እኔ የንባብ ውጤት ነው አልልም። ንባብ የቀሰቀሳቸው ጥያቄዎች አሉ። ግን ብዙዎቹ ጥያቄዎች ውስጣችን ያሉ ናቸው። እንደ ‘ድራጎኑ’ ውስጣችን ያንቀላፉ ናቸው። ንባብ አንዳንዱን ደመነፍስህን ያነቃዋል። ያስደነብረዋል። ተምሰልስሎት ደግሞ ያንን የደነበረ ደመነፍስ፣ ማንነት ያሰክንልሀል። እና ከራስህ ከተፈጥሮ በዙርያህ ካለ ሁሉ ነገር ጋር ህብር እንድትፈጥር ያደርግሀል።
ቢቢሲ- የመሻገር ሲቃ ለሁሉም ተደራሲ ወይንም አንባቢ የቀረበ ነው ብለህ ታምናለህ? ወይስ እንዲያነብበው እንዲወያይበት የምትፈልገው ወገን ነበር?
ያዕቆብ- አላምንም። የመሻገር ሲቃ ለንባብ ከበቃ በኋላ እያስገረመኝ ነበር። እንደዚህ ማለት ልክ ላይሆን ይችላል እንጂ ከጻፍኳቸው መጻህፍት ሁሉ በጣም የተሻለ እና እኔንም የሰራኝ መጽሐፍ ነው። መጽሐፍቶቼን ካየሀቸው ተመሳሳይ ጭብጦች ናቸው የሚቀነቀንባቸው። እነዚያ ጭብጦች ግን በየጊዜው ከንባቤ፣ ከሕይወት አስተውሎቴ ከደረስኩበት ሁኔታ ጋር እያደጉ፣ እየጎለመሱ የሚሄዱ ናቸው።. . . እኔ ስጽፍ የምሸጠውን ኮፒ እያየሁ እያሰላሁ የማገኘውን ዝና፣ የሚቀርብልኝን ጭብጨባ እያሰላሁ አይደለም የምጽፈው። መጀመርያ ነገር እኔ ተሰምቶኛል ወይ? በጻፍኩት ነገር ረክቻለሁ ወይ? የሚለው ነው የሚቀድመው። ምክንያቱም የመጀመርያው ነገር ጥበቡ ሊሰራው የሚገባው ደራሲውን ነው። እንጂ የምትሸጠውን ኮፒ ብዛት እያሰብክ ከሆነ የምትጽፈው፣ ለአንባቢ ነው የምትጽፈው ማለት ነው። ስለዚህ የእነርሱን ጭብጥ ነው የምታስተጋባው። ምን ብጽፍለት አንባቢ እኔን ሊቀበለን ይችላል የሚለውን እያሰላህ ነው ማለት ነው የምትጽፈው። ያ ደግሞ ማለት አንተ ራስህ ‘ጄኒውን’ [እውነተኛ] ደራሲ አይደለህም። ያ ሲሆን ልትጨምርም አትችልም። ሸክም ነህ። መጽሐፍህም ለአንድ ሰሞን ተነብቦ፣ እንደ ጋዜጣ ታይቶ ይጠፋል። መሻገር አይችልም። ስለዚህ የመሻገር ሲቃ. . . ለነፍስ የተጻፈ ነው። ለአልፎ ሂያጅ አንባቢ የተጻፈ መጽሐፍ ነው ብዬ አላስብም። በነፍስ ከቀረብከው እና የቀደመ ልምምዱ ካለህ ይህንን መጽሐፍ ማጣጣም ይቻላል። ግን እኔ ስጽፈው ለጥቂቶችም ለብዙኀኑም ብዬ አይደለም የጻፍኩት። መጀመርያ ነገር መጻፍ የነበረብኝ ነገር ነበር። ያ ነገር እኔ ውስጥ ሲብላላ ቆይቷል-ለስምንት ዓመታት። ያንን ካልጻፍኩት ደግሞ ሌላውን መወጠን ስለማልችል እንጂ የምሸጠውን ኮፒ፣ ኅብረተሰቡ አንዴት ሊቀበለው ይችላል የሚለው አሳስቦኝ አያውቅም።
- ‘ሆሊውድ ለኔ ሀብትና ትምህርት ቤቴ ነው’ – ፍርቱና ገብረስላሴ23 ታህሳስ 2023
- ምሥሎች በሰው ሰራሽ አስተውሎት እንዴት ይሠራሉ? ከእውነተኞቹስ እንዴት መለየት ይቻላል?19 ታህሳስ 2023
- ‘የጠፉ መጽሐፍት አዳኙ’ ኤልያስ ሜክሲኮን እስከ ወዲያኛው ይሰናበታት ይሆን?10 ታህሳስ 2023
ቢቢሲ- ቃየን በመጽሐፉ የመጀመርያ ገጾች ላይ፣ ገጽ 11 ላይ ሞቶ ነው የሚጀምረው። ታሪኩ ዋና ገጸባህሪው ሞቶ እንዲጀምር፣ የአጻጻፍ ይትባሀሉ እንዲህ እንዲሆን የፈለግከው ለምንድን ነው?
ያዕቆብ – ይህንን ይኹነኝ ብዬ ያደረግኩት ነውበተለመደው የአጻጻፍ መንገድ መጻፍ አልፈለኩም።እንደ አንባቢም አንደ ደራሲም ሳየው የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ሦስት ዓይነት የአጻጻፍ ይትባህሎች ናቸው ያሉት። አንደኛው መንገድ አዳም እና እንደ እርሱ ነው መጻፍ የምንፈልገው የሚሉ ሰዎች የሚሄዱበት መንገድ ነው። ሁለተኛው መንገድ ደግሞ የ70ዎቹ ልብወለዶች የፖስት ሞደርኒዝም እና የሞደርኒዝም ቀለም ይዘው የሚዋዥቁት ናቸው። ሦስተኛው ደግሞ ትሪለር ዘውግ ነው። በርግጥ እኛ አገር ይህ ዘውግ እየከሰመ ያለ ነው። ግን 2000ዎቹ መጀመርያ ጀመሮ በጣም እየተጻፈበት የነበረ ዘውግ ነው። ግን ይህ ብቻ በቂ ነው ወይ ለእኛ አገር ሥነ ጽሑፍ? ሌላ አተያይ፣ የመተረክያ መንገድ መፍጠር ያስፈልጋል።
ለሌላው ዓለም አዲስ ላይሆን ይችላል ግን እኔ ስጽፍ የሆነ የራሴን መንገድ ማምጣት ፈለግኩ። . . . ስለዚህ ስጽፍ ይህንን ነገር አስቤዋለሁ። ቀጥተኛ በሆነ የአተራረክ መንገድ የሆነ ታሪክ ልተርክ አልፈልግም። . . . ምናልባት ይህንን መጽሐፌን ከእኛ አገር ሥነ ጽሑፍ ትንሽ ለየት ያደርገዋል ብዬ የማስበውም ለዚህ ነው። ቃየን ሞቶ እንዲጀምር ለምን ፈለግክ ላልከኝም አንባቢ እንዲያተኩር የፈለግኩት ሌላ ነገር ላይ ነው። ታሪክም አይደለም የጻፍኩት። ታሪክን የሚያነብ ሰው እኔን አንዲከተለኝም አልፈልግም። ታሪክን ማንበብ የሚፈልጉ ሰዎች ከፈለጉ መጽሐፉን ያቃጥሉት። እኔ የጻፍኩት ከዚያ ያለፈ ነገር ነው። መግብያዬ ላይም እንዳልኩት በስራ ፈት ለሚያዛጋ አእምሮ ቀለብ ይሆን ዘንድ አይደለም የተጻፈው። ይኼ በነፍስ ለመንካት ነው የተጻፈው።
ቢቢሲ- በዚህ የመሻገር ሲቃ ውስጥ ካሉ ዋና ገጸባህርያት አንዱ ቃየን ነው። ለመሆኑ ስሙን ቃየን ለምን አልከው?
ያዕቆብ- ቃየንንም ሆነ ህብረቀለምን ስማቸውን ስሰጣቸው አስቤ ሆነ ብዬ ነው ያደረግኩት።ህብረ ቀለምን፣ ህብረ ቀለም ስል ከእርሷ የነፍስ መጠራት ጋር ከስዕሎቿም ጋር የሚገናኝ ትርጉም አለው። የቃየን ነገር በአጠቃላይ የሰው ልጅ እጣ ፈንታን የሚወክል ሆኖ ነው የቀረበው። የሰው ልጅ ከገነት ወጥቶ ወደ ገነት የመመለስ መቃተት ውስጥ ነው ያለው። ይህ ክርስትያናዊ በሆነው አስተሳሰብ ነው። እኔ ግን በአንድ ቀኖናዊ አስተሳሰብ ብቻ የምረጋ ሰው አይደለሁም።
በአጠቃላይ ሚቲዮሎጂካል የሆነውን የሰው ልጅ እጣ ፈንታ ትርጉም መፈለግ ውስጥ ያለሁ ሰው ነኝ። ሀይማኖቶች ሚቲዮሎጂ ናቸው። የትኛውም ሀይማኖት ውስጥ የሆነ ዓይነት የጋራ የሆኑ ሚቲዮሎጂካል ሀሰቦች አሉ።. . . በመጽሐፍ ቅዱስ ቃየን ከተሳሳተ በኋላ ‘ያገኘው ሰው አይገድለው ዘንድ ምልክት አደረገበት’ ይላል። ምልክቱ ምን አንደሆነ ግን አይነግረንም። በርካታ ሰዎች ምልክቱ ምን እንደሆነ ልናውቅ አልቻልንም ይላሉ። ምልክቱ እንዲህ ነበር ብሎ ሊነግርህ የሚችል አታገኝም።
መጽሐፍ ቅዱስም፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ያሉ ሌሎች የትርጓሜ ጽሑፎች ውስጥ አታገኝም። እኔ ግን ለዚህ ነገር የሆነ ዓይነት የምናልባት መልስ መስጠት ፈለግኩ። ካየኸው ጥላ በመጽሐፉ ውስጥ እንደዛ ሆኖ ነው የመጣው። ጥላ ነበር ያደረገለት። ስለዚህ በሆነ ዓይነት መንገድ ቃየን የተሸከመው ርግማን አለ ማለት ነው። የሆነ ሕመም አለ ማለት ነው። ያ ሕመም ሰው በመሆን የተሸከምነው ሊሆንም ይችላል።
በአማርኛሥነ ጽሑፍ ውስጥ ስሞችን ሁሉ በአንድ ፊደል ብቻ የሚወክሉ ደራሲያን መጥተዋል። ስሞች በጣም ‘ፕሮፋውንድ’ ትርጉም አላቸው። የሆነ ስም ስትሰማ ወደ አእምሮህ የሚመጣ የሆነ ምስል አለ። ያ ምስል ስለ ግለሰቡ የምትይዘው የተሳሳተ ቅድመ ግምት ሊሆን ይችላል። ግን ስሞች የሚሰጡት ትርጉም አለ። ቃየን እና ያዕቆብ ስትል አንድ አይደለም። ካስተዋልክም በአገራችን ከመጽሐፍ ቅዱስ በርካታ ስሞች ይወጣሉ። እስካሁን ግን ቃየን ተብሎ የሚጠራ ሰው ገጥሞኝ አያውቅም። ምክንያቱም ቃየን የሚለው ስም የሆነ የተረገመ ዓይነት ተደርጎ ስለሚታሰብ ለልጆች አይመረጥም። ነገር ግን አቤል የሚባሉ በርካታ ሰዎች ታገኛለህ። ቃየን የተጣለ የተረሳ ስም ነው ማለት ነው። በሆነ በመንገድ ያንን መተው፣ መርገምት፣ ማንሳት መንካት ስለፈለግኩም ነው።

ቢቢሲ- በመሻገር ሲቃ ተደጋግመው ከሚመላሱ ሀሳቦች ውስጥ በዋናነት ‘መሻገር’ ነው። በዚህ መሻገር ውስጥ ደግሞ በትዕምርትነት መስኮት ተቀምጧል። በርግጥ ገጸባህሪዋ ህብረ ቀለም/ ሜቲኮ/ መስኮትን የሙጥኝ ማለቷ፣ ያንንም መስኮት ከጥቂት ቀናት በስተቀር ዘግታ አለማወቋ፣ ነጻነትን፤ መሻገርን ከመፈለግ ብቻ ነው ወይስ ሌላ መንገር የፈለግከው አለ?
ያዕቆብ – ይህንን መጽሐፍ ለመረዳት ልትመዛቸው ከሚገቡ አንጓዎች መካከል አንዱ መስኮት ነው። . . . ይህንን መጽሐፍ ካየሀው በመስኮት ተጀመሮ በመስኮት ነው የሚያልቀው። ግን ሲጀመር ያለው መስኮት እና ሲጨርስ ያለው መስኮት የተለያዩ ናቸው። ሲጀመር አሁን ጥያቄህ ላይ እንዳነሳኸው ህብረ ቀለም በመስኮት ቆማ የሆነ ዓይነት ‘ኖስታልጂክ’ የሚመስል ስሜት ስታስተናግድ፣ ከመስኮቱ ጋር የሆነ ዓይነት ቅርርብ ሲኖራት እናያለን፤ ስትተኛ እንኳ መስኮቷን የመዝጋት ፍላጎት የላትም። ግላዊ የሆኑ ነገሮችን ስታከናውን እንኳ መስኮቷን የመዝጋት ፍላጎት የላትም። ምናልባት ገርበብ ብታደርገው ነው። መጽሐፉ በሁለት ክፍል የሚተረክ ነው እንዳነበብከው እና ሲያልቅ ደግሞ እርሷ መስኮቷን ትዘጋለች። ነገር ግን የከፈተችው መስኮት አለ። ይህኛውን መስኮት ዘጋችው እንጂ የሕይወቷን መስኮት ከፍታለች። ለሕይወት ‘ኤክስፖዝድ’ ሆናለች። ሂደቱን ጨርሳለች ወይ አላውቅም። ማንበብ ያስፈልጋል። ለቃየን በረከት ሆነው የመጡት ነገሮች ለእርሷ ግን አሳዳጅ ሆነው መጥተዋል። እነዚህ ሁሉ ነገሮች መነበብ አለባቸው። ዝም ብለህ ታሪኩን ልትዝናናበት የምታነብበው ከሆነ ብዙውን ነገር ልትስት ትችላለህ።
ሲያልቅ ቃየን የመጨረሻዎቹን ታሪኮች መስኮት ላይ ቆሞ ነው የሚተርከው። አይከል ከተማ ውስጥ የሆነች ጠባብ ክፍል ውስጥ፣ ተከፍታ የማታውቅ መስኮትን ከፍቶ፣ በዚያ ውስጥ ግን ሁሉንም አያለሁ ነው የሚለው። እስከ ባቢሎን፣ እስከ የአረብ በረሃዎች ድረስ ሁሉንም አያለሁ። በሁሉም ውስጥ አለሁ ነው የሚለው፤ ሁሉም በእኔ ውስጥ አለ ዓይነት ሀሳብ ያነሳል። ስለዚህ በዚህ ልብ ወለድ ውስጥ መስኮት ዋናው ‘ሜታፈር’ ነው። እንዲህ ለማለት ፈልጌ ነው እንዲያ ለማለት ፈልጌ ነው ካልኩኝ፣ ጭብጡን እገድለዋለሁኝ፣ የአንባቢውን ምናብ አኮሰምነዋለሁ። መስኮቱ ግን የሚነበብ ነው። እርሱ ብቻ ግን አይደለም። ሌሎችም አሉ።
ቢቢሲ- ህብረ ቀለም ለአንዳች ትልቅ ነገር እንደተጠራች ቃየን ደጋግሞ ይነግራታል። ለመሆኑ ህብረቀለም የተጠራችበት ያ ትልቅ ነገር ምንድን ነው?
ያዕቆብ-. . . መጽሐፉ ውስጥ እኮ ተመልሷል ይህ ነገር። ቃየን ሁሉም ሰው ተጠርቷል ይላታል። ሁሉም ሰው የሆነ ተዓምር የመፍጠር እምቅ ችሎታ ውስጡ አለ። . . . እያንዳንዳችን ውስጥ ያንቀላፋ፣ እንድናነቃው የሚጠብቅ ስናነቃው የሚጠቅመን፣ ሊያሻግረን የሚችል ‘ድራጎን’ አለ። ቃየን እያደረገ ያለው እርሷ ውስጥ ያለውን ‘ድራጎን’ ማስደንበር ነው። ያንን ለማስደነንበር ደግሞ የምታቋርጠው የራሷ በረሃ አላት። ሕ
ህብረ ቀለም ያንን በረሃ ለማቋረጥ ከነበረችበት ‘ኮምፈርት ዞን’ [ምቾት] እንድትወጣ ማድረግ ነበረበት። ለማድረግ የሞከረው ያንን ነው። ለአስር ዓመት ያህል የሳለቻቸውን ስዕሎች ሲያቃጥል የምናነብበውም ለዚያ ነው። ያ ትልቅ ‘ሾክ’ ነው። በኋላም እርሷ ስትል እንደምናነበው ሰዓሊ ብቻ ሳይሆን፣ ሰው የሆንኩት ከዚያ ሕመም ነጻ ስወጣ ነው ትላለች። ያ በረሃ ግን በቂ አይደለም። ይህ ሁሉ ሆኖ እንኳ፣ ራሷ ተሻግራ አልተሻገረች ይሆናል። . . . የመጀመርያው ነገር የሰው ልጅ ሁሉ የተጠራበትን ነገር ራስን ማግኘት ነው። ዋናው ግኝት የሰው ልጅ የተጠራበትን ራሱን ማግኘት ነው። በሚቶሎጂ ይህ ዓይነት ጭብጥ ተመላልሶ የሚተረክ ነው። ሰው ከተፈጥሮ ቅኝት ተነጥሏል። ወደ ተፈጥሮ ቅኝት የመመለስ መቃተት ውስጥ ነው ያለው። እና ህብረ ቀለም ለዚህ ጉዳይ ነው የተጠራችው የሚል አንድ ነጠላ ጭብጥ ለማስቀመጥ አንችል ይሆናል። ማስቀመጥም ትክክል አይመስለኝም።
ቢቢሲ- በተለያዩ ሥነ ጽሑፋዊ ስራዎች ውስጥ ራስን በመፈለግ፣ ለአንዳች ተልዕኮ በመላክ ውስጥ የምናየው ወንዶች ጀግኖችን ነው። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ደግሞ ህብረቀለምን እናገኛለን። አንተ ከተለመደው ወጣ ብለህ ሴት ጀግና/ ተጋዳሊት መፍጠር ፈልገሃል?
ያዕቆብ- መጽሐፉ ሴቴ እና ወንዴ ቀለም ነው ያለው። የመጀመርያው ክፍል በሴቷ ነው የሚተረከው። ሴቴ ቀለም ነው ያለው። የበለጠ ለልብ የሚቀርብ ዓይነት ነው። ሁለተኛው ክፍል ደግሞ በቃየን የሚተረከው ነው። እርሱ ደግሞ ካየሀው የበለጠ ለአእምሮ የሚቀርብ ነው። በተለየ ሁኔታ የሆነች ጀግና ሴት በአማርኛ ሥነ ጹሑፍ ውስጥ ላስነሳ ብዬ አይደለም የተነሳሁት። በቃ የሆነ ልጽፈው የሚገባኝ ጭብጥ ነበር። ልብወለድ ሌላ ነገር አይደለም። የአንተ የራስህ ፕሮጀክሽን ነው። አንተ ውስጥ የሚብላላውን ነገር በአንተ ኢ-ንቁ አእምሮ ውስጥ ያለውን የራስህን ምስል ነው የምትጽፈው። አንተ ደግሞ አንድ ብቻ አይደለህም። እያንዳንዱ ሰው ሴቴ እና ወንዴ ማንነት አለው። በተለየ ሁኔታ የሆነች ጀግና ሴት ልፍጠር ብዬ ተነስቻለሁ ብዬ አላስብም። ግን ደግሞ በሴት አንደበት ሊተረክ የሚገባው ታሪክ እንዳለ ገብቶኛል።
አንደኛ ነገር ህብረ ቀለም ባትኖር ቃየንም ቃየንን መሆን አይችልም ነበር። እንደውም እርሱ ያልነገረን ስለ እርሱ በርከታ ነገር አንድናውቅ ያደረገችን እርሷ ናት። ስለ እርሱ ስትነግረን ደግሞ ስለ ራሷም እየነገረችን ነበረ። ስለዚህ አንዱ ያለ አንዱ ብቻቸውን መቆም ይችላሉ ወይ? አይችሉም። .. .. .. ከእያንዳንዱ የጀግንንት ተግባር ወይንም ደግሞ ከእያንዳንዱ ጀግና ጀርባ ያንን ጀግንነት ያንን ታላቅነት፣ ያንን ስኬት ለማግኘት የተኬደበት በርካታ የሕመም ጉዞ አለ። ስለዚህ ሕብረ ቀለም ያለ ሕመም ልትሰራ አትችልም። እርሷም የምትለው ያንን ነው። ቃየንም ደጋግሞ የሚነግራት ሕመም ያስፈልግሻል። ሕመም ነው የሚፈጥርሽ እያለ ነው። ቡድሂስቶችም እንደሚሉት ዓለም ሕመም ነች። እያንዳንዱ ነገር ሕመም አለው። ግን ደግሞ ከሕመሙ ተደብቀው የ’ኮምፈርት ዞን’ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች አሉ። እርሱ ከዚያ ነው ሊያወጣት የፈለገው። በተለየ ሁኔታ በሴት አንደበት ልተርከው የሚገባኝ ታሪክ ነበረኝ። የሴት ጀግና ልፍጠር ብዬ ግን አልተነሳሁም። እንደዛም ካደረግኩ ልክ ነኝ ብዬ አላስብም፤ ሜካኒካል ነው የሚሆነው።
- “በወንድ ደራሲያን በሚገባ ተስለናል ብዬ ስለማላስብ ነው ስለሴቶች በትኩረት መጻፍ የፈለግኩት” ቤዛዊት ዘርይሁን3 ታህሳስ 2023
- የጦርነት ዳፋ የመጨረሻው ውጤት የሚታየው ጦር ሜዳ ላይ ሳይሆን ቤተሰብ ውስጥ ነው – ይፍቱሥራ ምትኩ12 ህዳር 2023
- “የሥነ ጽሑፍ ሥራዎቼ የፈውሴ ምንጭ ናቸው” ትዕግሥት ሳሙኤል22 ጥቅምት 2023

ቢቢሲ- ህብረቀለም ትረካውን ስትጀምርልን እድሜዋ 27 ነው። መጽሐፉ ላይ ከ12 ዓመት በፊት በ15 ዓመቷ ለመጀመርያ ጊዜ ጥላ እንዳየችአንድ ቦታ ላይ እናነባለን። እርሱን በመደመር ነው ይህንን ማለት የምንችለው። ለመሆኑ በዚህ ዕድሜዋ ላይ ታሪኩ እንዲጀምር የፈለግክበት ምክንያት አለ?
ያዕቆብ- በነገራችን ላይ 27 መሠረታዊ ቁጥር ናት።. . . የሰው ልጅ ከ27 እስከ 30 ባለው እድሜ ውስጥ ነው ለሆነ ዓይነት፣ ለተለየ ከራሱ ላለፈ ወይንም ከራሱ ለሚልቅ ዓላማ የሚጠራው። . . . ለምሳሌ ኢየሱስ ከዓለም ተነጥሎ ወደ ተራራ ወጥቶ መጸለይ የጀመረው፣ መስበክ የጀመረው 30 ዓመት ከሞላው በኋላ ነው። ሌሎች ትልልቅ የምትላቸው ሰዎችም የሆነ ዓይነት ውስጣቸው ያለውን እምቅ ችሎታ ማግኘት የጀመሩት 27 ሲሞላቸው ነው። ቫን ጎ ለምሳሌ 27 ዓመት ሲሞላው ነው ሰዓሊነት ያገኘው። እስከ 27 ዓመቱ ማንነቱን ለማግኘት ሲቃብዝ የነበረ ሰው ነው። ሚካኤል አንጀሎ ‘The creation of Adam’ን፣ በጣም ዓለም ሁሉ የሚደነቅበት እርሱንም በከፍታ ላይ ያስቀመጠውን ስራውን የሰራው 30 ዓመት እድሜው ላይ ነው።
ሌሎችም በርካታ ሰዎችን ልትጠቅስ ትችላለህ። የኒቼ ዛራቱራ 30 ዓመት ሲሞላው ከዓለም ተነጥሎ ወጣ ለዓለምም እውነት ሊሰብክ ወጣ የሚል ሀሳብ ያነሳል። የቡድሀን ታሪክ ውሰድ 30 ዓመት ሲሞላው ነው ከቤተመንግሥት ኮብልሎ ወጥቶ መገለጥን ፍለጋ (enlightenment ) በመናፈቅ ወጣ የሚልህ። ስለዚህ ከ27 እስከ 30 በጣም ወሳኝ ቁጥር ነው።
ከዚህ በተጨማሪም በሚስቲሲዝም ዓይን ስታይ የሰው ልጅ ሕይወት ሦስት የ27 ዓመታት እድሜ ነው ያለው ነው የሚባለው። የመጀመርያው 27 ዓመት አካል የሚጎለምስበት ነው። ሁለተኛው 27 ዓመት አእምሮ የሚጎለምስበት ነው። ሦስተኛው 27 አካልና አእምሮ ተሰናስለው ያንን ሰው የሚገሩበት እድሜ ነው። በእነዚህ ሦስት 27 ዓመታት በሚገባ የተሰራ ሰው ሦስቱን 27 ዓመታት ከጨረሰ ወዲያ ልክ እንደ ‘ዲቫይን ቢንግ’ የሆነ ዓይነት አምላክ አከል የሚመስል ሰው ነው የሚሆነው። . . . 27 ዓመት ነፍስ ከመለኮት እስትንፋስ አካል ከለበሰች በኋላ የረሳችውን የመለኮት እሳት ለመጀመርያ ጊዜ የምትገናኝበት እድሜ ነው። ከ27 እስከ 30 ያለችው እድሜ በጣም ወሳኝ ወቅት ናት። በዚያ ወቅት የምታሳያቸው ነገሮች፣ ያችን ወቅት የምትይዝባቸው መንገዶች ያንተን የወደፊት ዕጣ ፈንታ እስከ መወሰን አቅም አለው። ህብረ ቀለም ውስጥ ብቻ ሳይሆን ቃየንም ውስጥ ይህንን ቁጥር ብትፈልግ ልታገኘው ትችላለህ።
ቢቢሲ- በመሻገር ሲቃ ልብ ወለድ ውስጥ የሚፈከሩት ሃሳቦች እና ትዕምርቶች ብዙ ናቸው። አንዱ የህብረ ቀለም የካ ተራራን መውጣት መሻት ነው። ተራራ መውጣትን በልጅነቷ አባቷ ትከሻቸው ላይ እሽኮኮ አድርገውት ካለው ጋር አነጻጽራ ትነግረናለች። የህብረ ቀለም ተራራ የመውጠዓት ፍላጎት ምን ይነግረናል?
ያዕቆብ-. . . ተራሮች ትዕምርቶች ናቸው። ‘ፕሮፋውንድ’ የሆነ ትርጉም ነው ያላቸው። በህልምህም ተራራ ስትወጣ ካየህ ወደ ግብ ህልምህ እየተጠጋህ መሆንህ ነው የሚነገረው። ተራሮች የጥንካሬ ምልክት ናቸው። wonderer above the sea of fog የተሰኘውን የካስፐር ዴቪድ ፍሬድሪክ ስዕል ብታየው፣ የሳለው ሰው ተራራ ላይ ነው የቆመው። ጭጋጉ ሁሉ ሌላው ሁሉ ያለው ከእርሱ በታች ነው። ከግሳንግሱም፣ ከጭንቀቱም ሁሉ በላይ ሆኖ በኩራት ቆሞ ነው የምታየው። በትዕምርት ተራራ ላይ መውጣት ማለት ሁሉንም ፈተናዎች ማሸነፍ ማለት ነው። በመንፈስም በአካልም በአእምሮም፣ በኢኮኖሚም፣ በኃይልም በሁሉም ነገር መሻገር ነው። ተራራ ትዕምርት ነው። ይህንን ጭብጥ ከዚህ በፊትም ደጋግሜ የጻፍኩት ጭብጥ ነው። ምናልባትም ሙሉ በሙሉ የተውኩት ስላልሆነ ይሆናል እዚህ መጽሐፍ ውስት መልሼ ያካተትኩት።