ኪም ጆንግ ኡን
የምስሉ መግለጫ,ኪም ጆንግ ኡን

ከ 9 ሰአት በፊት

ሰሜን ኮሪያ በአውሮፓውያኑ 2024 ተጨማሪ ሦስት የስለላ ሳተላይቶችን ለማምጠቅ ማቀዷን አስታወቀች።

ሰሜን ኮሪያ ባለፈው ወር ያመጠቀችው የስለላ ሳተላይት የአሜሪካ እና የደቡብ ኮሪያ የጦር ሰፈሮችን ፎቶግራፍ ማንሳቱን አስታውቃለች።

ኪም ጆንግ ኡን የሰሜን ኮሪያ ሠራተኞች ፓርቲ የዓመቱ መዝጊያ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር ከደቡብ ኮሪያ ጋር የመዋሃድ አማራጭ ከአሁን በኋላ ተፈጻሚ የሚሆን አይደለም ብለዋል።

ኪም ጆንግ ኡን በንግግራቸው ጎረቤት አገር ደቡብ ኮሪያ አገራቸው ሰሜን ኮሪያን እንደ ጠላት አገር አድርጋ ነው የምትመለከተው ብለዋል።

ምንም እንኳ ሁለቱ ኮሪያዎችን ለማዋህድ ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ እርምጃ ተወስዶ ባያውቅም ኪም ከደቡብ ኮሪያ ጋር የመሃዋድ አማራጭ የለም በማለት ለመጀመሪያ ጊዜ መናገራቸው የአገራቸውን አቋም የሚያንጸባርቅ ጠንካራ ንግግር ተደርጎ ተወስዷል።

በሁለቱ ኮሪያዎች መካከል ያለው ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ውጥረት እየተሞላበት መጥቷል። ባለፈው ወር ፒዮንግያንግ የስለላ ሳተላይትን ማምጠቋ ሁለቱ አገራት ወታደራዊ ውጥረትን ለመቀነስ የደረሱትን ስምምነት የሚጥስ ተግባር ተደርጎ ተወስዷል።

ከዚህ በተጨማሪም ሰሜን ኮሪያ በተጠናቀቀው 2023 የተለያዩ አይነት ሚሳኤሎችን ለሙከራ ስታስወነጭፍ ቆይታለች። ባለፈው ወር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እግዶችን በመተላለፍ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ውጤቷ የሆነውን ረዥም ርቀት የሚምዘገዘግ ሚሳኤል ለሙከራ አስወንጭፋለች።

ይህ የሰሜን አሜሪካ ከተሞችን ሊመታ የሚችለው ሚሳኤል ለሙከራ መተኮሱ ምዕራባውያንን በእጅጉ ያስቆጣ ነበር።

በሌላ በኩል ደቡብ ኮሪያ ከአሜሪካ ጋር ወታደራዊ ትብብሮችን ማድረጓ ፒዮንግያንግን አላስደሰተም። በቅርቡ የኒውክለር ጦር መሳሪያዎችን የታጠቀ የአሜሪካ ሰርጓጅ መርከብ ወደ ሁለቱ ኮሪያዎች የውሃ ክልል አቅራቢያ ተጠግቷል።

ኪም በንግግራቸው “ግድ የለሽ በሆነው የጠላት እንቅስቃሴ በየትኛውም ሰዓት ጦርነት እንዲቀሰቀስ ሊያደርግ ይችላል” ስለማለታቸው የአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዝግቧል።

ኪም 2024 አገራቸው ብዙ ጦር መሳሪያዎችን የምታመርትበት፣ የኒውክለር እና የሚሳኤል ኃይሏን የምታጠናክርበት እንዲሁም ሰው አልባ አውሮፕላኖችን የምታመርትበት ዓመት ይሆናል ብለዋል።

የሰሜን ኮሪያው መሪ “ሊፈጠር ለሚችል የኒውክለር ቀውስ በፍጥነት ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀት አለብን” ስለማለታቸውም ተዘግቧል።