EthiopianReporter.com


የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ

ዜና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ለረሃብ አደጋ ዓለም አቀፍ ጥሪ አቀረበ

ዮናስ አማረ

ቀን: December 31, 2023

በትግራይ ክልል ወደ 91 በመቶ ሕዝብ ለረሃብ አደጋ መጋለጡን ያስታወቀው ጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ ለረሃብ አደጋው ዓለም አቀፍ ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቀረበ፡፡ የረሃብ አደጋው ከክልሉ በላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዓርብ ታኅሳስ 19 ቀን 2016 ዓ.ም. ለፌዴራል መንግሥቱና ለዓለም አቀፍ ለጋሾች ባቀረበው የዕርዳታ ጥሪ፣ የ1977 ዓ.ም. ረሃብን የሚያስንቅ አደጋ በትግራይ ተከስቷል ብሏል፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ አደጋው በተወሰኑ አካባቢዎች የተወሰነ ብቻ ሳይሆን መላ ክልሉን ያዳረሰ መሆኑን ገልጿል፡፡

የትግራይ ክልል የጦርነት የዞረ ድምር ብቻ ሳይሆን ከባድ የረሃብ አደጋ አንጃቦበታል ያለው የጊዜያዊ አስተዳደሩ መግለጫ፣ ረሃቡ በምን መነሻነት እዚህ ደረጃ እንደደረሰ አትቷል፡፡

በትግራይ ክልል ጦርነቱ ይዞት ከመጣው ሰብዓዊ ቀውስ በተጨማሪ፣ ክልሉ ከባድ የሚባል የድርቅ አደጋ ገጥሞት እንደቆየ ገልጿል፡፡ በሦስት ዞኖች የዝናብ እጥረት ማጋጠሙን፣ በሁለት ዞኖች ደግሞ በሰብል ላይ ጉዳት ያስከተለ ጊዜውን ያልጠበቀ ዝናብና ውርጭ መከሰቱን፣ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የበረሃ አንበጣ አደጋ መከሰቱንም አብራርቷል፡፡

ይህ ሁሉ ሳያንስ ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶች በትግራይ ሲያደርጉት የቆዩት የዕርዳታ አቅርቦት በጊዜያዊነት አቋርጠው መቆየታቸውንም አስታውሷል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የዕርዳታ ድርጅቶች ድጋፋቸውን መልሰው ቢጀምሩም ዕርዳታው በከፊል መሆኑንና ካለው ቀውስ አንፃር በቂ አይደለም ብሏል፡፡

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ችግሩ አሳሳቢና አጣዳፊ ምላሽ የሚጠይቅ መሆኑን በመገንዘብ ካለው ውስን በጀት ላይ 50 ሚሊዮን ብር መድቦ የዕርዳታ አቅርቦት ለማከናወን ጥረት ማድረጉን በመግለጫው ጠቅሷል፡፡ ሆኖም ከፍተኛ የአቅም ውስንነት እንዳጋጠመው በመግለጽ መላው የትግራይ ክልል አካባቢም ገና በአስተዳደሩ ሥር እንዳልገባም አስረድተዋል፡፡ ያም ቢሆን ጊዜያዊ አስተዳደሩ ለረሃቡ ሥጋት ፈጥኖ ምላሽ ለመስጠት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣት የምላሽ ሰጪ ግብረ ኃይል አደራጅቶ በተናጠል ሲታገል መቆየቱን ጠቁሟል፡፡  

በጦርነቱ ሳቢያ ከፍተኛ የመሠረተ ልማት ውድመት በክልሉ መድረሱን፣ የጤና ተቋማት መፈራረሳቸውን፣ በግለሰቦችም ሆነ በመንግሥት እጅ የነበሩ ሀብትና ንብረቶች መውደማቸውን የሚዘረዝረው ይህ መግለጫ፣ የረሃቡ አደጋ ከክልሉ አቅም በላይ መሆኑንና የፌዴራል መንግሥትና ዓለም አቀፍ ለጋሾች እንዲደግፉት ጥሪ አቅርቧል፡፡ 

በትግራይ ክልል በፕሪቶሪያ ስምምነት መፈረም የጥይት ጩኸት ቆሞ ሰላም እንዲሰፍን የፌዴራል መንግሥቱና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የበኩላቸውን ሚና መጫወታቸውን መግለጫው ያወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ከፕሪቶሪያ ስምምነት መፈረም ማግሥት ጀምሮ ረሃብ የብዙዎችን ሕይወት እየቀማ ይገኛል ብሏል፡፡ ከ1977 ዓ.ም. የከፋ ያለውን ዜጎችን በመቅጠፍ ላይ ያለ የረሃብ አደጋ ለመቀልበስ፣ የፌዴራል መንግሥትና ዓለም አቀፍ ለጋሾች ፈጣን ምላሽ እንዲሰጡ ነው ጊዜያዊ አስተዳደሩ በይፋ ጥሪ ያቀረበው፡፡