EthiopianReporter.com


ዜና
ለሚኒስትሯ የመኖሪያ ቤት ዕድሳት ከራሱ በጀት የተጠቀመው የቱሪዝም ሚኒስቴር ገንዘቡን ተመላሽ እንዲያደርግ…

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን: December 31, 2023

ቀድሞው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ይባል የነበረው ከጥቅምት 2014 ዓ.ም. ወዲህ ራሱን ችሎ እንዲቋቋም የተደረገው የቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሸን ለሚኒስትሯ ወ/ሮ ናሲሴ ጫሊ ለተሰጠው መኖሪያ ቤት ከራሱ በጀት ለጥገና በማለት ያወጣውን 431 ሺሕ ብር ተመላሽ እንዲያደርግ የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡

ማሳሰቢያው የተሰጠው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የቱሪዝም ሚኒስቴርን የ2014/15 ዓ.ም. በጀት ዓመት የሒሳብ ኦዲት ሪፖርት ታኅሳስ 17 ቅን 2016 ዓ.ም. ሲገመግም ነው፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ምንም እንኳ ለክብራቸው የሚመጥን መኖሪያ ቤት የሚገባቸው ቢሆንም፣ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱም ከፋይናንስ መመርያ ውጪ በውስን ጨረታ ለአሸናፊ ድርጅት በመስጠት ቤቱን ማሳደሱን፣ ይህም የመንግሥትን ውስን ሀብት ከታለመለት ዓላማ ውጪ ማዋቡን እንደሚያሳይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ሪፖርት ያስረዳል፡፡

በግምገማው ወቅት ቋሚ ኮሚቴው በፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የተሰጠን ቤት በኮርፖሬሽኑ ማስጠገን ሲገባው፣ ለተቋሙ ኃላፊ በሚል ያላግባብ ከመመርያ ውጪ ግዥ ለምን ፈጸመ ሲል ማብራሪያ ጠይቋል፡፡

 የፌዴራል ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ለሚኒስትሯ የሚመጥናችው ቤት መሰጠት ያለበት ቢሆንም፣ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የሚኒስትሯን ክብር ጠብቆ ማቅረብ ነበረበት ብለዋል፡፡ ቤቱ መጠገን ከነበረበትም በአከራይና በተከራይ ሕግ ውል አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት ኮርፖሬሽኑ ጠግኖ ማቅረብ እንደነበረበተ አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም ገንዝብ ሚኒስቴር የቤት ጥገናን በተመለከተ ምንም ዓይነት መመርያ ባላወጣበት ወጪ የተደረገው ገንዘብ መመለስ አለበት ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የቱሪዝም ሚኒስትሯ በበኩላችው ቤቱን ሲረከቡ ጉዳዩን ለፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በደብዳቤ መጠየቃቸውን ገልጸው፣ ‹‹ቤቱ ጣሪያው የሚያፈስ፣ እጅግ ለኑሮ በጣም አስቸጋሪ፣ ግድግዳው በጣም የበሰበሰ፣ የመኖሪያ ቤት ለማስመሰል ጥገና የተደረገለት እንጂ ተገቢ ጥገና የተደረገለት አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ የተሰጣቸው ቤት መጠነ ሰፊ ችግሮች ያሉበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ችግሩ አሁንም የቀጠለ በመሆኑ መፍትሔ የሚያስፈልገው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከዋና ኦዲተር የተሰጠውን አስተያየት በመቀበል፣ ‹‹ቤቱ ችግር ቢኖርበትም በተለየ መንገድ ችግሩን ለመፍታት እየሞከርን ነው፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ፣ ቤቱ ለምን ታደሰ ባይባልም አንድ አካል ቤት ሲያከራይ ቤቱ ለመኖሪያ ብቁ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርበታል ብለዋል፡፡ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ምን ይሠራል? ይህ ባልሆነበት በእጃችን ገንዘብ ስላለ ብቻ፣ በገንዘብ ማዘዝ ስለምንችል ብቻ፣ ሕግ ሳይፈቅድ የምንሠራቸው ሥራዎች የመንግሥትን በጀት ለብተናና ለብክነት የሚያጋልጡ በመሆናቸው ተጠያቂነት ያስከትላል፤›› ሲሉም ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ ገንዘብ ሚኒስቴር ለመሰል ጉዳዮች የሚረዳ መመርያ እንዲያዘጋጅ አሳስበዋል፡፡

ምክትል ሰብሳቢዋ ለቤት ዕድሳት የወጣው ወጪ በሕጉና በውሉ መሠረት መፈጸም ያለበት በመሆኑ፣ በክስም ሆነ በተፈለገው መንገድ ገንዘቡ ተመልሶ ሪፖርት እንዲደረግ አሳስበዋል፡፡

በተጨማሪም የፌዴራል ዋና ኦዲተር የኦዲት ግኝት እንደሚያሳየው ሪፖርቱ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ለመሥሪያ ቤቱ ኃላፊዎች ሾፌሮች፣ ታሜጋስ ከተሰኘ ድርጅት በተጋነነ ዋጋ የአልባሳት ግዥ መፈጸሙ ጥያቄ አስነስቶበታል፡፡

ለሾፌሮች ከተገዙት አልባሳት ሙሉ ልብስ የአንዱ ዋጋ 32,500 ብር፣ የሙሉ ልብስ አላባሽ ጫማ የአንዱ ዋጋ 13,500 ብር፣ ሸሚዝ የአንዱ ዋጋ 1,350 ብር፣ ከራባት የአንዱ ዋጋ 1,750 ብር፣ ቀበቶ የአንዱ ዋጋ 1,950 ብር፣ እንዲሁም ካልሲ የአንዱ ዋጋ 450 ብር ናቸው፡፡

የሚኒስቴሩ የሥራ ኃላፊዎች በሰጡት ማብራሪያ በውስጥ መመርያ አማካይነት ግዥ መፈጸሙን ገልጸው፣ በ2015 ዓ.ም. በተሰጠው የማስተካከያ መመርያ መሠረት ለአልባሳት ግዥ ገደብ እንዲወጣ ተጠይቆ አሁን ገደብ ተደርጓል ብለዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ወ/ር አለሌ በማጠቃለያ አስተያየታቸው፣ ‹‹በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ መመርያ የተባለ ነገር አይሠራም፣ የፋይናንስ ሕግ ያለም አይመስልም፣ የፈለገ ሰው እንደ ፈለገ ይገዛል፣ የፈለገ ሰው እንደ ፈለገ ይከፍላል፣ የፈለገ ሰው እንደ ፈለገ ያደርጋል፣ ሕግ የሚባል ነገር የሚሠራ አይመስልም፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም፣ ‹‹ሕግ ያስፈለገው ሕጉን እንድናስተዳድርበትና እኛም እንድንገዛበት በመሆኑ በፋይናንስ ክፍሉ ላይ አስተዳደራዊ ዕርምጃ ተወስዶ ሪፖርት ይደረግልን፤›› በማለት አስታውቀዋል፡፡