
ከ 5 ሰአት በፊት
የዩኬ መከላከያ ሚኒስትር ግራንት ሻፕስ አገራቸው የሁቲ ጥቃትን እንደምትመክት ተናገሩ።
የየመን ሁቲ አማጺዮች በቀይ ባሕር አካባቢ የመርከቦችን መሳለጥ ካስተጓጎሉ በኋላ ነው ሻፕስ ይህን አስተያየት የሰጡት።
የየመን ሁቲዎች ጥቃቱን የሚሰነዝሩት እስራኤል በጋዛ ላይ የጀመረችውን መጠነ ሰፊ ጥቃት እንድታቆም ለማስገደድ ነው።
በኢራን እንደሚደገፍ የሚነገርለት የሁቲ ኃይል ለሐማስ ያለውን ድጋፍ በይፋ ገልጿል።
ድጋፉን በተግባር ለመግለጽም ነው ከመቶ በላይ ድሮኖችን እና ሚሳኤሎችን መርከቦች ላይ ሲተኩስ የቆየው።
የሁቲ ኃይል በተለይ ወደ እስራኤል የሚጓዙና ለእስራኤል ስንቅና ትጥቅ እንዲሁም የንግድ ቁሳቁሶችን የጫኑ መርከቦችን ዒላማ ያደርጋል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ሻፕስ በዴይሊ ቴሌግራፍ ባሰፈሩት ጽሑፍ ‘’ሁቲዎች ሊሳሳቱ አይገባም፤ ተግባራቸውን እንመክተዋለን’’ ሲሉ ዝተዋል።
ጨምረውም በቀይ ባሕር አካባቢ ጥቃቶች ችላ ከተባሉ ቀስ በቀስ ወደ አካባቢያዊ ግጭት ሊያመሩ ይችላሉ ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ይህ የቀይ ባሕር ጥቃት በአጭሩ ካልተቀጨ ሌሎችም ከዚሁ መጥፎ ተግባር ትምህርት ወስደው ደቡብ ቻይና ባሕር እና ክሪሚያም ተመሳሳይ ተግባር ሊቀጥል እንደሚችልም ሚኒስትሩ አመላክተዋል።
ሚስተር ሻፕስ ይህ የሁቲ ጥቃት ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ አጋርነት የሚፈትን ነው፤ ዩኬ ከአጋሮቿ ጋር በጽናት ትቆማለች ብለዋል።
አሜሪካ ዓለም አቀፍ የባሕር ኃይል ጥምረትን ባለፈው ወር የመሠረተችው በቀይ ባሕር የሁቲ ጥቃት የመርከቦችን ጉዞ ማስተጓጎሉን ተከትሎ ነበር።
- በደቡብ አፍሪካ ምርጫ ሲቃረብ የኢትዮጵያውያን ስቃይ ለምን ይበዛል?ከ 6 ሰአት በፊት
- “ካሳ ሳይተላለፍልን መሬታችን እየታረሰ ነው” – በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት ከይዞታቸው የሚነሱ የሐይቅ ከተማ አርሶ አደሮች30 ታህሳስ 2023
- በለንደን በፖሊስ አባላት እና ንብረት ላይ ጉዳት ያደረሱ ኤርትራውያን በቁጥጥር ስር ዋሉ31 ታህሳስ 2023
በዚህ ማኅበር ውስጥ ዩኬ፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ባሕሬን፣ ኖርዌይ እና ስፔን ይገኙበታል።
ይህ ጥምረት ኤችኤምኤስ በሚባለው ጸረ ሚሳኤል ከሁቲ የተሰነዘሩ ጥቃቶችን መክቷል።
ትናንት እሑድ ደግሞ የአሜሪካ ባሕር ኃይል ሁቲዎች ትንሽ ጀልባ ተሳፍረው አንድ መርከብ ለማስቆም ሲሞክሩ እርምጃ ወስዶባቸዋል።
በመርከቡ የነበሩ የይድረሱልን ጥሪ ማስተላለፋቸውን ተከትሎ በቅርብ የነበረ የአሜሪካ ሄሊኮፕተር ደርሶ ሦስት ጀልባዎችን ከጥቅም ውጭ አድርጓል።
በጀልባው የነበሩት በሙሉ የተገደሉ ሲሆን 4ኛ ጀልባ ደግሞ ሸሽቷል።
አውሮፓና ኢሲያን በማገናኘት ረገድ ቀይ ባሕር ቁልፍ የሚባል መተላለፊያ ነው። በተለይ ለንግድ መርከቦች አማራጭ የማይገኝለት ወጪ ቆጣቢ መተላለፊያ ነው።
ተንታኞች እንደሚሉት ሁቲዎች መርከቦችን ማስተጓጎላቸውን ከቀጠሉ በበርካታ አገራት የጋዝ፣ የነዳጅና የሌሎች ምርቶች ዋጋ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊኖረው ይችላል።