London

ከ 7 ሰአት በፊት

የለንደን ከተማ ፖሊስ ትናንት ቅዳሜ ታኅሣሥ 20/2016 ዓ.ም. በደቡባዊ የከተማዋ ክፍል በተከሰተ ሁከት ላይ የተሳተፉ 8 ኤርትራውያንን ማሰሩን አስታወቀ።

ፖሊስ ጨምሮ እንደገለጸው በትናንቱ ሁከት አራት አባላቱ ጉዳት እንደደረሰባቸው እና በንብረት ላይም ውድመት አጋጥሟል።

ፖሊስ ኤርትራውን ተሳታፊ ሆነውበታል ባለው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ በተነሳው ሁከት አንድ የፖሊስ አባሉ በደረሰበት ጉዳት ሆስፒታል መግባቱን ጨምሮ አስታውቋል።

ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የወጡ ምስሎች ካምበርዌል በተባለ በደቡባዊ ለንደን በተከሰተው ግጭት ተቃዋሚዎች በዱላ የፖሊስ አባላትን ሲማቱ እና የፖሊስ ተሸከርካሪዎችን ሲያዋድሙ ታይተዋል።

የለንደን ፖሊስ ክስተቱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ የተቃውሞ ሰልፉ “በኤርትራ ማኅብረሰብ ውስጥ ባለው ውጥረት” የተከሰተ ነው ከማለት ውጪ የግጭቱ መነሻ እና ተሳታፊዎቹን በተመለከተ የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።

ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደም በበርካታ የአውሮፓ እና የአሜሪካ ከተሞች ከኤርትራ የባሕል ፌስቲቫል ዝግጅት ጋር ተያይዞ በርካቶችን ለጉዳት እና ለእስር የዳረገ ግጭት ሲከሰት ቆይቷል።

በተለይ በእስራኤል፣ ጀርመን፣ ኖርዌይ እና ካናዳ ያጋጠሙ ግጭቶች በሰልፈኞች እና በጸጥታ አስከባሪዎች ላይ ጉዳት አስከትለዋል።

የመንግሥት ደጋፊ ናቸው የሚባሉ ኤርትራውያን ከኤምባሲ ጋር በመተባበር የሚያዘጋጁት የባሕል ፌስቲቫል ለኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት ገንዘብ ማሰባሰቢያ ሥነ-ስርዓቶች ናቸው በማለት ተቃዋሚ ኤርትራውያን ፌስቲቫሎችን ለማወክ በሚያደርጉት ጥረት ሁከት ሲፈጠር ቆይቷል።

ኤርትራን እየገዙ ባሉት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አገዛዝ ላይ ከዚህ ቀደም በዳያስፖራው ተቃውሞዎች ቢሰሙም ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ግን መልኩን እየቀየረና በደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች መካከል በሚፈጠሩ ግጭቶች ደም መፋሰሶች እየታዩ ነው።

ትናንት በደቡብ ለንደን በተከሰተ ግጭት 50 ያክል ሰዎች ተሳታፊ እንደሆኑበት ፖሊስ አስታውቋል።

ፖሊስ ጨምሮም በአንድ ስፍራ ሥነ-ስርዓት ለማካሄድ ጥያቄ አቅርቦ ከነበረ ቡድን ጋር አብሮ ሲሳራ መቆየቱን ገልጾ፤ በቁጥጥር ስር የዋሉት ግን የሌላ ቡድን አባላት ናቸው ብሏል።

ፖሊስ ክስተቱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ በአመጽ በመሳተፍ፣ በንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ፣ ጉዳት የሚያስከትል መሳሪያ በመያዝ እና በጸጥታ አስከባሪ ሠራተኞች ላይ ጉዳት ማድረስ ወንጀሎች የተጠረጠሩ 8 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ብሏል።

ፖሊስ ጨምሮም በስፍራው የነበረው የተቃውሞ ሰልፍ ቅዳሜ ምሽት ላይ ሙሉ በሙሉ መበተኑን አስታውቋል።