EthiopianReporter.com 


በአዲስ አበባ ሕጋዊ ፈቃድ ያላቸው የስፖርት ውርርድ አጫዋቾች ብዛታቸው 120 ነው ተብሏል

ማኅበራዊ የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ከስፖርት ውርርድ አጫዋቾች ጋር መግባባት ላይ መድረሱ ተሰማ

ተመስገን ተጋፋው

ቀን: December 31, 2023

የስፖርት ውርርድ (ቤቲንግ) አጫዋቾች ሕጉን ተከትለው እንዲያጫውቱ፣ ቅርንጫፋቸውን ሲያስፋፉም የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ባስቀመጠው መመርያ መሠረት እንዲያከናውኑ መግባባት ላይ መድረሱ ታወቀ፡፡

የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላምና የፀጥታ ቢሮ ጋር በመተባበር ሐሙስ ታኅሳስ 18 ቀን 2016 ዓ.ም. ባዘጋጀው የውይይት መድረክ የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበርና ከስፖርት ውርርድ አጫዋቾች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

ከሰሞኑ የስፖርት ውርርድ አጫዋቾችን (ቤቲንግ) በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፀጥታ ቢሮ ባወጣው መግለጫ፣ በ3,241 የቤቲንግ ቤቶች ላይ የማሸግ ዕርምጃ መውሰዱ ይታወሳል፡፡

የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ንዋይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የስፖርት ውርርድ የሚያጫውቱ ሕጋዊ በሆነ መንገድ እንዲሠሩ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ ሕጋዊ ፈቃድ ያላቸው 120 የስፖርት ውርርድ (ቤቲንግ) አጫዋቾች እንዳሉ የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ቤቲንግ ቤቶች ቅርንጫፋቸውን ሲያስፋፉ ከብሔራዊ ሎተሪ ፈቃድ መጠየቅ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

በተለይ በከተማዋ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኬኖ በመባል የሚታወቅ ውርርድ በሕገወጥ መንገድ እያጫወቱ መሆኑን የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ፣ በቅርቡ የታሸጉት የስፖርት ውርርድ ቤቶች ሕጉን ተላልፈው ኬኖ ሲያጫውቱ በመገኘታቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በወቅቱም ሕጉን ያከበሩ ቤቲንግ ቤቶች እንዳልተዘጉና እስካሁንም እየሠሩ እንደሆነና ቤቲንግ ቤቶች ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ያከናውናሉ የሚል መረጃ ቢናፈስም፣ ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር በዚህ ጉዳይ ላይ ያገኘው መረጃ እንደሌለ አስረድተዋል፡፡

በሕገወጥ መንገድ የተሰማሩ ኬኖ ቤቶችም ሆኑ የስፖርት ወርርድ ቤቶችን በጋራ ለመቆጣጠር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት በውይይቱ ላይ መነሳቱን ገልጸዋል፡፡

ኬኖ የሚያጫውቱ ቤቶች ፈቃድ የሌላቸውና በብሔራዊ ሎተሪ ሥር ያልሆኑ መሆናቸውን፣ አንድ ግለሰብ የስፖርት ውርርድ ወይም ቤቲንግ ቤት ለመክፈት 1.5 ሚሊዮን ብር ዋስትና ማስያዣ እንደሚኖርበት አብራርተዋል፡፡

የከተማው የሰላምና የፀጥታ ቢሮ ወደ ዕርምጃ የገባው የቤቲንግ ጨዋታ በከተማዋ አስተዳደር፣ እንዲሁም በየዕለቱ በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ ሕይወት ላይ እየፈጠረ ያለውን አሳሳቢ ችግር በመረዳት መሆኑን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡