
December 31, 2023

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ያቀረበው ጥናት ላይ ውይይት ሲደረግ
በናርዶስ ዮሴፍ
ኢትዮጵያ ውስጥ ከተሰራጨው ጨርቃ ጨርቅ 53 በመቶ የሚሆነው በሕገወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ እንደሚገባ፣ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጥናት አስታወቀ።
በምክር ቤቱ አዘጋጅነት ሐሙስ ታኅሳስ 18 ቀን 2016 ዓ.ም. በስካይላይት ሆቴል በተካሄደው ሁለተኛ አገር አቀፍ ሕገወጥ ንግድን በተመለከተ በተዘጋጀ ኮንፈረንስ የቀረበው ጥናት፣ የኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ በኮንትሮባንድ ንግድ ከፍተኛ ጫና ውስጥ መግባቱን ያሳያል።
የጥናቱ አቅራቢ አቶ አግአዚ ገብረ ኢየሱስ እንደገለጹት፣ በዓመት 54 ሚሊዮን ዶላር ግምት ያለው ጨርቃ ጨርቅ ወደ አገሪቱ በኮንትሮባንድ እየገባ ነው። መንግሥት ከግብርና ከሌሎች የአገልግሎት ክፍያዎች ሊያገኝ ይችለው የነበረን 45 ሚሊዮን ዶላር በየዓመቱ እያጣ ነው ብለዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታት 1.5 ቢሊዮን ብር እንደሚያወጣ የሚገመት የጨርቃ ጨርቅ ምርት በጉምሩክ ኮሚሽን ሲወረሱ ቢገለጽም፣ በጥናቱ መሠረት በየዓመቱ በኮሚሽኑ ቁጥጥር የሚያዘው መጠን በሕገወጥ መንገድ እየተሠራጨ ካለው አሥር በመቶ ብቻ የሚሸፍን ነው ተብሏል።
በጉምሩክ ኮሚሽን የኢንተለጀንስ ዳይሬክተር አቶ ሰኚ ሰፋ በበኩላቸው፣ ‹‹ጥናቱ ሁሉን አቀፍ ነው ወይ የሚለው ትንሽ አጠያያቂ ነው። አንድ ጥናት ሲሠራ የሚያስፈልጉ መሟላት ያለባቸው መሥፈርቶች አሉ። በዚያ መሥፈርት ነው ወይ የተሠራው የሚለው ጥያቄ ውስጥ ይገባል፤›› ብለው ከአገሪቱ ፀጥታና ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ታሳቢ በማድረግ በሁሉም ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች የሚገኙ ተቆጣጣሪዎች እየሠሩ አይደለም ብለዋል። በተለይ በሰሜን ያለው ሁኔታና በሞያሌ በኩል ባለው መስመር ያሉ የፀጥታ ሁኔታዎች በቁጥጥር ሒደቱ ላይ ጫና አሳድረዋል ሲሉ አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት ገበያውን በስፋት የተቆጣጠሩት ልባሽ ጨርቆች (ቦንዳ) በዋናነት ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ፣ ከታይዋንና ከታይላንድ እንደሚገቡ ተገልጿል፡፡ የኮንትሮባንድ ልባሽ ጨርቆቹ መነሻ አገሮች ዋነኛ ተብለው ከተጠቀሱት አገሮች በቀን ከአሥር ሺሕ በላይ ቦንዳ እንደሚገባም ተጠቁሟል።
ገብያ ውስጥ ተሠራጭተው ያሉት ልባሽ ጨርቆች በጥራት ደረጃ፣ ተሳታፊ በሆኑበት የሕገወጥ ንግድ ዓይነትና ተቀባዮቻቸው እነማን ናቸው በሚሉ መሥፈርቶች ተገምግመው በሦስት ደረጃዎች ተመድበዋል።
በመጀመሪያ ደረጃ ላይ ያሉት “ታይዋን” በሚል ስም የሚታወቁ ሲሆን፣ የጥራት ደረጃቸው ከፍተኛ የሆኑ ከታይዋን አገር በኮንትሮባንድ የሚገቡ ናቸው፡፡ ታጥበውና አዲስ እንደሆኑ የሚያስመስል የመለያ ምልክት (Tag) ተለጥፎላቸው፣ ለእነዚህ አገልግሎቶችም በአንድ ልብስ ከ200 እስከ 400 ብር የሚከፈልባቸው ሲሆኑ፣ በአዲስ አበባ በተለይም በቦሌና ሃያ ሁለት አካባቢዎች ባሉ ቡቲኮች አዲስ ናቸው ተብለው ቀርበው ከሁለት ሺሕ እስከ ስድስት ሺሕ ብር የሚሸጡ ናቸው ተብሏል። ተቀባይና አሠራጭ ቡቲኮች በሳምንት ከ15 እሽከ 20 የሚደርሱ እንዲህ ዓይነቶቹን ልብሶች ከአከፋፋዮች ይቀበላሉ ተብሏል።
ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው “ዕፎይታ” የሚል ስያሜ የተሰጠው የልባሽ ጨርቅ ዓይነት ነው። በዚህ ሥር የተካቱት አብዛኞቹ ከታይላንድ በኮንትሮባንድ የሚገቡ ሲሆኑ፣ መካከለኛ የጥራት ደረጃ ያላቸውና በጅምላ እንደታሰሩ (በቦንዳ) ለአከፋፋዮች የሚሸጡና በብዛትም መርካቶ የሚቸበቸቡ እንደሆኑ ተገልጿል።
በሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው “እንከን” የሚል ስያሜ የተሰጠው የሕገወጥ ልባሽ ጨርቆች ንግድ መቀደድን ጨምሮ የተለያዩ እንከኖች ያሉባቸው የጥራት ደረጃቸው ዝቅተኛ የሆኑ ልብሶች ሲሆኑ፣ በስፋት በአየር ጤና አካባቢ ለመንገድ ዳር ሻጮች የሚከፋፈሉ እንደሆኑ ጥናቱ አብራርቷል።
ከእነዚህ በተጨማሪም ለአውሮፓ ገበያ ቻይና ውስጥ ተመርተው፣ አንድም ልብሶቹን ከአውሮፓ ያዘዙት ሰዎች ገንዘብ ሳይከፍሉ ሲቀሩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ያዘዙት ልብስ በተፈለገበት የአየር ሁኔታ ወቅት ሳይደርስ ሲቀር በቻይና አምራቾች በኩል እንዲወገዱ ሲወሰን ኢትዮጵያን ለመሳሰሉ ታዳጊ አገሮች እንደሚላኩ ጥናቱ ጠቅሷል።
በሌላ በኩል በጉምሩክ ኮሚሽን ቁጥጥር የሚያዙ የኮንትሮባንድ ልብሶች ከዚህ ቀደም የተለመደው ማቃጠል ቀርቶ ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች ስለሚከፋፈሉ፣ ለሕገወጥ አካላት መግቢያ በር ሆኖ ተገኝቷል ሲሉ የጥናቱ አቅራቢ አቶ አግአዚ ገልጸዋል።
‹‹ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ባለው አሠራር የተጀመረው የተያዙ የኮንትሮባንድ ልብሶችን ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች የመስጠትን የመልካምነት ሐሳብ ብንረዳም፣ አሠራሩ ግን በሕገወጦች ተጠልፎ ልብሶቹ ከታለመላቸው ዓላማ ውጪ ተመልሰው ወደ ገበያው ለሽያጭ መቅረባቸው በጥናቱ አጋጥሞናል፤›› ብለዋል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን ኢንተለጀንስ ዳይሬክተር አቶ ሰኚ በበኩላቸው፣ ‹‹ይህ በአንድ ተቋም ወይም በኮሚሽኑ ብቻ የሚፈታ አይደለም። አጥፊዎችን ስናገኝ በሕግ ቁጥጥር ሥር እያዋልን ነው። ለሚመለከተው አካል እያስተላለፍን ተገቢውን የሕግ ሒደት እየተከተልን ነው። ነገር ግን ከፍተኛ የሆነ የተቋማት ቅንጅት የሚጠይቅና የእኔነትን ስሜት ሁሉም ወስዶ መሥራት ያለበት ጉዳይ ነው፤›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
የጉምሩክ ኮሚሽን በ2016 በጀት ዓመት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 3.6 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ኮንትሮባንድ መያዙን ሪፖርት ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን፣ ከዚህም ጋር ተያይዞ 258 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው መገለጹ አይዘነጋም።