December 31, 2023 

የሹፌሮች ጉዳይ . . .

” በ2 ሳምንታት ብቻ ሰባት ሹፌሮች በታጣቂዎች ተገድለዋል። ከ2014 ዓ/ም ጀምሮ የተገደሉት ወደ 70 ይደርሳሉ ” – ጣና የአሽከርካሪዎች ማኀበር

በጅማና በአዲስ አበባ ከተማ መካከል ‘አስጎሪ’ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ሲያሽከረክሩ በነበሩ ሹፌሮችና ተሽከርካሪዎች ላይ ታጣቂዎች ታህሳስ 17 ቀን 2016 ዓ/ም ጥቃት ማድረሳቸውን ስሜ ከመጠቀስ ይቆይ ያሉ የዓይን እማኝ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

የዓይን እማኙ በሰጡት ቃል፣ “ ዓይኔ እያዬ ነው ሹፌሮቹን የገደሏቸው። ተሽከርካሪዎቹንም አቃጠሏቸው ” ሲሉ የተመለከቱትን አስረድተዋል።

ጥቃቱን የፈጸሙት እነማን እንደሆኑ፣ ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉ፣ ምን ያህል ተሽከርካሪዎች እንደተቃጠሉ እንዲገልጹ ጥያቄ የቀረበላቸው ታማኝ ምንጩ፣ ጥቃቱን የፈጸሙት ታጣቂዎች እንደሆኑ፣ ሹፌሮች ከታጣቂዎቹ በተተኮሰ ጥይት እንደተመቱ፣ አንድ ሹፌር ሕይወት ማለፉን፣ ከ11 በላይ ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸውን አብራርተዋል።

ስለ ሁኔታው ማብራሪያ እንዲሰጥ ከቲክቫህ ኢትዮጵያ ጥያቄ የቀረበለት የሹፌሮችን በታጣቂዎች እገታና ግድያ በጥልቀት በየወቅቱ የሚከታተለው ጣና የአሽከርካሪዎች ማኀበር (በማኀበራዊ ትስስር ገጹ “የሹፌሮች አንደበት) በበኩሉ፣ ማኀበሩ ባለው ክትትል መሠረት፣ “በሁለት ሳምንታት ብቻ ሰባት ሹፌሮች በታጣቂዎች ተገድለዋል። ከ2014 ዓ/ም ጀምሮ የተገደሉት ወደ 70 ይደርሳሉ ” ብሏል።

ይህን ያሉት ማኀበሩን የሚመሩ አንድ ምንጭ አክለውም ሹፌሮች የተገደሉት በሰሜን ጎንደር ማክሰኝት፣ በመተሃራ፣ በቡታጅራ መስመር፣ በደሴ መስመር በኦሮሚያ ልዩ ዞንና በሌሎች አካባቢዎች መሆኑን አስረድተዋል።

“ ከቀናት በፊትም በኦሮሚያ ክልል በቡታጅራ መስመር ከአሥር በላይ ተሽከርካሪዎች ተቃጥለዋል። አሽከርካሪዎችም በቅድሚያ  መንገዱን እያጣሩ መጓዝ አለባቸው ” ሲሉ አሳስበዋል።

የታጣቂዎቹ ዋነኛ ፍላጎት ምን እንደሆነ ተጠይቀው ሲያስረዱም፣ አንደኛ የገንዘብ ፍላጎት፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ እንዳይኖር ሰላምን ማወክ አላማቸው አድርገው በመነሳተቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ምን ቢደረግ መፍትሄ ሊመጣ ይችላል ? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ “ አሁን የትራንስፖርትና ሎጅስቲክ ሚኒስቴር አለ። በፓርላማ እየቀረበ ‘ይህን ያህል አጓጓዝን፣ ይህን ያህል አመላለስን’ ይላል የተጓጓዘውን የአገሪቱን ምርት። በፓርላማ ግን ሹፌሮች ተገድለዋል ብሎ መናገር አለበት ” ብለዋል።

አክለውም፣ “ ችግሩ በሚስተዋልባቸው ክልሎች የተከሰቱትን ችግሮች እንዲስተካከሉ መጠየቅ ነበረበት። ያ ሲጠየቅ ግን አይስተዋልም ” ሲሉ ወቅሰዋል። ካልሆነ ግን አሽከርካሪዎች አድማ በምታት ከመንቀሳቀስ ተቆጥበው ሕይወታቸውን ማትረፍ ግድ ይላቸዋል ተብሏል።

በየወቅቱ የሚስተዋለውን ችግር በተመለከተና ለተነሳው ወቀሳ ምን ምላሽ እንዳለው ቲክቫህ ኢትዮጵያ ከትራንስፖርትና ሎጅስቲክ ሚኒስቴር ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

ዘገባውን የላከው የአ/አ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባል ነው።