
ከ 5 ሰአት በፊት
ተቃዋሚዎች “ተጭበርብሯል” በሚል እንደገና እንዲከናወን በጠየቁት የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምርጫ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ቲሺሴኬዲ አሸናፊ መሆናቸው ይፋ ተደረገ።
ፕሬዝዳንቱ 73 በመቶ የሚሆነውን ድምጽ ያሸነፉ ሲሆን የቅርብ ተፎካካሪያቸው ሞይሴ ካቱምቢ ደግሞ 18 በመቶ ድምጽ አግኝተዋል ሲሉ ምርጫ አስፈጻሚ ባለስልጣናት ተናግረዋል።
ከአስር ቀናት በፊት የተካሄደው ምርጫ በሎጂስቲክስ ችግሮች የተሞላ ነበር።
በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች ምርጫው ለሁለተኛ ቀን እንዲራዘምም ተደርጓል።
ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች ዘግይተው የተከፈቱ ሲሆን 30 በመቶ የሚሆኑት የምርጫ ማሽኖች በድምጽ መስጫው የመጀመሪያ ቀን አልሰሩም ሲል አንድ የታዛቢ ቡድን ገልጿል።
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ድምጽ ለመስጠት ለሰዓታት ለመጠበቅ ሲገደዱ አንዳንዶቹ ደግሞ ተስፋ ቆርጠው ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል።
ችግሮቹ የተፈጠሩት የ60 ዓመቱ ትሺሴኪዲ እንዲያሸንፉ ለማጭበርብር ሆን ተብሎ የታቀደ ነው ሲሉ ተቃዋሚዎች ከሰዋል።
ከእሑዱ የምርጫ ውጤት በኋላ በርካታ ዋና ዋና ተቃዋሚዎች የተቃውሞ ሰልፎችን ጠርተዋል።
“የተጭበረበረው የምርጫ ውጤት ከታወጀ በኋላ ህዝባችን በብዛት ወደ ጎዳና እንዲወጣ ጥሪያችንን እናቀርባለን” ሲሉ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
ጦር ኃይሉ ምንም ዓይነት ሁከት እንዳይፈጠር በዋና ከተማዋ ኪንሻሳ የተለያዩ ቦታዎች የተሰማራ ሲሆን የቲሺሴኪዲ ደጋፊዎች ደግሞ ድሉን ለማክበር አደባባይ ወጥተዋል።
የምርጫ ኮሚሽኑ ኃላፊ ቀደም ሲል እንደገለጹት የተቃዋሚ እጩዎች አዲስ ምርጫ እንዲደረግ የፈለጉት “መሸነፋቸውን ስለሚያውቁ ነው… መጥፎ ተሸናፊዎች” በመሆናቸው ነው ብለዋል።
የምርጫ ኃላፊው ዴኒስ ካዲማ አንዳንድ ችግሮች መከሰታቸውን ቢያምኑም ውጤቱ የኮንጎን ህዝብ ፍላጎት የሚያንፀባርቅ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ፕሬዝደንት ትሺሴኪዲ ከሃያ ቀን በኋላ ሁለተኛ የስልጣን ዘመናቸውን ለመጀመር በዓለ ሲመታቸውን ይፈጸማሉ።
- በደቡብ አፍሪካ ምርጫ ሲቃረብ የኢትዮጵያውያን ስቃይ ለምን ይበዛል?ከ 6 ሰአት በፊት
- የዩኬ መከላከያ ሚኒስትር በቀይ ባሕር አካባቢ የሁቲን ጥቃት እንመክታለን አሉከ 5 ሰአት በፊት
- ግሪሊሽ በመኖሪያ ቤቴ ላይ የተፈጸመው ዝርፊያ እጅግ በጣም ስሜት የሚረብሽ ነው አለከ 5 ሰአት በፊት
የአንጋፋው ተቃዋሚ መሪ ኤቲየን ቲሺሴኬዲ ልጅ የሆኑት ፕሬዝደንት ትሺሴኪዲ ለመጀመሪያ ጊዜ እአአ በ2019 መመረጣቸው ይታወሳል።
ከ16ቱ እጩዎች መካከል አንዳቸውም ከአንድ በመቶ በላይ ድምጽ አላገኙም።
ካዲማ አክለው እንደተናገሩት ከተመዘገቡት 41 ሚሊዮን መራጮች መካከል 43 በመቶ ያህሉ በምርጫው ድምጽ ሰጥቷል።
ከ18ቱ የተቃዋሚ ፓርቲ እጩዎች መካከል በፍርድ ቤት ውጤቱን የሚቃወም ስለመኖሩ እስካሁን ግልፅ አይደለም። ካቱምቢ ፍርድ ቤቶች ነጻ ባለመሆናቸው ይህ ዋጋ እንደሌለው ቀደም ብለው ተናግረዋል።
ሕገ መንግሥታዊው ፍርድ ቤት የመጨረሻ ውጤቱን ከአስር ቀን በኋላ ይፋ ከማድረጉ በፊት የትኛውንም ቅሬታ ይቀበላል።
ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በቆዳ ስፋት ከፈረንሳይ በአራት እጥፍ ገደማ ትበልጣለች። መሰረታዊ መሠረተ ልማት ግን የላትም። አንዳንድ ከተሞቿ እንኳን በመንገድ አልተገናኙም።
ከ100 ሚሊዮን የአገሪቱ ህዝብ 2/3ኛ የሚሆነው ከድህነት ወለል በታች የሚኖር ሲሆን በቀን 2.15 ዶላር ወይም ከዚያ ያነሰ ገቢ ያገኛል።
መራጮች የፓርላማ፣ የክልል እና የማዘጋጃ ቤት ተወካዮችን መርጠዋል። በምርጫው ወደ 100 ሺህ የሚጠጉ ዕጩዎች ቀርበዋል።
በምርጫ ዘመቻ ወቅት ፕሬዝዳንት ቲሴሴኪዲ ምስራቃዊ የአገሪቱን ክፍል የተቆጣጠረውን ኤም 23 የተባለውን አማፂ ቡድን ይደግፋሉ ሲሉ የሩዋንዳውን ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜን ደጋግመው ወቅሰዋል። ሩዋንዳ በተደጋጋሚ ክሱን ውድቅ አድርጋለች።
በመጨረሻው የምርጫ ቅስቀሳው ወቅት ትሺሴኬዲ በሩዋንዳ ላይ ጦርነት ለመክፈት ቃል ገብተዋል። ታዛቢዎች ይህንን ብሄራዊ ስሜትን ለመፍጠር ያለመ ንግግር ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።
በምስራቅ አገሪቱ ክፍል ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በተካሄደው ጦርነት ምክንያት ምርጫው አልተካሄደም። ሰባት ሚሊዮን ያህል ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።
በደርዘን የሚቆጠሩ የታጠቁ ኃይሎች የአገሪቱን ከፍተኛ የማዕድን ሀብት የያዘውን አካባቢ ለመቆጣጠር እየተዋጉ ነው።