EthiopianReporter.com 


የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፍሬው ተገኝ (ዶ/ር)

ማኅበራዊ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ሲጀመር ተማሪዎች ኃላፊነት ለመውሰድም ይዘጋጁ አለ

በጋዜጣዉ ሪፓርተር

ቀን: December 31, 2023

በናርዶስ ዮሴፍ

በአማራ ክልል የሚገኙ አሥር የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከጥር 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት ሁለት ሳምንታት መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራ እንደሚጀምሩ ትምህርት ሚኒስቴር ዓርብ ታኅሳስ 19 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። 

በአማራ ክልል የፀጥታ ችግሮች ምክንያት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ በዚህ የትምህርት ዓመት የመጀመሪያው ወሰነ ትምህርት ተማሪዎቻቸውን መጥራትና መደበኛ ትምህርት መስጠት አልቻሉም። 

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፍሬው ተገኝ (ዶ/ር) ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ ዩኒቨርሲቲው ከመስከረም 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ተማሪዎችን ለመቀበል ተዘጋጅቶ የነበረ ቢሆንም፣ በክልሉ የፀጥታ ሁኔታ ሳቢያ መሰናከሉን ተናግረዋል። 

‹‹በእኛ በኩል የዝግጅት ክፍተት የለብንም፤›› ያሉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት፣ ‹‹በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቁጥጥር ሥር የሆነ የፀጥታ ሁኔታ አለ። ከእኛ ቁጥጥር ውጪ የሆነም የፀጥታ ሁኔታ አለ። ከእኛ ውጪ በሆነው ጉዳይ ላይ ምንም ማድረግ አንችልም›› ብለዋል፡፡ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቱ አክለውም ‹‹ምንም ማድረግ ባልቻልንበት ሁኔታ የሰው ልጅ ጠርቼ አንድ መጥፎ ነገር ቢከሰት ምንድነው የምለው? የሚለውን ተማሪዎችም፣ ወላጅንም ታሳቢ አድርገን ተማምነን ይቆይ የሚል አቋም ስለነበረን በዚህ ምክንያት ነው እስካሁን ቀስ እያልን የመጣነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል። 

የትምህርት ሚኒስቴር ከክልሉ ኮማንድ ፖስት፣ የፀጥታ አደረጃጀቶች፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአሥሩ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የክልሉ ፀጥታ አካላት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ተከታታይ ውይይቶችን ሲያደርግ መቆየቱን የገለጸ ሲሆን፣ የውይይቶቹ የመጨረሻው ክፍል ሐሙስ ታኅሳሥ 18 ቀን 2016 ዓ.ም. እንደተደረገ ታውቋል። 

ፍሬው (ዶ/ር) በውይይት ሒደቱ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አቅዶ የነበረው ተመራቂ ተማሪዎችን ወደ የትምህርት ግቢያቸው ማስገባት እንደነበረ ገልጸዋል። 

በሐሙስ በተደረገው ውይይት በክልሉ ባለው አንፃራዊ ሰላም ዩኒቨርሲቲዎቹ ለመደበኛ ትምህርት ክፍት እንዲሆኑም ተወስኗል። 

‹‹እስካሁን ባለን ልምድ ግጭቶች እዚህም እዚያም ሊቀሰቀሱ ይችላሉ። ቀጣይነታቸው ግን ብዙም አይደለም። አንድ ቀን ወይ ሁለት ቀን መስተጓጎል ሊፈጠር ይችላል ከዚያ ግን ያበቃል፤›› ያሉት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳት ፍሬው (ዶ/ር)፣ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው ተጠርተው ሲመጡ ታሳቢ ማድረግ ያለባቸውን ጉዳዮች ለሪፖርተር ገልጸዋል። 

በማብራሪያቸውም ሁሉም የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ሊያጋጥሙ የሚችሉ ዕክሎችን ከግምት በማስገባት ኃላፊነት መውሰድ አለባቸው ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ተማሪውም፣ ወላጅም፣ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብም እንደ አገር የሚመለከታቸውም አንድ ላይ ሆነን መደበኛ ትምህርት መጀመር አለብን ብለን ወስነናል፤›› ሲሉ አስታውቀዋል። 

በትምህርት ሚኒስቴር የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ አሥሩ የአማራ ክልል ከፍተኛ የመንግሥት የትምህርት ተቋማት ከጥር 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉ ሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ተማሪዎቻቸውን ጠርተው የመማር ማስተማር ሥራቸውን ይጀምራሉ ተብሏል።

በዩኒቨርሲቲዎቹ የተመደቡ ተማሪዎችም የዩኒቨርሲቲዎቹ የሚያደርጉትን ጥሪ እንዲከታተሉ ሚኒስቴሩ በመግለጫው  ጠቁሟል። 

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ተቋማቸው ከልደት (ገና) በዓል በኋላ ባሉት ቀናት ለተማሪዎቹ ጥሪ እንደሚያደርግ አሳውቀዋል።