ከ21ሺህ 800 ሰዎች በላይ ተገድለዋል ይላል በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስትር
የምስሉ መግለጫ,ከ21ሺህ 800 ሰዎች በላይ ተገድለዋል ይላል በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስትር

ከ 4 ሰአት በፊት

የእስራኤል መከላከያ በጋዛ የተጀመረው ጦርነት በአዲሱ ዓመት እንደሚቀጥል አስታወቀ።

የመከላከያ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ዳንኤል ሃጋሪ እንዳሉት ወታደሮችን ለረዥም ጦርነት የማዘጋጀትና የማደላደል ሥራ ከወዲሁ ተጀምሯል።

ይህም ማለት በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት ሙሉ ጦርነቱ ይቀጥላል ሲሉ ዘለግ ላለ ዘመቻ እየተዘጋጁ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ቃል አቀባዩ ጨምረው እንዳሉት የተወሰኑ ተጠባባቂ ጦር አባላት በዚህ ሳምንት ወደ ጋዛ ይሸኛሉ።

በጋዛ ጦርነት እስከ አሁን ከ21ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ብዙዎቹ ደግሞ ሴቶችና ሕጻናት ናቸው።

ይህን ያለው በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስትር ነው።

እስራኤል ጥቃቱን የከፈተችው ሐማስ ድንበር ተሻግሮ መብረቃዊ ጥቃት በመፈጸም 1200 ሰዎችን ከገደለና 240 ሰዎችን አግቶ ከወሰደ በኋላ ነበር።

እስራኤል ጋዛ ላይ የምታደርሰውን መጠነ ሰፊ ጥቃት አሮጌው የፈረንጆች ዓመት እስከተሸኘበት መጨረሻ ሰአት ድረስ አላቋረጠችም።

ትናንት እሑድ ብቻ ሌሊቱን 48 ፍልስጤማዊያን በጋዛ ከተማ ተገድለዋል። ከዚህም ባሻገር ብዙ ሰዎች በፍርስራሾች ተቀብረዋል።

ሌላ ጥቃት ደግሞ በአል አቅሳ ዩኒቨርስቲ ተጠልለው የነበሩ 20 ፍልስጤማዊያንን ገድሏል። መረጃውን ያወጣው ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ነው። ቢቢሲ ይህን መረጃ በራሱ አላረጋገጠም።

የተባበሩት መንግሥታት ባወጣው መረጃ የጋዛ 85 ከመቶ ሕዝብ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሏል። ይህም በአሐዝ ሲቀመጥ ከ2 ሚሊዯን ሕዝብ በላይ ይሆናል።

‘’ዛሬ የተቀረው ዓለም ሰማይ በርችት፣ በደስታና ሳቅ ይሞላል። የኛ የጋዛ ሰማይ ደግሞ ከእስራኤል በሚዘንብ ቦምብ ይሞላል” ስትል ዘይናብ ከሊል የተባለች የ57 ዓመቷ የሰሜን ጋዛ ነዋሪ ለሮይተርስ ተናግራለች።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ቅዳሜ ዕለት ጦርነቱ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ተናግረው ነበር።

“በሁሉም ግንባር እየተዋጋን ነው። ትልቅ ድል እያስመዘገብን ነው። ሆኖም ይቀረናል። ሙሉ ድል ጊዜን ይሻል’’ ብለዋል።

እንደ እስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ከሆነ በጋዛ የተጀመረው ጦርነት ለብዙ ወራት የሚቀጥል ይሆናል።

ትናንት እሑድ የእስራኤል ጥቃት በማእከላዊ ጋዛ አልማጋዚና አልቡረጄ አካባቢ ነበር። እሑድ ጠዋት ደግሞ በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስትር 150 ንጹሐን ተገድለዋል ብሏል።

የእስራኤል የፋይናንስ ሚኒስትር ፍልስጤማዊያን ጋዛን ጠቅልለው እንዲወጡ መክረዋል።