
December 31, 2023

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የንግድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ለማ ያዴቻ
የኤርፖርት ከተማው በፈጣን የባቡር መስመር ከቦሌ ኤርፖርት ጋር ይገናኛል ተብሏል
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) አቦሴራ በሚባል ሥፍራ ለመገንባት ላሰበው ግዙፍ የኤርፖርት ከተማ፣ የጠየቀውን የመሬት ይዞታ በቅርቡ ከክልሉ መንግሥት እንደሚረከብ አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና የንግድ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ለማ ያዴቻ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት አቦሴራ በሚባል ሥፍራ የሚገኙ ነዋሪዎችን ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመሆን እያስነሳ ነው፡፡
የአየር መንገድ ግሩፕ በቢሾፍቱ የሚገኘውን አቦሴራ በመባል የሚጠራውን የግንባታ ቦታ ከተረከበ በኋላ፣ በፍጥነት ግንባታውን እንደሚጀምር አቶ ለማ ገልጸዋል።
የሚገነባው የኤርፖርት ከተማው ከ38 እስከ 40 ካሬ ኪሎ ሜትር በሚሆን ቦታ ላይ እንደሚያርፍም አስረድተዋል፡፡
የኤርፖርት ከተማው ግንባታ በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅና ፕሮጀክቱ ከዛሬ አራትና አምስት ዓመት በፊት በተጠናበት ወቅት የአጠቃላይ ግንባታው ወጪ አምስት ቢሊዮን ዶላር እንደሚሆን ተሰልቶ የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ወጪው ከዚያ በላይ ሊሆን እንደሚችል አክለው ገልጸዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ግንባታ በምን ያህል ወጪ ይጠናቀቃል የሚለው ሲታወቅ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች መግለጫ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡
የኤርፖርት ከተማ ግንባታው በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ የሚከናወን መሆኑን የተናገሩት ሥራ አስፈጻሚው፣ ግንባታው ሲጠናቀቅ አውሮፕላን ማረፊያው በአንድ ጊዜ እስከ 200 አውሮፕላኖች የማቆም አቅም ይኖረዋል ብለዋል፡፡
የኤርፖርት ከተማው በቀጥታ ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ጋር በፈጣን ባቡር የሚገናኝ መሆኑን፣ የኤርፖርት ከተማው ዲዛይንም በአሁኑ ጊዜ በመዘጋጀት ላይ እንደሆነ ገልጸዋል።
በዚህ መሠረት የኤርፖርት ከተማውን ግንባታ ለማከናወን የሕንፃ ተቋራጮችን ለመምረጥ ጨረታ መውጣቱን ጠቅሰው፣ የሕንፃ ተቋራጮችን ለመምረጥ አየር መንገዱ ከአማካሪዎች ጋር እየተነጋገረ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በአዲስ አበባ የሚገኘው ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ሲሠራ 19 ሚሊዮን ሰዎች በዓመት የማስተናገድ አቅም እንዲኖረው ተደርጎ መሆኑን የገለጹት አቶ ለማ፣ ኤርፖርቱ በቅርቡ ማስፋፊያ ከተደረገለት በኋላ ግን በዓመት ከ22 ሚሊዮን በላይ መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ማግኘቱን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ2015 በጀት ዓመት 14 ሚሊዮን መንገደኞችን ማስተናገዱን፣ በዘንድሮ በጀት ዓመት ደግሞ 18 ሚሊዮን መንገደኞችን ለማስተናገድ አቅዶ እየሠራ መሆኑን የአየር መንገዱ መረጃዎች ያመለክታሉ።
የአየር መንገዱና የደንበኞቹ ዕድገት በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ከመሆኑ አኳያ የቦሌ ኤርፖርት በአጭር ዓመታት ውስጥ የአየር መንገዱን አጠቃላይ ደንበኞች የማስተናገድ አቅም እንደማይኖረው፣ በመሆኑም የአየር መንገዱን ዕድገት ያገናዘበ አዲስ ኤርፖርት መገንባት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ለማወቅ ተችሏል።
በዚህም መሠረት ከቢሾፍቱ ከተማ ወጣ ብሎ አቦሴራ በተባለ ሥፍራ በዓመት ከ80 ሚሊዮን በላይ መንገደኞችን ማስተናገድ የሚችል አዲስ የኤርፖርት ከተማ የመገንባት ውጥን ተይዟል። የሚገነባው አዲሱ ኤርፖርት መንገደኞችን ከማስተናገድ ባለፈ ዘመናዊ ሆቴሎች፣ ከቀረጥ ነፃ የግብይት ሥፍራና የካርጎ ሎጂስቲክስ ማዕከል እንደሚኖረው ታውቋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እ.ኤ.አ. በ2035 በዓለም የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ምርጥ 20 አየር መንገዶች አንዱ ለመሆን ዕቅድ ይዞ እየሠራ ሲሆን፣ ይህንን ዕቅድ ዕውን ለማድረግ ይረዳው ዘንድም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በቅርቡ የአየር መንገዱን ካፒታል ከ100 ቢሊዮን ብር ወደ 300 ቢሊዮን ብር ከፍ ማድረጉ ታውቋል።