
December 31, 2023

ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በሪሶርስ ኢኮኖሚክስ ተመርቀዋል፡፡ በዚያው በተመረቁበት ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት አገልግለዋል፡፡ በዴቨሎፕመንታል ስተዲስ ሌላ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ በሊደርሺፕ ደግሞ ሁለተኛ ዲግሪ ሠርተዋል፡፡ ከዩኒቨርሲቲ መምህርነት ወጥተው የላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪ ኢንተርፕራይዝ ውስጥ ሠርተዋል፡፡ አሁን ደግሞ የራሳቸውን ሥራ በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በግል የገነቧቸው የሱፐር ማርኬትና የሬስቶራንት ቢዝነሶች ጥሩ እየሠሩ እንደሆነ ቢገልጹም፣ በአገሪቱ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት የጀመሩትን የእርሻ ሥራ ማቋረጣቸውንም ይናገራሉ፡፡ ሥራ ፈጠራ ላይ ያተኮሩ ‹‹መነገጃ››፣ ‹‹የሀብት ቀመር›› እና ‹‹ተገለጥ›› የተባሉ ሦስት መጻሕፍት ማሳተማቸውንም ያስረዳሉ፡፡ የቢዝነስና ሥራ ፈጠራ ሥልጠናዎችን በመላ አገሪቱ እየዞሩ እንደሚሰጡና የኢኮኖሚ ነክ ጥናቶችን እንደሚሠሩ ከሚናገሩት ወጣቱ የምጣኔ ሀብትና የሥራ ፈጠራ ባለሙያ አቶ ጌታቸው ጳውሎስ ጋር ዮናስ አማረ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ላይ ያደረገው ሰፊ ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ሪፖርተር፡- በብዙ የትምህርት ተቋማት የኢኮኖሚና የሥራ ፈጠራ ትምህርቶች ይሰጣሉ፡፡ በተጨባጭ እነዚህ ትምህርቶች በተግባር መተርጎም በሚቻል መንገድ ነው ወይ የሚሰጡት? ችግር ፈቺና አገር ለመለወጥ የሚያስችሉ ሳይሆኑ ከውጭ ተቀድተው የመጡ የኢኮኖሚ ነክ የቀለም ትምህርቶች ናቸው የሚሰጡት ለሚባለው ትችት ምን ይላሉ?
አቶ ጌታቸው፡- ምዕራባዊያኑ በተለይ እንደ እንግሊዝና አሜሪካ ያሉ አገሮች በአፍሪካ አገሮች የትምህርት ፖሊሲ ሲቀረፅ ጀምሮ በተለያዩ መንገዶች ጣልቃ እንደሚገቡ ይታወቃል፡፡ እኛም ዘንድ የትምህርት ሚኒስቴር አካባቢ አይጠፉም፡፡ የመጽሐፍ ኅትመቶችንና ሌሎችን ስፖንሰር እናደርጋለን፣ ዘርፉን እንደግፋለን እያሉ የትምህርት ፖሊሲው ሲቀረፅ ጀምሮ የእነሱን ፍላጎት ለማስገባት እንደሚጥሩ ይታወቃል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የትምህርት ይዘቱ በውስጡ የያዛቸው የትምህርት ዓይነቶች አንድን ሰው ብቁ አድርጎ ለመቅረፅ አያስችሉም፡፡ አንድ ሰው ዘርፍ በቂ ዕውቀትና ክህሎት ሳያዳብር የሚመረቅበት ሁኔታ ይታያል፡፡ ይህ ከአስተማሪዎች ብቃት ማነስ ጋር የተያያዘም ሊሆን ይችላል፡፡ ሁለተኛም የሚሰጡ ትምህርቶች ከንድፈ ሐሳባዊ (ከቀለም ዕውቀትነት) በዘለለ በተጨባጭ በተግባር የማይተረጎሙ ሊሆኑም ይችላሉ፡፡
ለምሳሌ እኔ በግሌ ‹‹ፐርቼዚንግ ፓወር ፓሪቲ›› እየተባለ የሚሰጠውን የኢኮኖሚ ጽንሰ ሐሳብ አላምንበትም፡፡ አሜሪካኖቹ ያመጡት የውሸት ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ እነሱ በዓለም ላይ ባላቸው የዶላር ግብይት ተፅዕኗቸውን ይዘው ለመቀጠል በማሰብ ነው ያመጡት፡፡ የዶላር ምንዛሪ የሚሠሩ ሰዎች እኮ ምንም ነገር ሳይሸጡ ሀብታሞች ናቸው፡፡ ሌላ ምርትም ሆነ አገልግሎት ሳያቀርቡ እነሱ ግን ብዙ ገንዘብ ያገኛሉ፣ አሜሪካኖቹም ይህን ይጠቀማሉ፡፡ የዓለምን ኢኮኖሚ የሚቆጣጠሩበት አንዱ መንገድ ይኼው ‹‹ፐርቼዚንግ ፓወር ፓሪቲ›› የሚባለው ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ የወጪ ንግድን (ኤክስፖርትን) ለማበረታታት፣ እንዲሁም የገቢ ንግድን (ኢምፖርትን) ለመቀነስ እየተባለ እያንዳንዱ የቢዝነስና የኢኮኖሚ ተማሪ እንዲማረው ይደረጋል፡፡ ስለምንዛሪ ግብይትና ስለ ‹‹ፐርቼዚንግ ፓወር ፓሪቲ›› ይህ ሁሉ እየተነገረህ ነው የምትማረው፡፡ ይሁን እንጂ እነሱ እንደ ኢትዮጵያ ካሉ ደሃ የአፍሪካ አገሮች አንድ ምርት ለማስገባት የሚጥሉት ቀረጥና የጥራት ቁጥጥር ብለው የሚያስቀምጧቸው መሥፈርቶች ብዙ ናቸው፡፡ ከሰብዓዊ መብት ጋር አያይዘው የሚያስቀምጡት የፖለቲካ ቅድመ ግዴታም በዚያው ልክ የበዛ ነው፡፡ ስለዚህ ከአፍሪካ አገሮች ሚፈልጉትን ዓይነት ጥሬ ዕቃና የጥራት ደረጃ ካልሆነ በቀላሉ ወደ ገበያቸው እንዲገባ አያደርጉም፡፡
ትምህርቱ በዚህ የተነሳ ብዙ ህፀፅና ስህተት ያለው ሆኖ ይታየኛል፡፡ ትምህርቱ ከአገራችን ሁኔታ አንፃር በተግባር መተርጎም የሚቻል ብዙ ተጨባጭ ዕውቀቶች ያሉት ቢሆንም፣ ነገር ግን አብሮ የውሸት ንድፈ ሐሳቦችንም ያስተምራል፡፡ አብዛኞቹ የምንማራቸው ትምህርቶች የግሪክ ፈላስፎች የጻፏቸው በተለይ ደግሞ በኢኮኖሚክሱ የአሜሪካና የእንግሊዝ ምሁራን ያፈለቋቸውን ሐሳቦች ነው፡፡ እነሱ ለራሳቸው አገር ሁኔታ የፈጠሩትን ንድፈ ሐሳብ እየተማሩ በእኛ አገር ሁኔታ በተግባር ለመተርጎም ከባድ ነው፡፡ የእኛን ተጨባጭ ችግርም ሊፈታ አይችልም፡፡ ቻይኖችና ሌሎች እያደጉ ያሉ የእስያ አገሮች የምዕራባዊያኑን የኢኮኖሚ ንድፈ ሐሳብና ትምህርት በጥንቃቄ ነው የሚያዩት፡፡ የሚቀርፁት የትምህርት ፖሊሲም ከምዕራባዊያኑ ጋር የተራራቀ ነው፡፡ እኛ ነን ዝም ብለን የምዕራባውያኑን ሐሳብ እየቀዳን የምንወስደው፡፡ በተለይ ከእንግሊዞቹ ብዙ ነገሮች እንወስዳለን፡፡ ይህ ደግሞ ከእኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አብሮ አይሄድም፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ታሟል ይባላል፡፡ ይህ ከምን የመጣ ነው ለሚለው ማሳያዎችን ቢጠቅሱልን?
አቶ ጌታቸው፡- አንድ ኢኮኖሚ ታሟል ወይም ችግር አለበት ሲባል በማክሮ ኢኮኖሚ መለኪያዎች ጎልተው የሚነሱ የተወሰኑ ነጥቦች ይኖራሉ፡፡ አንደኛው የዋጋ ግሽበት ነው፡፡ በአንድ አገር ውስጥ የዋጋ ግሽበት አኃዝ ባለነጠላ ዲጂቶችን አልፎ ከአሥር በላይ አሻቅቦ ባለሁለት አኃዝ ሲሆን፣ በአብዛኛው ጤናማ አይደለም ነው የሚባለው፡፡ እኛ አገር ግን የዋጋ ግሽበት ከመቶ በመቶ በላይ ነው ያደገው፡፡ ዓብይ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ሲመጡ አንደኛ ደረጃ ጤፍ 2,800 ብር ነበር በኩንታል የሚሸጠው፣ አሁን ግን 13 ሺሕ ብር ደርሷል፡፡ ይህን መሰሉን የዋጋ ግሽበት ታዲያ በምን መንገድ ነው ማስላት የሚቻለው? በዚህች አምስት ዓመት ውስጥ የጤፍ ዋጋ ብቻ ወደ 500 በመቶ ነው ያሻቀበው፡፡ የኢኮኖሚ ጤናማነት መታወክ አንዱ ማሳያ ይህን ዓይነት የተጋነነ የዋጋ ግሽበት ነው፡፡ ሌላው የኢኮኖሚ ጤና መቃወስ ማሳያ ሥራ አጥነት ነው፡፡ በአገራችን ብዙ ወጣት ነው ያለው፡፡ ነገር ግን ብዙኃኑ የሚሠራው ነገር የለውም፡፡ አንድ ሰው ከዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ ዲግሪ ለመመረቅ ወደ 15/16 ዓመታት በትምህርት ያሳልፋል፡፡ ይህ ሁሉ እንዲሆን ደግሞ ቤተሰብና ዘመድ ወዳጅ ብዙ መስዋዕትነት ይከፍላል፡፡ መንግሥትም፣ አገርም፣ አካባቢውም ብዙ ኢንቨስት ያደርጋል፡፡ አንድ ሰው ተመርቆ ሥራ አልያዘም ማለት ይህ ሁሉ ኢንቨስትመንት ወደ ሥራ ሳይለወጥ ተቀምጧል፣ ወይም ባክኗል ማለት ነው፡፡ በአንድ ሰው የ16 ዓመታት የትምህርት ቆይታ ውስጥ የሚባክነው የአገር ሀብት ብዙ ነው፡፡ ሌላኛው የኢኮኖሚ መታመም ምልክት የመንግሥት በጀት ጉድለት ነው፡፡ መንግሥት በየዓመቱ በምን መንገድ ነው በጀቱን የሚሞላው? በግብር፣ በብድር፣ በዕርዳታ ወይስ ገንዘብ በማተም የሚለው ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ አንድ ኢኮኖሚ ጤናማ ነው የሚባለው በራሱ ገቢ ወጪውን ሲሸፍን መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንፃር የእኛ አገር በጀት ወደ 60 በመቶ በራሱ ገቢ እንደሚሸፈንና ቀሪው 40 በመቶ በዕርዳታና ብድር እንደሚሸፈን ይነገራል፡፡ ይህን በተመለከተ ትክክለኛ አኃዝ ይነገራል ብዬ አላስብም፡፡ ምክንያቱም በጥልቀት ቢፈተሽ በዕርዳታና ብድር የሚሸፈነው ከ40 በመቶ በላይ እንደሚሆን እገምታለሁ፡፡ ቦንድ በመሸጥ፣ ከብሔራዊ ባንክና ከባንኮች በሚገኝ ብድር፣ እንዲሁም በውጭ ዕርዳታና ብድር የሚሸፈነው በጀት ብዙ መሆኑ ይገመታል፡፡ ሌላኛው የኢኮኖሚ ጤና መታወክ ማሳያ ደግሞ ብድር የመክፈል አቅም መዳከም ነው፡፡ አገሮች የወሰዷቸው የተጠራቀሙ ብድሮች ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ከሚሊኒየሙ በኋላ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ከቻይና፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክ፣ ከአይኤምኤፍ፣ ከዓለም ባንክ፣ ከአገሮችና ከሌሎችም የብድር ምንጮች ብዙ ገንዘብ ተበድራለች፡፡ ማንም አበዳሪ ገንዘብ ሲያበድር ደግሞ ወለዱንም አስቦ ነውና የሚያበድረው እነዚህ ብድሮችም ከእነ ወለዳቸው ነው የሚከፈሉት፡፡ በቅርቡ ኢትዮጵያ መክፈል የነበረባትን የዩሮ ቦንድ ብድር ወለድ አለመክፈሏ ሲነገር ሰምቻለሁ፡፡ ይህ የኢኮኖሚ ጤናማ አለመሆን ራሱን የቻለ ማሳያ ነው፡፡ ብድር መክፈል አለመቻል እዳህ እየተከማቸ እንዲሄድ ከማድረጉ በዘለለ ተጨማሪ ብድር እንዳታገኝም እንቅፋት ይሆናል፡፡
በኢኮኖሚው ውስጥ ተመጣጣኝ ያልሆነ የገንዘብ ኅትመት አለ፡፡ በግልም በመንግሥትም ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ኅትመት አለ፡፡ በግል ያልኩት የሚያትሙ ስላሉ ነው፡፡ መንግሥትም ዜና እያወጣ ነው፡፡ በአገሪቱ ያለው የገንዘብ ኖት ኅትመት አገሪቱ ካላት ጥቅል የኢኮኖሚ ምርት ጋር ተጣጥሞ ካልሄደ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ይዞ ነው የሚመጣው፡፡ ሌላኛው የኢኮኖሚ ሕመም የድህነት መጠን መጨመር ነው፡፡ የዋጋ ግሽበት ሲኖር የሰዎች የመግዛት አቅም ይዳከማል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ቁጠባ አይኖርም ማለት ነው፡፡ ቁጠባ ከሌለ ደግሞ ኢንቨስትመንት ይዳከማል፡፡ ኢንቨስትመንት ከሌለ ደግሞ የሥራ ዕድል አይኖርም፡፡ ሰዎች ተጨማሪ ገቢ ሊያገኙ የሚችሉበት ዕድል ይጠፋል፡፡ በእንዲህ ዓይነት የድኅነት አዙሪት ውስጥ አንድ ደመወዝተኛ የሆነ ሰው የወር ደመወዙን እንደምንም አብቃቅቶ ወሩን ለማለፍ ይሞክራል እንጂ የተለየ ነገር አያስብም፡፡ ስለዚህ ከአመጋገብ፣ ከአለባበስና፣ ከመኖሪያ አቅርቦት ጀምሮ ወደ ባሰ የድህነት ሕይወት ውስጥ እየገባ ይሄዳል ማለት ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ መንግሥትም ባመነው መሠረት በሁለት ዓመታት ውስጥ ወደ 15 ሚሊዮን ተጨማሪ ደሃ መፈጠሩን ሲዘገብ ሰምቻለሁ፡፡ በግለሰብ ደረጃ የድህነት አኗኗር መባባስ የአገርን ኢኮኖሚ ጤናማ አለመሆን አመላካች ነው፡፡ ወደ አሥር ሚሊዮን ደሃ ተፈጠረ ሲባል ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ላላት ኢትዮጵያ ትንሽ ነው ሊባል ቢችልም፣ ይህ አኃዝ ግን ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር እንኳ ቢነፃፀር የብዙ አገሮች ሕዝብ ሊወጣው ይችላል፡፡
የፋይናንስ ተቋማት ያለባቸው የገንዘብ እጥረትም አንዱ የኢኮኖሚ ችግር ምልክት ነው፡፡ ግሽበት ከፍተኛ ሲሆን ሰዎች ያላቸውን ገቢ ለማብቃቃት ስለሚቸገሩ ቁጠባ ይቀንሳል፡፡ ቁጠባ ሲቀንስ ደግሞ የፋይናንስ ተቋማት የገንዘብ እጥረት ይገጥማቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ይህን መሰሉ የኢኮኖሚ ድባቴ ከቀጠለ በጥቂት ጊዜ ውስጥ አዳዲስ የፋይናንስ ተቋማትና የሪል ስቴት ዘርፉ ይቃወሳሉ የሚል ሥጋት አለኝ፡፡ የፋይናንስ ተቋማት ዋና ገቢ ብድር በመስጠት የሚገኝ ወለድ ነው፡፡ መንግሥት ደግሞ ብድር በመገደቡ ብዙ ነባር ባንኮች ጭምር አጣብቂኝ ውስጥ የገቡበት ሁኔታ አለ፡፡ የፋይናንስ (የሊኩዲቲ) ችግር በፋይናንስ ተቋማት ላይ ከባድ ቀውስ ነው የሚፈጥረው፡፡
እኛ አገር ሁሉም ነገር በፖለቲካ መነጽር ስለሚታይ ደፍሮ የሚወጣና የሚናገር የለም እንጂ፣ የፋይናንስ ተቋማት የገጠማቸው ችግር ሥር የሰደደ ነው፡፡ የባንክ ኃላፊ የሆኑ ሰዎችን አውቃለሁ፡፡ ብዙዎቹ ለደንበኞቻቸው የቆጠቡትን አውጥተው ለመስጠት ገንዘብ እንደሚቸግራቸው ይናገራሉ፡፡ ሌላ ቅርንጫፍ ሄዳችሁ ሞክሩ የሚባልበት ጊዜ ላይ ተደርሷል፡፡ በግብርናም በኢንዱስትሪም የአዳዲስ ኢንቨስትመንቶች መቀነስ መታየቱ ሌላው የኢኮኖሚ ችግር ማሳያ ነው፡፡ ከእነዚህ ሁኔታዎች አንፃር ካየነው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ታሟል፡፡ ኢኮኖሚው መታመም ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ችግር ውስጥ ነው ያለው፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖዎች እንደገጠሙት መንግሥት ያወሳል፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ ተፅዕኖ እንዳሳረፈበት፣ በሌላም በኩል የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በመካከለኛው ምሥራቅ የእስራኤልና የሐማስ ግጭት በኢኮኖሚው ላይ ጫና እንደሚኖራቸው ይገልጻል፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ ደግሞ በአገር ውስጥ የተከሰተው ጦርነትና ግጭቶችም ተፅዕኖ አሳዳሪ መሆናቸው ይነገራል፡፡ ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ምን ዓይነት ችግር ውስጥ ነው የሚገኘው ማለት ይቻላል?
አቶ ጌታቸው፡- የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ችግሮች ምንጮቻቸው በርካታ ናቸው፡፡ በተለይ ምርታማ ያልሆኑ ኢንቨስትመንቶች ላይ በግልም በመንግሥትም የሚፈሰው ሀብት መበራከቱ ለኢኮኖሚው መታመም ዋና መነሻ ነው፡፡ አገሪቱ ያላት ሀብትም ሆነ ካፒታል ውስን ነው፡፡ ይህን ሀብት ደግሞ ቶሎ ወደ ምርታማነት በሚሸጋገሩ ሥራዎች ላይ አሟጦ ማዋል ካልተቻለ ለኢኮኖሚው መልሶ ማነቆ ነው የሚሆነው፡፡ ቅድሚያ የሚሰጠውን በቅደም ተከተል ለይተህ ያለችህን ውስን ሀብት ተራ በተራ የማታውል ከሆነ አገሪቱን ኪሳራ ላይ ነው የምትጥለው፡፡ እንደ ነዳጅ ወይም ወርቅ የመሳሰሉ አውጥተን በአንዴ ወደ ገንዘብ ልንቀይራቸው የምንችላቸው የተትረፈረፉ የተፈጥሮ ሀብቶች የሉንም፡፡ አብዛኛውን የመንግሥት ገቢ ከቀረጥ፣ ከታሪፍና ከግብር፣ እንዲሁም ከብድርና ከዕርዳታ የሚገኝ ነው፡፡ ይህን ከመሰለ ውስን ምንጭ የሚገኝ ውስን ሀብትን ምርታማ ላልሆኑ ፕሮጀክቶች ኢንቨስት የምታደርግ ከሆነ ግን የሀብት ብክነት ነው የሚፈጥረው፡፡
ከዚህ አንፃር በግሉም ሆነ በመንግሥት የሚካሄዱ ኢንቨስትመንቶች መስመሩን በሳተ ሁኔታ ቶሎ ምርታማ ላልሆኑ ዘርፎች ነው የሚውሉት፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ አሁን ባለው የፀጥታ ችግር የተነሳ ብዙ አቅም ያላቸው የግሉ ዘርፍ ኢኮኖሚ አንቀሳቃሾች በአብዛኛው በሪል ስቴት ቢዝነስ ተገድበዋል፡፡ ትልቅ አቅም እያላቸው በቶሎ ለራሳቸውም ለአገራቸውም የተሻለ ገቢ የሚያስገኙ ሥራዎችን ትተው ግንባታ ለመምረጥ ብዙዎች እየተገደዱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ትልልቅ ፎቆችና ቤቶች እንደሚገነቡት ያህል፣ ኢንዱስትሪዎችና ሌሎች ብዙ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ፕሮጀክቶች ሲገነቡ አይታይም፡፡ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ ብዙ ሀብት እየፈሰሰ ነው፡፡ የሪል ስቴት ግንባታ ላይ ብዙ ሀብት ይውላል፡፡ ይህ ሁሉ ሀብት ደግሞ በቶሎ ገቢ ሊያመጣ በሚችል ዘርፍ ላይ ቢውል ኖሮ የተሻለ የኢኮኖሚ መነቃቃት ይፈጠር ነበር፡፡ ኮንስትራክሽን ዘርፉ ትልቅ ሀብት ይዞ የተቀመጠ ነው፡፡ የባንኮችን የገንዘብ እጥረት ያባባሰውና የብድር አቅም ያዳከመው አንዱ ምክንያት ይኸው ነው፡፡ አብዛኛውን በግሉ ዘርፍ የሚፈሰው ካፒታል ሀብት ይዘው ቁጭ በሚሉ ሥራዎች ላይ ነው የሚውለው፡፡ በመንግሥት የሚገነቡ ፓርኮችና መናፈሻዎችም ቢሆኑ ተመሳሳይ ውጤት ነው ያላቸው፡፡ ብዙ የአገር ሀብት እየፈሰሰባቸው ያሉ፣ ትልቅ አቅጣጫ ተይዞ የሚገነቡ የመናፈሻና የፓርክ ኢንቨስትመንቶች በአጭር ጊዜ ኢኮኖሚን አያሳድጉም፡፡ እነዚህ ግንባታዎች ከዚያ ይልቅ የዕድገት ውጤቶች ናቸው፡፡ ኢኮኖሚው ሲያድግ የሚታሰብባቸው እንጂ ውድ የአገር ሀብት የሚፈስባቸው አይደሉም፡፡ አገር ሲያድግ በራሱ ጊዜ ከተማ የማስዋብና የማሳመር ፍላጎትም አብሮ ይመጣል፡፡ ይህን መሰል ፕሮጀክት አቅዶ መገንባት ግን ዕድገት አምጪ አይደለም፡፡ በእነዚህ ፕሮጀክት ላይ የሚፈሰው ሀብት ተመልሶ የአገር ኢኮኖሚን የሚደግፍበት ሁኔታ ዝቅተኛ ነው፡፡ መንግሥት የሚገነባው የቤተ መንግሥት ፕሮጀክትም ቢሆን የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጠው አንገብጋቢ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህን ቤተ መንግሥት ለመገንባት ብዙ ሀብት እየዋለ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ብዙ ሀብት ይዞ ይቀመጣል፡፡ ይህ ደግሞ የአገሪቱን ውስን ሀብት የሚያዳክምና የፋይናንስ እጥረት እንዲፈጠር የሚያደርግ ነው፡፡
ጦርነትም ቢሆን ልክ ምርታማ እንዳልሆኑ ኢንቨስትመንቶች ኢኮኖሚን ያቃውሳል፡፡ ጥይት ስትተኩስ ዶላር ወይም ገንዘብ ነው የምትተኩሰው፡፡ ገንዘብ አውጥተህ ነው የምትዋጋው፣ ነገር ግን ኢንቨስትመንት አይደለምና ከኪሳራ ውጪ የሚያመጣልህ ትርፍ የለም፡፡ እሳት ይተፋል መልሰህ የምታገኘው ገቢ ግን የለም፡፡ አሁን ላይ ለጠመንጃ፣ ለተተኳሽና ለወታደር ብዙ ገንዘብ እየፈሰሰ ነው፡፡ ለወታደር ማሠልጠኛ ብዙ ገንዘብ ይፈሳል፡፡ ሄዶ ጦርነት ላይ እንዲሞት እንጂ አምራች ዜጋ እንዲሆን የሚደረግ ኢንቨስትመንት አይደለም፡፡ ይህ አዙሪት ደግሞ የኢኮኖሚ ቀውሱን አባብሶታል፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ኢትዮጵያ የኮሮና ወረርሽኝን ጨምሮ ብዙ አደጋዎችን አስተናግዳለች፡፡ ኮሮና ሳያንስ የአንበጣ መንጋና ድርቅ በተደጋጋሚ ተከስቶባታል፡፡ ይህ ደግሞ የኢኮኖሚ ችግር መፍጠሩ የሚካድ አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- ዓለም አቀፉ ተቀያያሪ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሁኔታ የፈጠረው ኢኮኖሚያዊ ችግርስ?
አቶ ጌታቸው፡- ዓለማችን ብዙ ዓይነት የኢኮኖሚና የፖለቲካ ዳይናሚክስ እያስተናገደች ነው፡፡ መጀመሪያ በሩሲያና በዩክሬን ቀጥሎ ደግሞ በእስራኤልና በፍልስጤም አካባቢ የተፈጠሩ ጦርነቶች የዓለም ኢኮኖሚ እንቅስቃሴን አዛብተዋል፡፡ በሩሲያና በዩክሬን ጦርነት መጀመሪያ ወቅት እንዲያውም ከፍተኛ የዘይት እጥረት በአገራችን ተከስቶ ነበር፡፡ ያ አካባቢ የዓለምን ከፍተኛ የስንዴና የዘይት ምርት የሚሸፍን ስለነበር ጦርነቱ ሲፈጠር የዓለም ምግብ ገበያ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ተፅዕኖ ፈጥሮ ነበር፡፡ የወረቀት ምርቶች ላይ ጭምር ከፍተኛ የዋጋ ንረት ፈጥሮብናል፡፡ እንደኔ ያሉ መጻሕፍት የሚጽፉ ሰዎች የሩሲያና የዩክሬን ግጭት ያመጣውን ተፅዕኖ ከርቀት ሆነን ዓይተነዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በጋዜጣ ኅትመት የተሰማሩትን ችግር ደግሞ ከዚህ አንፃር ማሰብ ይቻላል?
አቶ ጌታቸው፡- ‹ሳቅ…› አዎን በጣም እንጂ፡፡ ትልልቆቹ ዝሆኖች በሚያደርጉት ፍልሚያ ሳሩ ነው የሚጎዳው ይባላል፡፡ በሩቁ ቢሆኑም ትልልቆቹ ሲዋጉና ሲጣሉ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ደካማ አገሮች ተፅዕኖውን ለመጋፈጥ ሁሌም ይገደዳሉ፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ቀውስ ምንጭ ፖለቲካዊ መነሻ ያለው ነው ይባላል፡፡ የፖለቲካው ምስቅልቅል ነው ወደ ኢኮኖሚው የተጋባውም ይባላል፡፡ ይህንን በተጨባጭ የሚደግፍ ማሳያ ማቅረብ ይቻላል?
አቶ ጌታቸው፡- የአገሮቹ የሰላም ዕጦት የኢኮኖሚ ችግር ምንጭ እየሆነ ይገኛል፡፡ የሰላም ዕጦት ከጦርነት የተለየ ነው፡፡ በየአካባቢው ያሉ ሥራ አጥ ወጣቶች ሥራ በማጣታቸው የተነሳ አካባቢን ይረብሻሉ፣ ሥራና እንቅስቃሴን ያውካሉ፡፡ እኔ በግሌ ወደ መርቲ አካባቢ የነበረኝን የእርሻ ሥራ ከተውኩ አራት ዓመት ሆነኝ፡፡ በዚያው አካባቢ አብዛኛውን በእርሻ ሥራ የተሰማራ ባለሀብት ሥራውን ትቶታል፡፡ የፀጥታ ዕጦት አዳዲስ ቢዝነሶች እንዳይጀመሩ ብቻ ሳይሆን ነባር ኢንቨስትመንቶችም ሥራቸውን እንዲተው የሚያስገድድ ምክንያት ነው፡፡ የቱሪዝም ፍሰትንና የሰዎችን እንቅስቃሴም በእጅጉ ጎድቶታል፡፡ የሰዎች ፍሰትና እንቅስቃሴ ከሌለ ደግሞ ኢኮኖሚ ይኮማተራል፡፡ የዜጎች እምነት ማጣትና የብሔር ፌዴራሊዝም ፖለቲካው ኢትዮጵያን ከመቼውም ጊዜ በላይ እየጎዳት ነው ያለው፡፡ ሰዎች ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ ሄደው በግብርና፣ በማዕድን፣ ወይም በማምረቻ ዘርፍ እንዳይሠሩ በፖለቲካው ላይ እምነት ማሳደር ተቸግረዋል፡፡ አብዛኛው ባለሀብት አዲስ አበባ ተወስኖ ነው ያለው፡፡ አዲስ አበባም ቢሆን ሰው ቋሚ ሀብት ማፍራት ወይም ፎቅና ቤት ግንባታ ላይ ነው ተሰማርቶ ያለው፡፡ አዲስ አበባ ደግሞ ሰፊ ከሆነችው ኢትዮጵያ ትንሽ ክፍል ናት፡፡ ሰዎች በፖለቲካ ሥርዓቱ በተለይ በብሔር ፌዴራሊዝሙ ላይ እምነት ስላጡ የትም ቦታ ሄደው ኢንቨስት ለማድረግ ይፈራሉ፡፡ ይህ በመሆኑ ደግሞ ከፍተኛ የምርትና አገልግሎት እጥረት አገሪቱ ገጥሟታል፡፡ በዘር ፌዴራሊዝም የተገነባው የፖለቲካ ሥርዓቱ አግላይ ነው፡፡ በየትም ቦታ ተንቀሳቅሶ ሀብት የማፍራት ዕድልን ይገድባል፡፡ በኢትዮጵያ ተንቀሳቅሶ ለመሥራትም ቢሆን ዋስትና የታጣበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ እኔ ለምሳሌ በቀደም ዕለት አምቦ ነበርኩ፡፡ ከአምቦ ወጥቼ ወደ ታች ለመሄድ ብፈልግም የፀጥታ ሥጋት ስላለ ይቅርብህ ነው የተባልኩት፡፡
ነጋዴም ሆነ ኢንቨስተር ብዙ ጊዜ ዋስትና ያለው አካባቢን ነው የሚመርጠው፡፡ አንድ ቦታ ለመሥራት መተማመኛ ካጣ ማንም አይገባም፡፡ ሀብቱን ማፍሰስና አደጋ ላይ መውደቅ ማንም አይፈልግም፡፡ ይህ የኢንቨስተር መሠረታዊ ባህሪ ነው፡፡ የውጭም ሆነ የአገር ውስጥ ባለሀብት ማንም አደጋ ተጋፍጦ መሥራትን አይፈልግም፡፡ የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግርም ለኢኮኖሚ መውደቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ከውጭ የሚመጡ ኢንቨስተሮችን፣ ባለሀብቶችን ወይም ዳያስፖራዎችን ብቻ ሳይሆን በአገር ቤት ያለውንም ሥራ መሥራት የሚፈልግ ሁሉ የሚያስመርር ነው፡፡ ትንሽ ጉዳይ ለማስፈጸም የምትጠየቀው ጉቦ ከፍተኛ ነው፡፡ የሚያናግርህና በቀናነት የሚያስተናግድህ ሰው የለም፡፡ አብዛኞቹ ከውጭ የገቡ የህንድና የሌላም አገር ድርጅቶች እየተማረሩ ለቀው ሲሄዱ ታዝቤያለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- በየጊዜው የተለያዩ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ይወጣሉ፡፡ እነዚህ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሚባለው ደረጃ በኢኮኖሚው ዘርፍ የሚጨበጥ ዕድገትና ለውጥ የማይፈጥሩት ለምንድነው?
አቶ ጌታቸው፡- ኢኮኖሚያችን ከሚፈተንባቸው ችግሮች አንዱ የፖሊሲ ችግር ነው፡፡ እኔ ኢኮኖሚስት ነኝ፣ ነገር ግን ኢኮኖሚው በምን ዓይነት የፖሊሲ አቅጣጫ እንደሚመራ ግልጽ አይሆንልኝም፡፡ የአንድ አገር ኢኮኖሚን ለመምራት የአገሩን ተነፃፃሪ መወዳደሪያ (ኮምፓራቲቭ አድቫንቴጅ) በግልጽ መለየትና ማስቀመጥ ይጠይቃል፡፡ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ ለማሸነፍ የሚያስችሉ ተነፃፃሪ መወዳደሪያዎችን የለየ ፖሊሲ አውጥተህ ከታችኛው መዋቅር እስከ ላይኛው በደንብ አስጠንተህ ተግባራዊ ለማድረግ ካልቻልክ ኢኮኖሚው ሊነቃነቅ አይችልም፡፡ ሁሉን ነገር መግዛት፣ ሁሉን ነገር ማድረግ ወይም ሁሉን ነገር መሥራት አትችልም፡፡ ይህ ደግሞ በግለሰቦች ደረጃ ያለ ብቻ ሳይሆን በአገር ደረጃም የሚገጥም ውስንነት ነው፡፡ ግለሰብ እንደማይችለው አገሮችም አይችሉም፡፡ ስለዚህ ያለህ ነገር ላይ አተኩረህ መሥራት አለብህ፡፡ ውጤታማ ልትሆንባቸው የምትችልባቸውን መስኮች በመለየት መሥራት ይጠይቃል፡፡ በዚህ በኩል የፖሊሲ ችግር አለ፡፡ የተምታታ ነገር ነው የሚታየው፡፡ ይህ ደግሞ ለኢኮኖሚው መዳከም ችግር ሆኗል፡፡ ብዙ አገሮች ያደጉትና በዓለም ተወዳዳሪነታቸውን ያሰፉት ያላቸውን ዕምቅ አቅም ለይተው እሱን አውጥቶ መጠቀም በመቻላቸው ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ የጠራ ፖሊሲ ሊኖር ይገባል፡፡
ሪፖርተር፡- ኢኮኖሚው አዳዲስ ዕድሎችን መፍጠር እንዳቃተውና አዳዲስ የሥራ ዕድሎች መፍጠር ተስኖታልም ይባላል፡፡ ኢኮኖሚው ተጨማሪ የሰው ኃይል ወደ ሥራ ማስገባት የከበደው በምን የተነሳ ነው?
አቶ ጌታቸው፡- የአምራች ዜጋ ቁጥር በኢትዮጵያ ዝቅተኛ ነው፡፡ አብዛኛው ለመብል እንጂ ለሥራ ያልደረሰ ሕዝብ ነው ያለው፡፡ ለሥራ የደረሰውም ቢሆን የሚሰማራበት የሥራ ዕድል እንደ ልብ የሚገኝ ባለመሆኑ የተነሳ፣ የፀጥታ ችግርን ጨምሮ በአገር ላይ ብዙ የኑሮ ምስቅልቅል ይፈጠራል፡፡ አዳዲስ የሥራ ዕድል ለመፍጠር መፍትሔ ተብሎ የተጀመረው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታም ኪሳራ ነው ያመጣው፡፡ ኢንዱስትሪ ፓርክ መገንባት የኢንዱስትሪ መስፋፋትን አያመጣም፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተገነቡ ያሉት በውጭ ብድር፣ በዕርዳታና በልመና ነው፡፡ ቂሊንጦ የሚገኘው የኢንዱስትሪ ፓርክ ብዙ ገንዘብ ወጥቶበታል፡፡ ግን እንደምታዘበው ገብቶ እየሠራበት ያለው ባለሀብት ትንሽ ነው፡፡ ለፓርኩ መሠረተ ልማት ማሟያ የፈሰሰው በርካታ ገንዘብ ሳይመለስ ተቀምጧል ማለት ነው፡፡ የያዘው መሬት ለእርሻ ቢውል ኖሮ ብዙ ሰብል ይሰበሰብበት ነበር፡፡ ኢንዱስትሪ የሚታሰበው የጥሬ ዕቃ ምርትና ምርታማነት ሲኖር ነው፡፡ ወይም ደግሞ ያልተጠበቀ የተፈጥሮ ሀብት ስታገኝ ሊሆን ይችላል ወደ እዚህ የሚተኮረው፡፡ እኛ ጋ ግን በየቦታው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተገንብተዋል፡፡ ነገር ግን ምን ያህል ውጤታማ ናቸው የሚለው ጥያቄ የሚነሳበት ነው፡፡ ጥቂት የኢንዱስትሪ ዞኖች ካልሆኑ በስተቀር በውጭ ብድር የተገነቡና ብዙ ሀብት የፈሰሰባቸው የኢንዱስትሪ ዞኖቻችን በታሰበው መንገድ ውጤታማ አለመሆናቸው ታይቷል፡፡ በየቦታው የተገነቡና በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን የሚያስመርቁ ዩኒቨርሲቲዎቻችንም ቢሆን ተመሳሳይ ውጤት ነው ያላቸው፡፡ እነሱ የሚያስመርቁትን ያህል የሰው ኃይል የሚቀበል የሥራ ዕድል እየተፈጠረ አይደለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲዎቹን ማስተዳደርና መምራት ራሱን የቻለ ከፍተኛ ሀብትና ጉልበት የሚጠይቅ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ኢኮኖሚው በየዓመቱ በዚህን ያህል በመቶ አደገ ይባላል፡፡ ብዙዎች ግን ይህ ለሪፖርት የሚነገር አኃዝ እንጂ ትርጉም ያለው ዕድገት አለመኖሩን ይከራከራሉ፡፡ እርስዎ በንግድ እንደ መሰማራትዎና ዘርፉን እንደሚያጠና ሰው በተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አለ ይላሉ?
አቶ ጌታቸው፡- አኃዙ አለ፣ ዕድገት የለም ብሎ መካድ አይቻልም፡፡ ቁጥሩ ቢያከራክርም ዕድገቱ አለ፡፡ ነገር ግን ዕድገቱ ጤናማ አይደለም፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገት በኢትዮጵያ አለ ብለን እንድንናገር የሚያደርጉ ሰዎች፣ ምናልባት ከአሥር ሺሕ የማይዘሉ ውስን ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የገቢ አለመመጣጠን ከፍተኛ እየሆነ ነው፡፡ ስለዚህ ኢኮኖሚውን የሚቆጣጠሩት የተወሰኑ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከዚህ ውጪ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ይህን ያህል ደረሰ የሚባለው ብዙ ጊዜ የሚሰላው የዋጋ ግሽበትን ታሳቢ ሳያደርግ ነው፡፡ የዛሬ ሦስት ዓመት የአሥር ሺሕ ብር የመግዛት አቅምና ዛሬ ያለው አቅም አንድ አይደለም፡፡ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከፍተኛ መቃወስ ውስጥ ነው ያለው፡፡ ኢኮኖሚው አድጓል ለማለት ይህን የሚደግፍ የምታየው ነገር የለም፡፡ የኢኮኖሚ አኃዝ ጭማሪ አለ፡፡ ነገር ግን ኢኮኖሚው አድጓል እንዳትል ብዙ ነገሮች ይፈትኑኃል፡፡ የገንዘብ የመግዛት አቅም እየተዳከመና የኑሮ ውድነት እየጨመረ ነው የመጣው፡፡ በሌላ በኩል የድህነት ምጣኔ መጨመሩን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች እየወጡ ነው፡፡ ሰዎች በየቀኑ እየደኸዩና ለመኖር እየተቸገሩ በተጨባጭ እየታየ ኢኮኖሚው እያደገ ነው ብሎ መከራከር ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ሌላውን ትተን የዋጋ ግሽበቱ ግምት ውስጥ ገብቶ የዕድገት አኃዙ ቢለካ ቁጥሩ በእጅጉ ማሽቆልቆሉ አይቀርም፡፡ ለምሳሌ የዛሬ አምስት ዓመት አንተ የአሥር ሺሕ ብር ደመወዝተኛ ነበርክ እንበል፡፡ ዛሬ ደግሞ 20 ሺሕ ብር ይከፈልሃል ቢባል ያንተ ገቢ እኮ 100 በመቶ ነው ያደገው፡፡ ነገር ግን የዛሬ አምስት ዓመት በአሥር ሺሕ ብር ትኖር የነበረውን ኑሮ ዛሬ ትኖረዋለህ ወይ የሚለውን ብትጠየቅ ግራ ነው የሚገባህ፡፡ ኢኮኖሚህ መቶ በመቶ አደገ ተብሎም ከካቻምናውም ሆነ ከአምናው የተሻለ ኑሮ መኖር ሊከብድህ ይችላል፡፡
ሪፖርተር፡- ኢኮኖሚያዊ ነፃነትን ማስፋት (ኢኮኖሚክ ሊበራላይዜሽን) እንዲሁም ለውጭ ኢንቨስትመንትን በሰፊው መክፈት በመፍትሔነት ይነሳል፡፡ መንግሥት የኒዮ ሊበራሊስቶች ጣልቃ ገብነት እያለ ለረዥም ጊዜ ሲያጣጥለው ቢቆይም፣ አሁን ግን ከእነ ዘገምተኝነቱ ተዘግተው የቆዩ የኢኮኖሚ መስኮችን ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት የማድረግ ዕርምጃ እየወሰደ ነው፡፡ የመንግሥትን የኢኮኖሚ ጣልቃ ገብነት መቀነስ መጀመሩም ይነገራል፡፡ አሁን ላጋጠሙ የኢኮኖሚ ችግሮች ይህንን እንደ አንድ መፍትሔ ማቅረብ ይቻላል?
አቶ ጌታቸው፡- አይሆንም፣ ቅድም እንዳነሳሁት ፈረንጆቹ በኢኮኖሚ ትምህርት ስም ካስተማሩን የውሸት ትምህርት አንዱ ይህ ነው፡፡ እነሱ እኮ አሁንም ኢኮኖሚን ሊበራላይዝ አላደረጉም፡፡ ኢቲዮ ቴሌኮምን ከፍተን ዓይተነዋል፡፡ ሆቴሎችንና ሌሎች የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ሸጠን ዓይተነዋል፡፡ እኔ የላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪ ውስጥ ሠርቻለሁ፡፡ በመንግሥት ሥር የነበረው ለግል ተሸጦ ምን ሲሠራ እንደነበር ዓይቻለሁ፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ዕርምጃ ውጤቱን ስትገመግመው የተለየ ነገር አታገኝም፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ለምን ብቻውን ተብሎ ሳፋሪኮም መጣ፡፡ እሱ በመምጣቱ ግን የዶላር ግኝታችን አልጨመረም፡፡ የእሱ መምጣት ያመጣው ነገር ካለ በተጨባጭ ማየት ይኖርብናል፡፡ እኔ በግሌ በመንግሥት ይዞታ ሥር መቆየት አለባቸው ብዬ የማምንባቸው ዘርፎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት የጥሬ ዕቃ አቅርቦት በመንግሥት መሥራት አለበት ብዬ ነው የማስበው፡፡ በግል አትራፊ ላይሆን ስለሚችልና ትልቅ ኢንቨስትመንት ስለሚጠይቅ ጥሬ ዕቃን ለኢንዱስትሪ ለማምረት ብዙዎች አይሰማሩም፡፡ አትራፊ የሆኑ ዘርፎች ላይ ማንም ለመግባት አያንገራግርም፡፡ ስለዚህ መንግሥት የአንዱስትሪዎችን መሠረታዊ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ መሰማራት ግዴታ አለበት፡፡ የግል ዘርፉን ለማበረታታት መንግሥት ሊወስዳቸው የሚገቡ ብዙ ዕርምጃዎች መኖር አለባቸው፡፡ ፋብሪካዎች በጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር ከሚዘጉና የግሉ ዘርፍ ከኢንዱስትሪ መስክ ከሚርቅ የዘርፉን ክፍተቶች መሙላት ከመንግሥት ይጠበቃል፡፡
የኃይል ማመንጨትና አቅርቦት ዘርፍ ለውጪ ኢንቨስትመንት ክፍት መሆን አለበት ይባላል፡፡ ይሁን እንጂ ክፍትስ ቢሆን ማን ይገባበታል ተብሎ መታሰብ አለበት፡፡ የኃይል አቅርቦት ዘርፍ መጠነ ሰፊ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ ነው፡፡ በቀላሉ መሠራት የማይችል ዘርፍ ነው፡፡ ዘርፉ ስለተከፈተ ብቻ ኢንቨስተሮች ተንደርድረው መጥተው ይገቡበታል የሚል ዕሳቤ መኖር የለበትም፡፡ የኢኮኖሚ ሊበራላይዜሽንና ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት የማድረግ ጉዳይ በኢኮኖሚ ትምህርቶች ስለሚሰጥ ብቻ ተደጋግሞ ይነሳል እንጂ፣ በተጨባጭ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣቱን እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ ከዚህ ይልቅ ሌሎች ትርጉም ያላቸው የተሻሉ የኢኮኖሚ ማነቃቂያ ዕርምጃዎችን መውሰድ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያለው የግብር አሠራር ሥራ ፈጣሪዎችን የሚያበረታታ አይደለም፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግሩና ሙስናው ተጨምሮበት መንግሥት የግሉን ዘርፍ እንደ ሌባ ነው የሚያየው፡፡ ገቢዎችና ነጋዴው ሌባና ፖሊስ ሲጫወቱ ነው የሚኖሩት፡፡ እህቶቻችን የጀበና ቡና መሸጥ ሥራ ሠርተው እንዳይኖሩ እንኳን ብዙ እንግልት ይገጥማቸዋል፡፡ ከሚያገኙት አንፃር ከፍተኛ ግብር ነው የሚጠየቁት፡፡ የግሉ ዘርፍ በግብርና በንግድ አሠራሮች ተቀፍድዶ የተያዘ ነው፡፡ ጉቦ ይጠየቃል፣ መረጃ አያያዝ ላይ ችግር አለ፣ ግምት የተጋነነ ነው፣ ተመን ይጣልብሃል፣ መጉላላት ይገጥምሃል፣ የንግድ ቤት አከራዮች ዋጋ እንዲጨምሩ የሚገፋፋ አሠራር ነው የሚተገበረው፡፡ ይህ ሁሉ ውጣ ውረድ ሥራ ፈጠራን ያቀጭጫል፣ ንግድና የኢኮኖሚ ዕድገትንም ያደናቅፋል፡፡ እኔ የንግድ ሥልጠናዎችን እሰጣለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ፈጠራ፣ ንግድና ኢንቨስትመንት እንዳያድግ ትልቁ እንቅፋት መንግሥት ነው፡፡ የመንግሥት አሠራር በችግር የተተበተበ ነው፡፡ ኢኮኖሚው አደገ ሥራ ተፈጠረ እየተባለ አኃዝ የሚነገረው በአብዛኛው ለዜና ፍጆታ ነው፡፡ ብዙ የሥራ ዕድል መፍጠር በሚችለው የግሉ ዘርፍ ላይ እንቅፋት የሚፈጥረው ሌላ ነገር ሳይሆን ራሱ መንግሥት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በጦርነትም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች ኢኮኖሚው የገጠመውን ከባድ ችግር ለመቅረፍ ተበታትኖ ያለውን የአገር ሀብት ወደ አንድ አሰባስቦ መረባረብ እንደሚጠይቅ አንዳንዶች ይመክራሉ፡፡ ለምሳሌ የህዳሴ ግድብ በሕዝቡ ርብርብ እንደተገነባው ሁሉ በጦርነት የወደሙና የተጎዱ አካባቢዎችንም ሕዝብ አስተባብሮና ሀብት አሰባስቦ መልሶ መገንባት ይቻላል ይላሉ፡፡ ይህን ተደጋግፎና ተባብሮ ኢኮኖሚውን የመገንባት አማራጭ መከተል ይገባል ብለው ያስባሉ?
አቶ ጌታቸው፡- አሁን እኮ ማን ማንን ነው የሚደግፈው? ሁሉም እኮ ወድቋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ በቅርበት ነው የምንከታተለው፡፡ ለምሳሌ አዳዲሶቹ ሲዳማ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ደመወዝ መክፈል እንኳን እንደተቸገሩ እንሰማለን፡፡ የአዲስ አበባ ከተመ አስተዳደር እንኳ ይኼው ችግር እንዳጋጠመው ሰሞኑን ሲወራ ሰምቻለሁ፡፡ ከተለያየ ቦታ ሀብት አሰባስቦና አቅምን አስተባብሮ ኢኮኖሚን ማነቃቃት ይቻላል የሚባለው ጉዳይ የሚሠራው፣ የሆነ አካባቢ የተሻለ አቅምና መነቃቃት ሲኖር ነው፡፡ በጦርነቱ በአማራና በትግራይ ክልሎች ብቻ እኮ ወደመ የሚባለው እጅግ ብዙ ሀብት ነው፡፡ እሱም ሳያንስ በሰላም ዕጦት ሳቢያ አሁንም ድረስ ከፍተኛ ችግር ኢኮኖሚው እያስተናገደ ነው፡፡ ጦርነቱ ቆመ ሰላም ወረደ ተባለ፣ ነገር ግን አሁንም ድረስ አማራ ክልልን አቋርጦ የሚያልፍ የየብስ ትራንስፖርት አልተጀመረም፡፡ በአፋር ክልል አልፎ የሚሄድ ትራንስፖርት ካልሆነ በስተቀር የአውሮፕላን መጓጓዣ ብቻ ነው ወደ መቀሌ ያለው፡፡ አምቦን አልፈህ ወደ ወለጋ መስመር መሄድ አትችልም፡፡ በኢትዮጵያ በፀጥታ ችግር የተነሳ የማይደረስባቸው አካባቢዎች ብዙ ናቸው፡፡ ከምንም በላይ የችግራችን ሁሉ መነሻ የሰላም ዕጦት ነውና ሰላሙን ማስጠበቅ ሊቀድም ይገባል፡፡ መተማመን መፍጠር ይኖርብናል፡፡ ዜጎች ለመሥራት፣ ለመንቀሳቀስ፣ ለመነገድም ሆነ ወጥቶ ለመግባት በመንግሥት ላይ አመኔታ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ለችግሩ መነሻ ለሆኑ ችግሮች መጀመሪያ መልስ መስጠት ይኖርብናል፡፡
ሪፖርተር፡- ለኢኮኖሚ ሕመሙ እርስዎ በግልዎ መፍትሔ የሚሏቸው የማገገሚያ ሐሳቦች አሉ?
አቶ ጌታቸው፡- ኢትዮጵያ ሰፊ አገር ናት፡፡ በግብርናው ዘርፍ ለመሰማራት ከአገሪቱ መሬት ከ30 በመቶ በላይ አመቺ ነው ይባላል፡፡ እስካሁን የምንጠቀመው ግን ውስን መሬት ነው፡፡ ስለዚህ አዳዲስ መሬቶችን ወደ ግብርና ሥራ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ ጥቅም ላይ ያልዋሉ መሬቶችን በመስኖ ጠለፋም ሊሆን ይችላል በሌላ መንገድ ለግብርና ሥራ ማዋል ይኖርብናል፡፡ እስካሁን እየተሠራ ያለው ለሽንኩርትና ለቲማቲም ይውል የነበረ መሬትን ወስዶ ለስንዴ የማዋል አሠራር ነው፡፡ ሽንኩርትና ቲማቲም ከልክሎ ስንዴ ማስመረት ተመልሶ የገበያ ቀውስ ነው ሲፈጥር የታየው፡፡ ያሉት መሬቶች እንዳሉ ሆነው ምርታማነትን ማሳደግ የሚችሉ አዳዲስ መሬቶችን ማስፋት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ሌላው መፍትሔ ላለፉት 3,000 ዓመታት የቆየንበትን የግብርና አመራረት ባህል መቀየር አለብን፡፡ የመሬቱ ምርታማነት በየጊዜው እየወረደ ነገር ግን በኋላ ቀር አስተራረስ በማዳበሪያና በኬሚካል ፍዳውን እያሳየነው ነው፡፡ የግብርናው በተጨባጭ ካላደገ ኤክስፖርትና የኢንዱስትሪ ግብዓት ብቻ ሳይሆን መሠረታዊ ፍጆታም አገሪቱ ሲቸግራት ይኖራል፡፡ ለዕርዳታ የሚመጣ ስንዴን ግብዓት የሚያደርጉ ዳቦ ቤቶች እኮ ነው ያሉን፡፡ ሌላው መፍትሔ የግሉ ዘርፍ የማይሠራቸውን የግብርና ሥራዎችን መንግሥት ማከናወን አለበት፡፡ መንግሥት ባለሀብት ሊገባባቸው በማይችሉ ለግብርና በተመቹ አካባቢዎች ገብቶ ሰፋፊ እርሻ ልማቶችን መሥራት አለበት፡፡ ባለሀብቶች ሰፋፊ እርሻዎችን እንዲያለሙ መበረታታት አለባቸው፡፡ ነገር ግን ባለሀብቶች በማይደርሱባቸው አካባቢዎች የመንግሥት ሚና አስፈላጊ ነው፡፡ አንዳንድ የግብርና ውጤቶች የተትረፈረፉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የቆዳ ምርት በኢትዮጵያ የተትረፈረፈ ነው፡፡ በየቤቱ የሚታረዱ እንስሳት ቆዳ ፈላጊ አጥቶ ሲጣል ይታያል፡፡ አገሪቱ ግን በርካታ ሚሊዮን ዶላሮችን ለቆዳ ውጤቶች ከውጭ ማስገቢያ ትከፍላለች፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግርን ለመቅረፍ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ ነው፡፡ ቆዳውን ወደ ጫማ መለወጡን የግሉ ዘርፍም የሚሠራው ቢሆንም፣ ጥሬ ዕቃውን አሰባስቦ ማቅረቡ ላይ መንግሥት ቢገባ አገሮቹ ብዙ ትጠቀማለች፡፡ ሌላኛው መፍትሔ የምለው የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች (ኢኖቬሽን) ላይ አተኩሮ መሥራትን ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ያልተነኩ የማዕድን ዘርፍ ልማቶችን ማስፋፋትም አስፈላጊ ነው፡፡ ወርቅ፣ የድንጋይ ከሰል፣ ዩራኒየም፣ ቶርማሊን፣ ሳፋየር፣ ኤመራልድ፣ ወዘተ አገሪቱ ብዙ ዓይነት ማዕድናት የታደለች ናት፡፡ የብረት ማዕድን ዋግ ህምራ አካባቢ በሰፊው አለ፡፡ ስለዚህ ዝም ብለህ ፓርክ ከመገንባትም ሆነ አሻንጉሊት ከመግዛት ያለህን ሀብት አውጥተህ ብታለማ አገር ትቀይራለህ፡፡ ኢንዱስትሪ ሳናስገባው በጥሬው እንኳ ለውጭ ገበያ ብንጭነው ብዙ እናተርፍበታለን፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የዜጎችን ምርታማነት ሊያሻሽል የሚችል መዋቅርና አደረጃጀት መፍጠርም ሊታሰብበት ይገባል፡፡ እስካሁን ሲሠራበት የቆየው አስተዳደራዊ መዋቅር የፖለቲካ መሣሪያ እንጂ ልማትን የሚያበረታታ አይደለም፡፡ ወረዳና ቀበሌ እያለ የሚሄደው መዋቅር ለልማት አልጠቀመም፡፡ በዚህ ላይ በግሌ ብዙ እያጠናሁ ነው፡፡ ፈጣሪ ከረዳኝ ሁኔታውን የሚቀይር የጥናት ውጤት ይዤ እቀርባለሁ፡፡ ወረዳና ቀበሌ እየተባለ ለፖለቲካ መገልገያነት የተፈጠረው መዋቅር በልማት ማዕከላት ቢተካ የሚል የራሴ ሐሳብ አለኝ፡፡ አንድ ዞን ለምሳሌ በምሥራቅ ሸዋ ዞን ወደ 20 ወረዳዎች አሉ፡፡ በሁሉም ወረዳዎች 800 አካባቢ ቀበሌዎች አሉ፡፡ ሁሉም አካባቢዎች ደግሞ ለተለያዩ ልማቶች የተመቸ የየራሳቸው ዕምቅ አቅም አላቸው፡፡ በየአካባቢው ያለውን ዕምቅ አቅም ያማከሉ የኢኮኖሚ ማዕከላት ቢፈጠሩና መንግሥትም የየአካባቢው ሕዝብም ሼር ቢኖራቸው፣ ከአስተዳደር ሥራ ጎን ለጎን ውጤታማ ልማት በየቦታው ማካሄድ ይቻላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ነባሩ አስተዳደራዊ ሥርዓት ለፖለቲካና ለአስተዳደር ሥራ እንጂ ለልማት የሚጠቅም አይደለም የሚል እምነት አለኝ፡፡ ኢንዱስትሪዎቻችን ባላቸው አቅም እንዲያመርቱ ማድረግ መቻልም ሊታሰብበት ይገባል፡፡ በአገር ደረጃ የማምረት ዘመቻ ቢካሄድ እመክራለሁ፡፡ የፖለቲካ ሰዎች ሳይሆኑ የተማሩ ሰዎች በሚመሩት አደረጃጀት፣ በአገር ደረጃ ምርታማነትን የሚያሳድግ ዘመቻ ቢደረግ ነው የምለው፡፡ የገንዘብ ፖሊሲ ላይ ብቻ በመጫወት ተጨባጩን የምርታማነት ጉዳይ ወደ ጎን ብሎ የሚመጣ ለውጥ የለም፡፡