
December 31, 2023

የዳሸን ባንክና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቲኬት ክፍያ ብድር አሠራር ይፋ ያደረጉበት ሥነ ሥርዓት
ባንኩ የሚፈቅደው የብድር መጠን 600 ሺሕ ብር መሆኑ ታውቋል
ዳሸን ባንክና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኞች የአገር ውስጥና የውጭ አገር በረራ የቲኬት ክፍያ ብድር የሚያገኙበት አሠራር ይፋ አደረጉ፡፡
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ የሚሆነው ‹‹ጉዞዎ ይቀድማል ክፍያው ይደርሳል›› በሚል የተሰየመው ይህ አሠራር፣ በተለይ በንግድ ሥራ ላይ ለተሰማሩ አስመጪዎችና ለዕረፍት ከቤተሰቦቻች ጋር ወደ ውጭ ለሚሄዱ ደንበኞች አመቺ መሆኑን ሐሙስ ታኅሳስ 18 ቀን 2016 ዓ.ም. በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
የዳሸን ባንክ ዲጂታል ባንኪንግ ዋና መኮንን አቶ ዮሐንስ ሚሊዮን፣ ‹‹ሁለቱ ተቋማት ስምምነት ያደረጉበትን አሠራር ተጠቃሚ ለመሆን የሚፈቀደው የብድር መጠን 600,000 ብር ነው፤›› ብለዋል፡፡ የብድር ተጠቃሚዎች ክፍያውን በስድስት ወይም በአሥራ ሁለት ወራት መፈጸም እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡
ደንበኞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን በዳሸን ባንክ የሒሳብ ቁጥር መክፈት እንደሚጠበቅባቸው፣ በተጨማሪም በባንኩ ቢያንስ ለሦስት ወራት አገልግሎት ያገኙ መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
አቶ ዮሐንስ አክለውም፣ አገልግሎቱን ለማግኘት ደንበኞች በአቅራቢያቸው የሚገኝ የዳሸን ባንክ ቅርንጫፍ በሚያመሩበት ወቅት አስፈላጊ ሰነዶችን ማሟላትና ማስያዣ ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡
ደንበኞች የተፈቀደላቸው የብድር መጠን ሲያልቅ ማደስ የሚችሉበት አሠራር እንደሚኖር፣ በአንዴ የወሰዱትን ብድር ለተለያዩ በረራዎች ከፍለው መጠቀም እንደሚችሉ ዋና መኮንኑ አብራርተዋል፡፡
የአየር ትራንስፖርት ክፍያ አገልግሎቱን የሚጠቀሙ ደንበኞች በመረጡትና ብድሩን በወሰዱበት የጊዜ ገደብ፣ ከብድሩ ጋር የሚፈለግባቸውን ወለድ እንዲከፍሉ ጠቁመዋል፡፡
አንድ ደንበኛ አዲሱን አገልግሎት ለመጠቀም ቅድመ ሁኔታዎችን ካሟላ በኋላ በቅርንጫፍ የተፈቀደለትን የብድር መጠን የሚወስድ መሆኑን፣ የተፈቀደለትን ገንዘብ መጠቀም የሚያስችል የአንድ ጊዜ መለያ ቁጥር መልዕክት በተንቀሳቃሽ ስልኩ የሚደርሰው መሆኑን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና የንግድ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ለማ ያዴቻ ገልጸዋል፡፡
በዚህ መሠረት ደንበኛው የተሰጠውን መለያ ቁጥር በአየር መንገዱ የሞባይል መተግበሪያ ላይ በማስገባት፣ ትኬት መቁረጥና የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችል አስረድተዋል፡፡
ዳሸን ባንክና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዘረጉት ይህ አዲስ አሠራር በገንዘብ እጥረት ምክንያት ወደ ተለያዩ አገሮች በረራ ማድረግ ለሚፈልጉ ደንበኞች ትልቅ አማራጭ መሆኑን፣ የዳሸን ባንክ የኤጀንሲ ባንኪንግ ቢዝነስ ዲፓርትመንት ዳይሬክተር አቶ ብሩክ ኃይለ መስቀል ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
‹‹በአሁኑ ወቅት ለደንበኞች የቀረበው ይህ አሠራር የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ በማምጣት ነው፤›› ያሉት ዳይሬክተሩ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመጠቀም ያሰቡ ሰዎች ተቀጣሪ ወይም በግል ሥራ የተሰማሩ ከሆኑ የንግድ ፈቃዳቸው፣ እንዲሁም ሌሎች ነገሮችን እንደ ማስያዣ ማቅረብ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡