

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮልከር ቱርክ
ዜና መንግሥት ለሽግግር ፍትሕ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር የፖለቲካ ቁርጠኝነቱን እንዲያሳይ ተመድና ኢሰመኮ አሳሰቡ
ቀን: December 31, 2023
- በኢትዮጵያ አጥፊዎችን ተጠያቂ ያለማድረግ ልማድ እንዲቆም ጠይቀዋል
- ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ወንጀሎች በምሕረት መታለፍ የለባቸውም ብለዋል
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት በጋራ ባወጡት ሪፖርት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሽግግር ፍትሕ ሥርዓት ቀረፃና ትግበራ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር የፖለቲካ ቁርጠኝነቱን በማያሻማ መንገድ እንዲያሳይ አሳሰቡ።
መንግሥት አካታች፣ ተጎጂዎችን ያማከለና ሰብዓዊ መብትን የሚያከብር የሽግግር ፍትሕ ሒደት ለመንደፍና ለመተግበር ምቹ ሁኔታን መፍጠር አለበት ያሉት ሁለቱ የሰብዓዊ መብት ተቋማት፣ ‹‹ለዚህም ሲባል በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የተከሰቱ ግጭቶችን በውይይትና በሰላማዊ መንገድ መፍታት፣ በመላ ኢትዮጵያ ሰላምና ፀጥታን ማስከበር፣ የሕግ የበላይነትን ማፅናትና የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና አፈጻጸሙ ዓለም አቀፍ መሥፈርቶችን ባከበረ መንገድ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት፤›› ብለዋል።
ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕግ ጥሰቶችን መከላከልና በኢትዮጵያ ተደጋግሞ የሚስተዋለውን አጥፊዎችን ተጠያቂ ያለማድረግ ልማድ (Culture of Impunity) እንዲያበቃ በማድረግ፣ መንግሥት ወሳኝ ዕርምጃዎችን እንዲወስድ ጠይቀዋል።
መንግሥት የሽግግር ፍትሕ ሒደትን የሚመሩና የሚተገብሩ አካላትን፣ በተለይም እንደ የወንጀል ተጠያቂነትና እውነት የማፈላለግ ያሉ ሒደቶች ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን የሚያሟሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባው አሳስበዋል። ለዚህም ሲባል የወንጀል ተጠያቂነት፣ እውነት የማፈላለግና መሰል ሒደቶችን የመምራትና የመተግበር ኃላፊነት የሚወስዱ አካላት ከፖለቲካ ጫና የፀዳ፣ ገለልተኛ፣ ተዓማኒ፣ ሕጋዊና ብቃት ያላቸው መሆኑ በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ሊኖረው ይገባል ብለዋል።
በተጨማሪም ከባድ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንና በደሎችን በፈጸሙት ላይ ምሕረት የመስጠት ምንም ዓይነት አማራጭ ሳይደረግ፣ የወንጀል ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ አሳስበዋል።
ሁለቱ ተቋማት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተጎጂዎችን በማነጋገር ባካሄዱት ጥናት ተጎጂዎች የገንዘብ ካሳ ማግኘትን፣ ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መነሻ የሆኑትን የሥር ምክንያቶች ለይቶ ማወቅን፣ ከፍርኃት/ከሥጋት ነፃ ሆኖ መኖርን፣ ነፃ የሆነ እውነትን የማፈላለግ (Truth Seeking) እና የማውጣት ሒደትን፣ መሠረታዊ የሆኑ አገልግሎቶችን ማግኘትን፣ መብቶችን መልሶ መጠቀም ማስቻልንና ለተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ መስጠትን እንደሚፈልጉ መረዳታቸውን በጥናት ግኝታቸው አስፍረዋል።
የሽግግር ፍትሕ ባለሙያዎች የሥራ ቡድን ያከናወናቸው ጠቃሚ ሕዝባዊ ምክክሮች እንደተጠበቁ ሆነው፣ የፖሊሲ አውጪዎች በብሔራዊ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ቀረፃ ሒደት ላይ የተጎጂዎች ድምፅ እንዲሰማ፣ መፍትሔ እንዲያገኙና የተጎዱ ማኅበረሰቦች ፍላጎት በበቂ ሁኔታ እንዲካተት በዚህ ሪፖርት የቀረቡትን ግኝቶች በጥብቅ እንዲያጤኗቸው አሳስበዋል።
በተጎጂዎች ፍላጎትና ቅድሚያ በሚሰጧቸው ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ትኩረት የሚያደርግና በሰብዓዊ መብቶች ደንቦች ላይ የተመሠረተ እውነተኛና ሁሉን አቀፍ የሽግግር ፍትሕ ሒደት መተግበር በአገር አቀፍ ደረጃ የደረሱ ጥፋቶችን የሚመጥን ምላሽ ለመስጠት፣ ፍትሐዊና ሰላማዊ ነገን ለመገንባትና ብሔራዊ አንድነትን ለማምጣት ከሁሉም በላይ ተገቢ መሆኑን አመልክተዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮልከር ቱርክ፣ ኢትዮጵያ ከፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ጋር የተጣጣመ አገራዊ የሽግግር የፍትሕ ፖሊሲን ለማዘጋጀት የወሰደቻቸውን ተጨባጭ ዕርምጃዎች በበጎ እንደሚቀበሉት አስታውቀዋል።
‹‹የሽግግር ፍትሕ ሥርዓትን ለመተግበር የተጀመረው ጥረት ሁሉን አቀፍና ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ደንቦችና ደረጃዎች ጋር የሚጣጣም እንዲሆን፣ የተጎዱ ሕዝቦችን በተለይም ሴቶችንና ልጃገረዶችን ማዕከል ያደረገ መሆኑን ማረጋገጥ ወሳኝ ነው፤›› ያሉት ከፍተኛ ኮሚሽነሩ ቮልከር ቱርክ፣ ‹‹መንግሥታት ግዙፍ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎችንና የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግ ጥሰቶችን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት የሚፈጸሙ ወንጀሎችን የመመርመርና ለፍርድ የማቅረብ ግዴታ አለባቸው። ጥሰት ወይም እንግልት የተፈጸመባቸው ሰዎች ፍትሕ የማግኘት መብት፣ እንዲሁም በቂ፣ ሁሉን አቀፍ፣ ፈጣንና ውጤታማ ካሳ የማግኘት መብት አላቸው፤›› ብለዋል።